EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Tuesday 2 August 2016

ጀግንነት ማለት ለእኔ ይህ ነው!

(በወንድይራድ ኃብተየስ)
ጀግና ምን ማለት ነው? ለእኔ በተሰማራበት መስክ በታማኝነት አገሩንና ህዝቡን የሚያገለግል ሁሉ እርሱ ጀግና ነው፡፡ አገርን ከወራሪ ከጠላት መከላከል የቻለ ለአገሩና ለህዝቡ አሊያም ለብዙሃኑ ህይወቱን የሰጠ እሱ ጀግና ነው፤ በግብርናው ዘርፍ ተሰማርቶ አገርንና ህዝብ በምርት እንዲትረፈረፍ ያደረገ፣ በመንግስት ስራ ተሰማርቶ ህብረተሰቡን በቅንነትና በታማኝነት ያገለገለ እሱ ጀግና ነው፤ በንግድ ተሰማርቶ የተጣለበትን ግብርና ታክስ በአግባብ የሚከፍል እሱ ጀግና ነው፤ ወዘተ… ብቻ ሁሉም በተሰማራበት አገርንና ህዝብን በቅንነት በታማኝነት የሚያገለግሉ ሁሉ ለእኔ ጀግኖች ናቸው።

በሀገራችን ያሉ አንዳንድ ነጋዴዎች ከሚያገኙት ጥቅም ጋር ሲነፃፀር ተገቢውን ግብር አይከፍሉም የሚል ትችት ሲቀርብ እናያለን፣ እንሰማለን፡፡ እንዲያውም አንድ መካከለኛ ደመወዝ የሚከፈለው የመንግስት ሠራተኛ በዓመት የሚከፍለውን ግብር ያህል እንኳ የማይከፍሉ ባለመደብሮች፤ ካፌዎች፤ ሆቴሎች፤ ወዘተ እንዳሉ አንዳንዶች በአደባባይ ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ኢትዮጵያ ካላት የህዝብ ብዛትና ሃብት አኳያ ከሰሃራ በታች ካሉ አገሮች እንኳን ሲነጻጸር የምትሰበስበው ግብር ዝቅተኛ የሚባል ነው፡፡
አንድ ዜጋ አገር ሰላም ሆኖ ሰርቶ ከሚያገኘው ጥቅምና ገቢ ተገቢውን ግብር ካልከፈለ አገር ወዳድነት እምኑ ላይ ነው? ህዝባዊነት የቱ ጋ ነው? ሀገር ሰላም ልትሆን የምትችለው የጸጥታ አስከባሪዎች ሲኖሩ ነው፡፡ እነዚህ አካላት ሊኖሩ የሚችሉት ደግሞ ሁላችንም የሚገባንን ማድረግ ስንችል ብቻ ነው፡፡ በሀገራችን ያለውን ልማት ለማስቀጠል ከእያንዳንዳችን ምን ይጠበቃል? የእኔ ድርሻ ምንድነው? ምን ላበረክት እችላለሁ? የሚለው አተያይ የእያንዳችን እሳቤ መሆን መቻል አለበት፡፡ ዜጋው ተገቢውን ግብር መክፈል ካልቻለ መንግስት ሊያቀርባቸው የሚገቡ ማህበራዊ አገልግሎቶች ሊሟሉ አይችሉም፡፡ የመንግስት እያንዳንዱ ወጪ ከእያንዳንዳችን ኪስ የሚሰበሰብ ገንዘብ እንጂ ከሰማይ የሚወርድ መና አይደለም፡፡ ግብርን በታማኝነትና በወቅቱ መክፈል መቻል ለእኔ ኩራት ነው፤ እኔ ግብር መክፈል የቻልኩት ሰርቼ መጠቀም በመቻሌ ነው የሚል ስሜት በሁሉም የግብር ከፋይ አካላት መጎልበት መቻል አለበት፡፡
በሀገራችን ብዙውን ጊዜ ግብርን በሰዎች ላይ በግዳጅ እንደተጫነ "ዕዳ" አድርጎ የመመልከት አዝማሚያ ለረዥም ዘመናት ሰፍኖ ከመቆየቱ ጋር ተያይዞ ግብርን መክፈል ከውዴታ ይልቅ የግዴታ ይዘቱ አመዝኖ እንዲታይ የተደረገበት ሁኔታ ለአገራችን የግብር አሰባሰብ ደካማ መሆን የራሱ አስተዋጽዎ አበርክቷል፡፡ በዚህም ሳቢያ ይመስለኛል አንዳንዶች ግብር መክፈልን እንደብሄራዊ ኩራት ከመቁጠር ግብር መክፈልን እንደ እዳ የሚቆጥሩት፡፡ አንዳንዶች ግብር መሰወርን አገርና ህዝብን መስረቅ መሆኑን አይገነዘቡትም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን ስለ ግብር ያለው አስተሳሰብ እየተለወጠ በመምጣቱ ሁኔታዎች መሻሻል እያሳዩ ናቸው፡፡ በርካታ ነጋዴዎች ግብራቸውን በታማኝነትና በወቅቱ በመክፈል የህዝብና የአገር አጋርነታቸውን በተግባር በማስመስከር ላይ ይገኛሉ፡፡ እንዲህ ያሉ ለአገርና ለህዝብ የሚያስቡ ወገኖች ሊመሰገኑ ይገባል፡፡
