EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Monday 13 October 2014

ሰንደቅ አላማችን በተለያዩ የመንግስት ስርዓቶች


የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ታሪካዊ ዳራ ሲታይ ከ100 አመት በላይ ታሪክ ያለውና የተለያዩ መንግስታዊ ስርዓቶችን ያለፈ ነው፡፡ በዚህ እድሜውና የመንግስታት መቀያየር ውስጥም አሁን ያለበትን ቅርፅ፤ አርማና ትርጓሜ ከመያዙ በፊት በተደጋጋሚ ተቀያይሯል፡፡

እነዚህ በየስርዓቱ የነበሩ ሰንደቅ አላማዎች የጋራ የሆኑ መለያዎች ነበሯቸው፡፡ በሁሉም ሰንደቅ አላማዎቻችን የነበሩት ቀለሞች አረንጓዴ፤ ቢጫና ቀይ ናቸው፡፡ ከ1890 በፊት ከነበረው እና ከደርግ ውድቀት በኋላ በሽግግሩ ወቅት ለአጭር ጊዜ ከነበረው ሰንደቅ አላማ ውጪ በሁሉም ላይ አርማዎች ነበሩ፡፡ በተጨማሪም ከ1890 በፊት ከነበረው ሰንደቅ አላማ ውጪ በሌሎቹ ላይ ሶስቱ ቀለሞች /ከላይ ወደታች በቅደም ተከተል አረንጓዴ፤ ቢጫና ቀይ/ አግድም ተሰድረው ይገኛሉ፡፡


ይህ እንዳለ ሆኖ ሰንደቅ አላማዎቹ ላይ በሚሰፍረው አርማ የተነሳ የተለያዩ አላማዎችን እሴቶችን ሲያስተላልፉ ኖረዋል፡፡ በአፄ ሚኒሊክ ዘመነ መንግስት በሰንደቅ አላማው ላይ ዘውድ የጫነ አንበሳ መስቀል ይዞ ይታይ ነበር፡፡ በአፄ ሃይለስላሴ ዘመንም ይሄው አንበሳ ሞዓ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ የሚል ፅሁፍና ኮከቦች ተጨምረውለት እስከ ወታደራዊው የደርግ ስርዓት ድረስ ቀጥሏል፡፡ ደርግ ስልጣኑን እንደያዘ አንበሳው ላይ የነበረውን ዘውድ ያነሳ ሲሆን በመስቀሉም ቦታ የጦር ጫፍ ምልክት አስቀምጧል፡፡ በ1979 ደርግ አንበሳውን ሙሉ በሙሉ በማውጣት በምትኩ ጦር፤ ጋሻ፤ ማረሻ፤ የስንዴ ዘለላና ሌሎች ምልክቶችን ያካተተ አርማ አስቀምጧል፡፡ ከኢሰፓ ምስረታ በኋላም ሌላ ለውጥ በማድረግ “የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ” የሚል ፅሁፍና የኢሰፓ መገለጫ የሆነ አነስተኛ አርማ በውስጡ ያካተተ አርማ በሰንደቅ አላማው ላይ እንዲሰፍር አድርጓል፡፡ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ደርግ ከተገረሰሰ በኋላ በነበረው የሽግግር መንግስት ወቅት ምንም አይነት አርማ በላዩ ላይ ሳይኖረው ቆይቷል፡፡ የኢፌዴሪ መንግስት ከተቋቋመ ጀምሮ እስካሁን ደግሞ በክብ ሰማያዊ መደብ ላይ የተቀረፀ ብሔራዊ አርማ አለው፡፡

ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው በሰንደቅ አላማ ላይ አርማን ማስቀመጥ ከኢትዮጵያ የሰንደቅ አላማ ታሪክ ያልተናነሰ እድሜ ያለው ነው፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ አርማ ሳይኖረው አገልግሎት ውስጥ የዋለበት ጊዜ የለም ማለት ይቻላል፡፡ እዚህ ላይ ውይይት ሊያስነሳ የሚችለው ጉዳይ በየዘመናቱ አርማዎቹ የያዙት መልዕክት እንጂ በርግጥ ሰንደቅ አላማ ላይ አርማ ማስቀመጥ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በብዙዎቹ የአለም አገራትም የሚደረግ በመሆኑ አከራካሪ ጉዳይ ሊሆን አይችልም፡፡

የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ

በኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀፅ ሦስት መሰረት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ከላይ አረንጓዴ፣ ከመሃል ቢጫ ከታች ቀይ ሆኖ በክብ ሰማያዊ መደብ ላይ የተቀረፀ ብሔራዊ አርማ ይኖረዋል። ህገ መንግስታችንን ለመዘርዘር የወጣው አዋጅ ቁጥር 654/2001 ደግሞ ሰንደቅ አላማችን የሪፐብሊኩ ሉአላዊነትና የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በእኩልነትና በመፈቃቀድ ላይ የመሰረቱት ዴሞክራሲያዊ አንድነት ምልክት መሆኑን በአፅንኦት ያብራራል።

