EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Saturday 21 April 2018

ፍሎረንስ እና ጉባ ምንና ምን ናቸው?


(በሚሚ ታደሰ)
በአዉሮፓ ታሪክ ዉስጥ መካከለኛዉ ዘመን ተብሎ የሚታወቀዉ ጊዜ የአውሮፓ አህጉር፤ በተለይም ምእራብ አዉሮፓ ከዳር ዳር እግር ከወርች በያዘዉ የጨለማ ዘመን (The Dark Age) ዉስጥ ድህነት፤ ርሀብ፤ በሽታ፣ እርዛትና ተስፋ ማጣት አሽመድምዶት ታሪክ በማይዘነጋዉ የሰቆቃ ጊዜን ለመቶ አመታት ያለፈበት ዘመን ነዉ፡፡ የመቶ አመቱ ጦርነትና የሮማን ኢምፓየር መፈረካከስ የተገለጠበት፤ የእርስ በእርስ መተላለቅ፣ መሀይምነት፣ ርሀብ፣ ተስቦ፣ ወዘተ… አዉሮፓን ወደ ሙት አዉድማነት የቀየረበት፤ አዉሮፓዉያን የማይዘነጉት የሰቆቃ ጊዜ ነበር፡፡

ከዚህ ሁሉ ዉርጅብኝ በኋላ አዉሮፓ ዳግም ወደ ነበረችበት የስልጣኔና የታላቅነት ዘመን ለመመለስ ከጣሊያኗ ፍሎረንስ ከተማ የለዉጥ ፍላጎትን ያዘሉ ድምጾች መሰማት ጀመሩ፡፡ እነ ሊዮናርዶ ዳቬንቼ፤ ዳንቴ፤ ማይክል አንጀሎና መሰሎቻቸው በጥበብ ስራቸዉ የአዉሮፓን ጣረ ሞት ለማደብዘዝ በብርቱ ታገሉ፡፡ ከምድረ ብሪታኒያም እነ ቶማስ ሞር በተለይም ዊሊያም ሼክስፒር በቱባ የስነ ጹሁፍ አብዮቱን ይበልጥ አቀጣጠለዉ፡፡ የጀርመናዊዉ ጉተምበርግ የህትመት ማሽን ፈጠራም ለጸረ መሀይምነት ትግሉ ተጨማሪ ጉልበትን ይዞ ከተፍ አለ፡፡ ይህም በአህጉሩ የጨለማዉ ዘመን ማብቂያ ትግል ወደማይቀለበስበት ምእራፍ ለመሸጋገሩ ማሳያ ሆነ፡፡ ይህ ወቅት ነው እንግዲህ ለአዉሮፓ ህዳሴ (renaissance) በር ከፋች የሆነው፡፡
ህዳሴ ወይም ሬኔሳንስ የሚለው ቃል ከፈረንሳይኛ ቋንቋ የተወሰደ ሲሆን በአህጉሩ የተካሄደዉን በእዉቀት መመንደግን፤ ድህነትን ድል መንሳትን፤ ለዉጥ መሻትን እንዲሁም የአስተሳሰብ አድማስን በማስፋት ለኢኮኖሚያዊ እድገት፤ ለፈጠራ፤ ለጥበብ ስራ ትኩረት መስጠትን በአጠቃላይ በአስተሳሰብ ዳግም ዉልደትን (rebirth) ዘመንን ያመላክታል፡፡ ከዛም ጊዜ ወዲህ አዉሮፓ ድህነትን እስከ ወዲኛዉ በሚባል ደረጃ ተሰናበተዉ፤ በጊዜም ሂደት ለዉጡን ከትዉልድ ወደ ትዉልድ በማስቀጠል በኢኮኖሚ የፈረጠመ፤ የፈጠራ፤ የሳይንስና የቴክኖሎጂ አህጉር ሆነ፡፡ አሁን ላይ ከአህጉሩ አልፎ ለሌላዉ የአለም ክፍል የሚበቃ የዳበረ ኢኮኖሚን መፍጠር ችሏል፡፡
አንዳቸዉ ከአንዳቸዉ በብዙ መስፈርቶች ይለያያሉ እንጂ በአራቱም የአለም አቅጣጫዎች የለዉጥ እርሾ የሆኑ ከተሞች፣ ክልሎች፣ አካባቢዎች መኖራቸዉ አያጠያይቅም፡፡ አዉሮፓን ለመቶ አመታት አሸልቦበት ከነበረበት የድህነት እንቅልፍ፤ የኋላ ቀርነትና የሰመመን ጉዞ በለዉጥ ደዉሏ ያነቃችዉ የጣሊያኗ ፍሎረንስ ከተማ ነች፡፡ በዘመናት የጊዜ ሂደት በለዉጥ ማእከልነቷ ታሪክ እራሱን የደገመባት ልዩ ስፍራ አሁን ላይ ታይታለች፡፡ እርሷም በምስራቅ አፍሪካ የዉሃ ማማ ተብላ ከምትታወቀው ሀገር የህዳሴ ደወሏን ያሰማችው ጉባ ነች፡፡