ግብር መክፈል ፈጣን ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገትን ለማጋገጥና የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ትርጉም ባለው ሁኔታ ለማሻሻል፣ የአገርን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ፣ ከድህነት ለመውጣት፣ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍልን ለማስፈን ትልቅ ሚና አለው፡፡ በአሁኑ ወቅት በበርካታ ሀገሮች ዘንድ ግብርን መክፈል እንደ ዋነኛ የዜግነት መብት ማረጋገጫና ክብር መገለጫ ሆኗል፡፡ በአገራችንም በርካቶች የሚጠበቅባቸውን ግብር በአግባቡና በወቅቱ በመክፈል አገራዊ ግዴታቸውን በመወጣት ላይ ይገኛሉ፡፡ ይሁንና አሁንም ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ነጋዴዎች ግብር መሰወርን እንደመብት የሚቆጥሩ እንዳሉ መመልከት ይቻላል፡፡ እንዲህ ያለ አስነዋሪ ተግባራት ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችን ወደ ትክክለኛ መስመር እንዲመለሱ መምከርና ማስተካከል የሁላችንም ስራ መሆን አለበት፡፡
በአገራችን የመሠረተ ልማትና ማህበራዊ የአገልግሎት ዘርፎች ዝርጋታና ማስፋፋያ ሥራዎች ላይ መንግስት የልማት ኃይል ሆኖ የመስራቱ ፋይዳ የጎላ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ምክንያቱም የአገራችን የመሰረተ ልማት ሁኔታ መሻሻል ቢያሳይም አሁንም እጅግ ኋላ ቀርና ከፍተኛ የማስፋፋት ስራ የሚጠይቅ ነው፡፡ ይህ ደግሞ እውን የሚሆነው መንግስት ተገቢውን ግብር ማሰባሰብ ሲችል ብቻ ነው፡፡
መንግስት ለዜጎች የስራ ዕድል እንዲፈጠር ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በነጻ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት መንግስት የግል ሴክተሩ ሊሞላው በማይችላቸውና የገበያ ክፍተት ባለባቸው የልማትና አገልግሎት ዘርፎች ውስጥ በተመረጠ መልኩ ጣልቃ እየገባ ክፍተቶቹን በመሙላት ኢኮኖሚያዊ ዕድገቱን በማፋጠን ላይ ይገኛል፡፡ የእነዚህን የልማት ዝርጋታና ማስፋፊያ ወጪዎች ለመሸፈን የሚያስፈልገው ፋይናንስም የዚያኑ ያህል እጅግ በርካታ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግስት መሰረተ ልማትን በመላ አገሪቱ ለመዘርጋት በቢሊዮን የሚቆጠር ብር በማውጣት ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ገንዘብ ከየትም የሚመጣ ሳይሆን ከእያንዳንዳችን ኪስ በግብር የሚሰበሰብ እንደሆነ ታሳቢ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም ሀገሪቱ ትመራበት የነበረው የንግድ ሥርዓት ኋላ ቀር፤ ነጻ የገበያ ውድድርን የማይጋብዝና ከዚህም በላይ በኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ የታጠረ ስለነበር አሉታዊ ጎኑ ያመዘነ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ከዚህ አንጻርም የግብር ክፍያና አሰባሰቡም በበርካታ ውስብስብ ችግሮች ውስጥ እንዲያልፍ ግድ ብሎ ቆይቷል፡፡ በመሆኑም ለረዥም ዓመታት ሲያገለግል የነበረውን ኋላ ቀር ሕግ በማስቀረት በምትኩ ዘመናዊ የንግድ ሥርዓትን ለማስፈን በሚያስችል አቅጣጫ የነበሩ ጉድለቶች ተገምግመውና ታርመው አዲስ የንግድ ሕግ መውጣቱ ይታወሳል፡፡ ይህ ሁኔታ በአገራችን የግብር አሰባሰብ ስርዓት ላይም አዎንታዊ ለውጦችን አምጥቷል፡፡
