EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Monday 19 February 2018

“ስልጣን መልቀቅም መምራት እንደሆነ አትርሳ” ኔልሰን ማንዴላ



(በመሐመድ ሽፋ መሐመድ)
በአህጉራችን አፍሪካ እንዳለመታደል ሆኖ በታሪክ አጋጣሚ ስልጣን የጨበጠ መሪ ስልጣኑን በሰላማዊ መንገድ ለሌሎች ለማስተላለፍ ያለው እድል እጅግ በጣም ጠባብ ነው፡፡ ለዚህም ነው በርካታ የአህጉራችን መሪዎች ስልጣን ላይ ከወጡ በኋላ የሚለቁት በመፈቅለ መንግስት አልያም በሸፍጥ ውርደትን ተከናንበው ዘብጥያ በመውረድ ነው፡፡
ይህ የሆነበት በርካታ ምክንያት ቢኖረውም በጥቅሉ ግን አብዛኛው የአህጉሪቱ መሪዎች በተፈጥሮ ሃብት ላይ የተንጠለጠለውን የየሃገራቸውን ሃብት ስልጣናቸውን ተገን በማድረግ እየዘረፉ መኖር ስለሚፈልጉ ነው። የበይ ተመልካች ያደረጉት ህዝቡ ደግሞ መጪው ይዞት የሚመጣውን በቅጡ ባይረዳውም እንኳን ከዛሬ ነገ ይሻላል በሚል ተስፋ መሪዎቹን አንድም በጦር ሃይሉ ስልጣን ግልበጣ፣ አልያም በታጠቁ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመጨረሻ እርምጃ ወይም ደግሞ ደም በሚያፋስስ የጎዳና ላይ አመፅ ያስወግዳቸዋል።
ያም ሆኖ ግን አዲሶቹም አዲስ ነገርን ሳይሆን ከቀደሙት መሪዎች ክፉ ክፉውን እየወረሱ፤ ስልጣንን  የህዝብና የአገር ችግር መፍቻ ሳይሆን የራሳቸው ማበልፀጊያ እያደረጉት አርጅተው እስኪሞቱ ከስልጣናቸው መንበር መውረድን አይሹትም። ይህ ፍላጎታቸው የህዝብ ቁጣ ሲነሳ እንኳ በሀይል እስከመደፍጠጥ የሚደርስ እርምጃ እንዲወስዱ ያደርጋቸዋል፡፡ በእንዲህ አይነት የስልጣን ጥማት አዙሪት ውስጥ የገቡ መሪዎች ለአፍሪካ ችግር መፍትሄን ሳይሆን ሌላ ችግርን እየከመሩባት ኖረዋል። አሁን አሁን ከሚታዩ ጥቂት ሰላማዊ የስልጣን ሽግግሮች ውጭ የአፍሪካን የዘመናት ታሪክ የሚወክለው ይሄኛው ገፅታ ነው።
የቀደሞ የደቡብ አፍረካ መሪ ኔልሰን ማንዴላ የአመራር ጥበብን ሲያስተምሩ ስልጣን መልቀቅም መምራት እንደሆነ አትርሳ ይላሉ። አንድ መሪ የመሪነት ጊዜውን ከጨረሰ በኋላ ቦታውን ለተከታዮቹ ማስረከብ እንዳለበት ነው ማንዴላ በዚህ ነጥባቸው የሚስተምሩት፡፡ ይህን መልዕክት ብዙዎቹ የአፍሪካ መሪዎች ከመስማት አልፈው እንዳልተገበሩት ቢታወቅም የእኛው ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ግን ስልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው በመልቀቅ ትልቅ ክብር የሚያስቸራቸውና ለሌሎች ምሳሌ የሚያሰኛቸውን ታላቅ ውሳኔ ወስነው ለማየት በቅተናል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ለሃገራቸው ሰላምና መረጋጋት ሲሉ በራሳቸው ውሳኔ ስልጣናቸውን ለማስረከብ ጥያቄ ማቅረባቸው በዘመናዊ ኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው መሪ የሚያደርጋቸው ብቻ ሳይሆን እንኳን የስልጣን ዘመናቸው ሳያልቅ ይቅርና፤ ካለቀም በኋላ ደርበው ደራርበው በስልጣን መቆየት ለሚሹ መሪዎች ሁሉ ትምህርትን የሚሰጥ ነው።
አቶ ኃይለማርያም ለአገራቸው የአቅማቸውን ያበረከቱ አያሌ ልማትና እድገት እንዲመዘገብ ብሎም የዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲሰፍን የታገሉ መሪ ናቸው። ከመምህርነት እስከ ሀገር መሪነት ድረስ ደረጃ በደረጃ ራሳቸውን እየገነቡ የመጡ የተማሩ መሪ መሆናቸው በራሱ አኩሪ ታሪካቸው ነው፡፡ ከታላቁ መሪያችን ጓድ መለስ ዜናዊ ያልተጠበቀ ህልፈት በኋላ በተፈጠረው አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ድርጅታቸውና ሕዝብ የሰጣቸውን አደራ ተቀብለው የተጀመረውን የለውጥ ሂደት ማስቀጠል መቻላቸውን ታሪክ የማይዘነጋው ሀቅ ነው፡፡