በአዋጁ መሠረት ክቡ ሰማያዊ መደብ የሚወክለው የልማትም የዴሞክራሲም ምንጭ የሆነውን ሰላማችንን ነው። በብሔራዊ አርማው ውስጥ የሚታዩት ቀጥተኛና እኩል መስመሮች ደግሞ የብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዲሁም የሃይማኖቶችን እኩልነት ይወክላሉ። ቀጥታና እኩል ከሆኑት መስመሮች የተዋቀረው ኮከብ ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በመፈቃቀድ የመሰረቱት ዴሞክራሲያዊ አንድነት አርማ ነው።

በቅርፁም ሆነ በይዘት በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ላይ የተጨመሩት አዳዲስ እሴቶች እነዚህ ሦስት መልዕክቶች ናቸው። ሰላም፣ እኩልነትና ዴሞክራሲያዊ አንድነት። እነዚህ እሴቶች በነባሩ የሰንደቅ አላማ በጐ ታሪካችን ላይ የተደመሩ አዎንታዊ እሴቶች ብቻ አይደሉም። ይልቁንም በአገራችን የከፋ ድህነት፣ የኋላቀርነትና የጦርነት ምዕራፍ ተዘግቶ አዲስ የለውጥና የእድገት ምዕራፍ መከፈቱን ያበሰሩ የለውጥና የእድገታችን ምንጮች ናቸው።

የቀደሙት ስርዓቶች አርማዎች ሲታዩ የገዥዎችን የበላይነትና እነርሱ ነን ብለው የሚያስቡትን ስዩመ እግዚአብሔርነት የሚሰብኩ እንጂ ሕዝባዊነትን የሚያንፀባርቁ አልነበሩም፡፡ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ግን የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ጥቅም፤ ፍላጎትና መብቶች መሰረት ያደረገ የአንድነታቸው ተምሳሌት ነው፡፡

ማንም እንደሚገነዘበው ከሰላም፤ ከእኩልነትና ከዴሞክራሲያዊ አንድነት አንፃር ያለፈ ታሪካችን የተዛባ ብቻ ሳይሆን በእጅጉ የሚያሸማቅቅ ነበር። አገራችን ለዘመናት ብዙሃነታችንን ማስተናገድ አቅቷት የተለያዩ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሃይማኖቶች እስር ቤት ሆና ኖራለች። እኩል በተፈጠርንባት መሬት ላይ እኩል እንድንሳተፍና እንድንጠቀም እድል የሚሰጥ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ጠፍቶ ለዘመናት በዘግናኝ የድህነት አዙሪት ውስጥ ቆይተናል።

ይህ አስከፊ ታሪካችንን ዛሬ በመሰረቱ ተቀይሯል። በአሁኑ ወቅት የዜጐች የጋራና የተናጠል መብቶች ያለገደብ የተከበሩበት ህገ መንግስት ባለቤቶች ነን። በዚህ ምክንያት ዛሬ ደረጃው ሊለያይ ይችላል እንጂ ሕዝብ ያለበት የሃገራችን ክፍል ሁሉ ፈርሶ እየተገነባ ነው። ሰላም፣ እኩልነትና ዴሞክራሲያዊ አንድነታችን በወለዱት ልማት አዲሲቷ ኢትዮጵያ በመገንባት ላይ ነች።

ባለፉት አስራ ሶስ  ዓመታት ባለሁለት ዲጂት የኢኮኖሚ እድገት  አስመዝግበናል። በትግበራ ላይ ያለ ሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ሲጠናቀቅም ሀገራችን በበርካታ ዘርፎች መሰረታዊ ለውጦችን በማስመዝገብ እስካሁን የተመዘገቡ ስኬቶች ወደ ሌላ ከፍታ እንደሚሸጋገሩ ይጠበቃል፡፡ ረጅም በማይባል ጊዜ ውስጥ ደግሞ ለኑሮና ለስራ የምትመች አገር ትኖረናለች። ከዚህ አንፃር መጪው ጊዜ በእርግጥም ብሩህ ነው። ሰንደቅ አላማችንም የዚህ ብሩህ ጉዞ ምልክት ነው

ሰንደቅ አላማችን የሉዓላዊነታችን መገለጫ፣ በብዝሃነታችን ላይ ለተመሰረተው አንድነታችን አርማ ነው!!

2 comments:

  1. አንድ ሆኖ የኖረን ህዝብ እየበታተናችሁ ደሞ አታፍሩም የበፊቱን ለመውቀስ ስትሞክሩ ማፈሪያዎች።

    ReplyDelete
  2. አንድ ሆኖ የኖረን ህዝብ አባልታችሁ አባላታችሁ ይኸው እያነካከሳችሁት ነው ብሔረሰብ ቅብርጥሴ ብላችሁ ጌታ የጃችሁን ይስጣችሁ በታተናዃት ሀገሪቷን

    ReplyDelete