የንግዱ ኀብረተሰብ በሚካሄዱ የልማት ሥራዎች ላይ ዋነኛ ተሳታፊ ለመሆን ያለውን ተነሳሽነት ከሚያሳይበት መንገድ አንዱ ትክክለኛ ግብርን በወቅቱ በመክፈል ብሔራዊ የዜግነት ግዴታን መወጣት ሲችል ነው፡፡ አገራችን ከድህነት ልትወጣ የምትችለው፤ ሁሉም ዜጎች ከአገሪቱ ሃብት እኩል ተጠቃሚ የሚሆኑበት አሰራር የሚዘረጋው መንግስት የማህበራዊ መገልገያዎችን ማስፋፋት ሲችል ነው፡፡ ይህ ደግሞ እውን የሚሆነው እያንዳንዱ ግብር ከፋይ ዜጋ የተጣለበትን ግብር በአግባብና በታማኝነት መክፈል ሲችል ብቻ ነው፡፡
በአገራችን ግብር የመክፈል ስሜት ከፍተኛ መሻሻል እንዳሳየ አሌ የሚባል አይደለም፡፡ የአገራችን የኢኮኖሚ ዕድገት መፋጠን እንዲሁም የመንግስት በጀት ከዓመት ወደ ዓመት እያደገና እየተመነደገ የመጣው የአገራችን የግብር አሰባሰብ ስርዓትም ለውጥ እያሳየ መምጣቱን ይመሰክራል፡፡ ይሁንና አሁንም አገራችን ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ገቢ ለማሰባሰብ ረጅም መንገድ መጓዝ ይኖርባታል፡፡ ይህ ሥራም በዘመቻ መልክ የሚሰራ የአንድ ጊዜ ተግባር ሳይሆን ቀጣይነት እንዲኖረው ተደርጎ በቋሚነት ሊሰራበት ይገባል፡፡ በግብር አወሳሰንም ሆነ አከፋፈል ላይ ችግር ሊፈጠር ይችላል፡፡ በግብር አሰባሰብ ሂደት የሚፈጠሩ የአፈጻጸም ስህተቶችና የሚመለከተው የመንግስት አካል በቀየሰው የቅሬታ አቀራረብና ማስተናገጃ ሥርዓት እልባት የሚሰጣቸው ይሆናሉ፡፡ ይህ ደግሞ ሕጋዊና የሰለጠነ አካሄድ ነው፡፡
መንግስት በአሁኑ ወቅት ኀብረተሰቡን አሁን ካለው ሁኔታ በተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግና በምጣኔ ሀብት የጠነከረች ሀገር ለመፍጠር ከምንጊዜውም በተሻለ ሁኔታ እየሰራ ይገኛል፡፡ መንግስት ይህን ከባድ ኃላፊነት በብቃት እንዲወጣ ከተፈለገ ደግሞ ሊኖር የሚችለው አማራጭ ወቅታዊና ትክክለኛ ግብርን የመሰብሰብ አቅምን በአስተማማኝ መገንባት ሲችል ብቻ ነው፡፡
የሚሰበሰበው ግብር፣ ታክስ እንዲሁም የአገልግሎትና የመጠቀሚያ ክፍያዎች በበኩላቸው ከህዝብ ተሰብስበው ተመልሰው ለሀገርና ለህዝብ ጥቅም የሚውሉ መሆናቸውን መገንዘብና አምኖ መቀበል ተገቢ ነው፡፡ እያንዳንዱ ግብር ከፋይ ዜጋ አገር ወዳድነቱንና ወገንተኝነቱን ግብር በመክፈል መግለፅ ይኖርበታል፡፡ ግብር የሚያጭበረብር ህዝብንና መንግስትን እንደማጭበርበር ይቆጠራል፡፡ ምክንያቱም መንግስት አገርን ሊቀይሩ የሚችሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን የሚገነባው በሚሰበስበው ግብር እንደሆነ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ግብር መክፈል ያኮራል፣ ግብር መክፈል የአገርንና የህዝብን ደህንነት ያስጠብቃል፣ ግብር መክፈል መሰረተ ልማትን ያስፋፋል፣ በአጠቃላይ ግብር መክፈል ልማትን ያፋጥናል፡፡ ግብር መክፈል ኩራት ነው፡፡ ግብር መክፈል በዚህ አግባብ ቢታይ መልካም ይመስለኛል፡፡
(ምንጭ፡ አይጋ ፎረም)

No comments:

Post a Comment