EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Monday 16 July 2018

ከአስመራ እስከ አዲስ አበባ የተዘረጋ የማያረጅ የፍቅር ሸማ


                                                     


                                                                                             
                        በኤፊ ሰውነት

 "ተዛወሪ አውቶብሰይ ተዛወሪየ
አስመራ ሸዋ ኾይኑ መፋቐርየ፡፡
ኮሚደረ ፀቢሒ አቡንየ
ሰላምን ፍቐርን ዘይብሉ አይጥዕሙንየ፡፡
ተዛወሪ ነፋሪት ነፋሪትየ
አክሱም መቐለ ኾይኑ መፋቐርየ፡፡" 

ይህን በግርድፉ ወደአማረኛ ስናመጣው አውቶብሴ ዙሪ አስመራና ሸዋ ፍቅር ሆነዋልና፡፡ ሰላምና ፍቅር ከሌለበት የቲማቲም ወጥም አይጣፍጥም፡፡ አንቺ አውሮፕላን ዙሪ አክሱምም መቐለም ፍቅር ሆነዋልና የሚል ትርጉም አለው፡፡ ይህ ዜማ ድምፃዊ ዳዊት ሽላን የአገራችን ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አሕመድ የኤርትራ ጉብኝት ወቅት በነበረው በተደረገው የእራት ግብዣ ስነ-ሥርዓት ላይ ያዜመው ነበር፡፡ ዜማው እንኳን ከአጠገብ በዛው በኤርትራ ምድር ላይ ሆኖ ለሚሰማው ይቅርና በቴሌቭዥን መስኮት ሁነቱን ስንከታተል ለነበረው አንጀት ድረስ ሰርስሮ የሚገባ ዜማ ነበር፡፡ በእርግጥም ያ የፀብ ግድግዳ ተደርምሷል፡፡ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ሕዝብ ፍቅሩን አድሷል፡፡ ወንደማማች ሕዝቦች ፀብን ሳይሆን ፍቅርን፣ አብሮ ማደግን፣ አብሮ መልማትን፣ ሁለት ሉዓላዊ አገር ግን እንደ አንድ ትልቅ ሕዝብ ሆነው ወደፊት ለመራመድ ቃል የተገባቡት እለት ነው፡፡ 
 

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለውን ግንኙነት ወደ አዲስ የትብብር ምዕራፍ በማሸጋገር ችግሮችን ዲፕሎማሲያዊ በሆነ መንገድ መፍታት እንደሚገባና የሁለቱንም አገራት ሕዝቦች ተጠቃሚ ማድረግ የሚቻልበት ጉዳይ ላይ ማተኮር እንደሚገባ ባስተላለፈው ውሳኔ መሰረት የኢሕአዴግ ሊቀመንበርና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚንስቴር ዶር አብይ አሕመድ የመጀመሪያ የሥልጣን ርክክብ ወቅት በፓርላማ ባደረጉት ንግግር ይህን መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የአልጀርሱን ስምምነት በመቀበል በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል እንደሚሰራ ማሳወቁን ተከትሎ የኤርትራ መንግስት አዎንታዊ ምላሹን ሰጥቷል፡፡ ይህን አዎንታዊ ምላሽ ተከትሎ ነው እንግዲህ ዶ/ር አብይ በኤርትራ መንግስት በተደረገላቸው ግብዣ በኤርትራ ጉብኝት ያደረጉት፡፡ የሁለቱ አገራት ሕዝቦች ኢትዮጵያ የሰላም ጥሪዋን ባስተላለፈች ማግስት ነው ህልማችን እውን ሊሆን ነው በሚል ልጅ ከአባቱ ሚስት ከባሏ እናት ከልጇ ወዳጅ ከዘመዱ የሚገናኝበትን ቀን በተስፋ ይጠባበቅ የጀመረው፡፡ 

የኤርትራ መንግሥት ለሰላም ጥሪው አዎንታዊ ምላሽ በሰጠ ማግስት የሁለቱ አገራት ህዝቦች የፍቅር ዜማ አዜሙ፤ በደስታ ፈነጠዙ፤ ህልማቸው በእርግጥም ቅዠት አልነበረም፡፡ ዶ/ር አብይ አስመራ ለጉብኝት በመሄድ የሁለቱንም ሕዝቦች ህልምና ፍላጎት ማሰሪያ አበጅተውለታል፡፡ እናቶች የደስታ እንባ እያነቡ አምላካቸውን አመሰገኑ፡፡ የፀብ ግድግዳ ተደርምሷል፡፡ አሁን በእኛ መካከል ፍቅር እንጂ ፀብ የለም ሲሉ አዜሙ፤ እልል አሉ፡፡ ፍቅር የተራበ ወንድማማች ሕዝብ፡፡ እንባስ ይህን ደስታ ይመጥነው ይሆን? እልልታስ ይህን ሃሴት ይገልፀው ይሆን? ለዚህ በቅርብ እውን ይሆን ለማይመስለው የሁለቱ አገራት ግንኙነት ይሄ ዜና እንኳን እነዚህን ሕዝቦች ዓለምን ጮቤ ያስረገጠ ታሪካዊ ክስተት ሆኗል፡፡ የአፍሪካ መሪዎች ይህን ተከትሎ በቲውተር ገፆቻቸው እንኳን ደስ አላችሁ በሚል ያስተላለፉትን መልዕክት ማየት በእርግጥም የሁለቱ አገራት ጉዳይ የአፍሪካ ቀንድ ዓብይ ጉዳይ መሆኑን ለመገንዘብ ያስችላል፡፡ ደስታው ከእኛ ደስታ በላይ የብዙዎች ደስታ መሆኑን ያሳየ ነው፡፡ የዓለም መንግሥታት ከጎናችሁ ነን ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ 