ከአክሱም እስከ ጋፋት፣ ከላሊበላ እስከ ሐረር፣ ከጢያ እስከ ኮንሶ ምድር ደምቀው የሚታዩ የስልጣኔ አሻራዎች የኢትዮጵያ የከፍታ ዘመን ህያዉ ምስክሮች ናቸዉ፡፡ ይሁን እንጂ ኢትዮጲያም እንደ አዉሮፓዉያኑ ሁሉ በታሪክ አጋጣሚ በተለይም በዘመነ መሳፍንት ባለፈችበት የእርስ በእርስ መቆራቆስና ሽኩቻ እንዲሁም ስልጣንን ከአፈሙዝ ለማግኘት በነበሩ ትንቅንቆች የተጠመዱት ገዥዎቿ ለህዝቡ የሚበጅ ስራ መስራት ተስኗቸው ኖረዋል፡፡ በስልጣኔ ማማ ላይ የነበረችው ሀገራችን የብርሀን ዘመኗን እያደር ደብዝዞ ቁልቁል ተንደርድራ በድህነትና ኋላቀርነት ተርታ ከተሰለፉ ሀገሮች ጎራ ተመድባለች፡፡
የደርግ ስርአት በህዝቦች ከባድ መስዋትነት ከስልጣኑ ከተወገደ በኋላ አዲስ ታሪክ በሚሊዮን እጆች በመጻፍ ላይ ይገኛል፡፡ አዲሱ ትዉልድ ባለፉት ሁለት አስርት አመታት የጎደፈ ገጽታውን፣ የደበዘዘ ማንነቱን የሚቀይሩ ስኬቶችን እያስመዘገበ ነው፡፡ በአራቱም አቅጣጫዎች የለዉጥ ደዉሎች መሰማት ላይ ናቸዉ፡፡ በዚህ የታሪክን ጠባሳ በሚሽር የታሪክ ምእራፍ ዉስጥ በርካታ ስራዎች ቢሰሩም የጉባ ተራሮች እምብርት ግን ዋናዉ የኢትዮጵያ ህዳሴ የስበት ማዕከል ሆኗል፡፡  
ከልጅ እስከ አዋቂ፤ ከተማሪው እስከ ከፍተኛው ባለሀብት፣ ከአርሶ አደሩ እስከ መንግስት ሰራተኛዉ፤ በሀገር ውስጥም በውጭም ያለውን ኢትዮጲያዊ ከዳር ዳር ያነቃነቀው የዘመናት ቁጭት የወለደው ታላቁ የኢትዮጲያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ በጉባ ተራሮች እቅፍ ውስጥ ይገኛል፡፡
ለሀገራችን ብሎም ለአፍሪካ የህዳሴ ዘመን ብርሃንነት የታጨችዉ ዳግማዊት ፍሎረንስ ‘ጉባ’ ታሪካዊ አደራዋን ከግብ ልታደርስ በኢትዮጲያ ልጆች ደጀንነት ፈጣን ጉዞዋን ቀጥላለች፡፡ በጉባ የምትባክን አንዳች ሽርፍራፊ ሰኮንድ የለችም፡፡ በጉባ ተራሮች ንዳድ ያልተንበረከኩት ጀግኖች ክንድ ዛሬም እንደ ጅማሮዉ 24 ሰዓት የድህነትን ተራራ መናድ እንደቀጠሉ ናቸዉ፡፡
ሁሉም በየአቅሙ ለ7ኛ ጊዜ በደረሰ የቦንድ ግዢ ጭምር የራሱን ደማቅ ታሪክ እያሳረፈ ያለው ግድባችን ከታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ የይቻላል መንፈስን የተላበስንበት ድንቅ የዘመን ስጦታ ነዉ፡፡ ገና ከድህነት እየተላቀቀች ባለች ሀገር፣ በህዝቦቿ እልህና ወኔ፣ ያለ ማንም የዉጭ ሀይል ድጋፍ ግንባታው ከ65 በመቶ በላይ መድረስ ችሏል፡፡ በመጪዉ ሰኔም ዉሃ መሰብሰብ ይጀምራል፡፡ ጉባም እንደ ፍሎረንስ ከተማ ሁሉ፤ የሀገራችንን የህዳሴ ዘመን ማብሰሪያ፤ የጨለማዉ ዘመን መባቻ ታሪካዊ ስፍራ የሚያደርጋትን የብርሀን ጉዞ ከዳር ልታደርስ ጉዞዋን ቀጥላለች፡፡ ከጉባ የሚፈነጥቀዉ ብርሀን የጨለማ ምሳሌ ሆኖ የሚጠቀሰዉን አህጉር ጽልመት ሊገፍ የቀሩት ጥቂት አመታት ብቻ ናቸው፡፡

No comments:

Post a Comment