በሁለቱ አገራት መካከል የፍቅር ድልድይ ተግንበቷል፤ አንዳችን ለአንዳችን እንኖራለን እንሰራልን ሲሉ የሁለቱ አገራት መሪዎች በሕዝቦቻቸው ፊት ቃል ገብተዋል፡፡ አገራቱ የሰላምና የጋራ ትብብር ስምምነት በመፈራረም ወደፊት እንጂ ወደኋላ እንደማይመለሱ አስረግጠው ለሕዝቦቻቸው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ የሁለቱን አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ መደበኛነት ለመመለስ፣ በሁለቱ አገራት መካከል አዲስ አበባና አስመራ ኢምባሲዎቻቸውን በመክፈት የድፕሎማሲ ግንኙነት ለመጀመር የሚያስችል፣ የሁለቱ አገራት አየር መንገዶች ወደ ሁለቱ አገራት እንዲበሩና የስልክ አገልግሎት እንዲጀመር እንዲሁም የወደብ አገልግሎት ለመጀመር የሚያስችል የመግባቢያ ስምምንት በፊርማቸው አፅድቀዋል፡፡ የስምምነቶቹ መፈረም የጥላቻን በር ዘግቶ አዲስ የትብብር ምዕራፍ የከፈተ መሆኑም ለሁሉም ብስራት ነው፡፡

ዛሬ ደግሞ ይህ ቃል ማሰሪያው ሊጠበቅ ኢትዮጵያውያንም የኤርትራ ሕዝብ በፍቅር ተቀብሎ በፍቅር የሸኘላቸውን መሪያቸውን በፍቅር አፀፋውን ሊመልሱ እንግዳቸውን ለመቀበል ሽር ጉድ እያሉ ነው፡፡ የኢፌዴሪ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነገ ቅዳሜ ማለዳ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቄ አዲስ አበባ ይገባሉ፡፡ የአዲስ አበባ ሕዝብና አጎራባች ከተሞች በሚደረገው አቀባበል ላይ ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን ተላብሰው እንግዳቸውን እንዲቀበሉ መልዕክት ተላልፏል፡፡ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በሶስት ቀናት ቆይታቸው የሃዋሳ ኢንዱስሪ ፓርክን የሚጎበኝ ሲሆን በሚሊኒዬም አዳራሽ 25 ሺህ ሰው በሚገኝበት ደማቅ ዝግጅት እንደሚኖር አስታውቋል፡፡ 

የኢትዮጵያና የኤርትራ ጉዳይ እልባት ማግኘቱ የሁለቱን ሕዝቦች ቤት በደስታ ያሞቀ ዜና ሆኗል፡፡ ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው ዓመታትን ያስቆጠሩ ቤተሰቦች ደስታቸው ከህልፈታቸው በፊት ሆኗል፡፡ የስልክ መስመር በተለቀቀ ማግስት ሃሎ ሃሎ እንኳዕ ደስ በለኩም ያልተባባለ የለም፡፡ ከኢትዮጵያ ሬዲዮው ጋዜጠኛው አዲስ አለም ሓድጎን ጀምሮ ይህን ታሪክ የሚጋሩ ግለሰቦችን ያነጋገረው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትና የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ይህ ክሰተት ምን ማለት እንደሆነ ባለታሪኮቹ የደስታ እንባ እያፈሰሱ ሲገልፁ አድምጠናል፡፡ ይህ ከአስመራ እስከ አዲስ አበባ የተዘረጋው የፍቅር ሸማ አያረጅም አይበላሽም ይደምቃል እንጂ አይታጠፍም፡፡ ይህ ብስራት የሁለቱ አገራትና ሕዝቦች ብስራት ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ቀንድ ብስራት ነው፡፡ ዛሬ ኤርትራ ውስጥ መሽጎ አገር ማተራመስ ቦታ የለውም፡፡ አሁን በእነዚህ አገራት መካከል የነበረው ግንብ በፍቅር ተደርምሷል፡፡ አሁን የሚጠበቅ የሁለቱ አገራት ሕዝብና መንግሥት ይህን ሁኔታ ወደላቀ ደረጃ ማድረስ ነው፡፡ 

ሚዲያውም የሃይማኖት አባቶችም እስካዛሬ ያጣነውን መልማትና መተባበር ወደፊት ለማራመድ ሁሉም መትጋት እንደሚገባው መልዕክት ማስተላለፍ ነው፡፡ የነገው ጉብኝትም የተሳካ እንዲሆን ኢትዮጵያውያን ፍቅር እንደሚያሸንፈን በተግባር ማሳየት ይገባናል፡፡ ፍቅር ያሸንፋል፡፡ የሁለቱ አገራት ግንኙነት በፍቅር ያብባል፡፡

No comments:

Post a Comment