አቶ ኃይለማርያም ሀገራችን የጀመረቻቸውን ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች በእለት ተዕለት ክትትል በመምራት አንዳንዶቹን ለፍፃሜ ሌሎቹን ደግሞ በስኬት መስመር እንዲቀጥሉ ያስቻሉ ናቸው። የባቡር መንገድ ፕሮጀክቶችንና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ስኬቶችን ለመረመረ አቶ ኃይለማርያም የሀገር መሪ ብቻ ሳይሆኑ ዘመኑ ያፈራቸው ምርጥ ኢንጂነር መሆናቸውን ለመመስከር አያንገራግርም።
እርሳቸው የሚመሩት መንግስት ድህነትን ድል ለማድረግ ትምህርትና ስልጠና ያለውን ወሳኝነት በመረዳት ለሰብዓዊ ሃብት ልማት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ተረባርቧል፡፡ ፋይናንስ ለልማት ያለውን ቁልፍ ፋይዳ ተገንዝበው ለህዝባቸው በተለይም ለወጣትና ለሴቶች ከፍተኛ የብድር ገንዘብ በአነስተኛ ወለድ እንዲቀርብ አድርገዋል፡፡ ለወጣቶች የስብዕና ግንባታና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት መስራት የቅድሚያ አጀንዳቸውም ነበር።
የመልካም አስተዳደር እጦት የሀገራችን ህዝቦች ቀዳሚ ችግር መሆኑ በመንግስትና በድርጅት ደረጃ ተለይቶ ከወጣ በኋላም ለችግሩ እልባት ለመስጠት እንደ ሀገር መሪ የሚያስመሰግኗቸውን ተግባራት ፈፅመዋል። ችግሩ በዝርዝር ሳይንሳዊ ጥናት እንዲታወቅና ለህዝብ ይፋ እንዲሆን ከማድረግ ጀምሮ የማሻሻያ ሪፎርሞችን ያስተገበሩ ናቸው። የአመራር በጥቅም መተሳሰር እንዲሁም በዘመድና በጋብቻ መሥራት እንዳለ በግልፅ በማሳወቅ ህዝቡ ከመንግስት ጎን ቆሞ እንዲታገለው አነሳስተዋል። በስራቸው ያሉ አመራሮችንም "እዚህ ብዙ እናወራልን እንጂ ስንወጣ የራሳችንን ኔትዎርክ እንጠብቃለን" በማለት ፊት ለፊት የወቀሱ ቅን የህዝብ ልጅ ናቸው፡፡
የልማት ባንክን አሰራር ሪፎርም በማድረግ በልማት ሰበብ ሲመዘበር የነበረውን የአገር ሃብት ማዳናቸው፣ ለዘመናት የብሶት ምንጭ የሆነው የአዲስ አበባ ውሃ ችግር በዘላቂ መንገድ ለመፍታት ቁርጠኛ አመራር መስጠታቸው፣ በዜግነትና ኢሚግሬሽን ተቋም የነበረን የጥቅም ሰንሰለት በጣጥሰው በመጣል ቀልጣፋ አሰራር እንዲሰፍን ማስቻላቸው፣ ስለ ህገወጥ ስደት ልዩ ትኩረት ሰጥተው ምክር ቤት እንዲቋቋም ማድረጋቸው፣ የኢትዮጵያ አምባሳደሮችን ሰብስብው ምን ያህል ኢንቨስተር ማምጣት እንዳለባቸውና እንዳመጡ መሞገታቸውና ሌሎች ብዙ ስኬቶቻቸውን በማንሳት የመልካም አስተዳደር ችግርን ለመቅረፍና ተጠያቂነትን ለማስፈን የነበራቸውን ቁርጠኝነትና ተጨባጭ ስኬት መመስከር ይቻላል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ መምህራንን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ የመንግስት ሠራተኞች ቤትና የመስሪያ መሬት እንዲያገኙ አድርገዋል፤ የህዝብ ምክር ቤቶች የመንግስት አካላት ሥራ አፈጻፀምን እየገመገሙ የማስተካከያ አቅጣጫን እንዲያስቀምጡ ደግፈዋል። የመንግሥት ዋና ኦዲተር ጥርስ ያወጣው በማን ጊዜ ነው ቢባል በእርሳቸው የአመራር ዘመን ስለመሆኑ ማንም ይመሰክራል፡፡
አቶ ኃይለማርያም በሀገራችን ከፍተኛውን የአስፈፃሚ ስልጣን ከያዙ ጀምሮ ሀገራችን በውጭ ግንኙነትና ዴፕሎማሲ ረገድ ያስመዘገበቻቸውን ስኬቶች በማስቀጠል ረገድም ታሪካዊ ሚናቸውን ተወጥተዋል። ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀዳሚ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መዳረሻ በማድረግ ለቡዙሃን ኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል በመፍጠር ተስፋቸውን አለምልመዋል። በአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበርነታቸው የአፍሪካ ህብረት 2063 አጀንዳ ውጤታማ ሆኖ እንዲቀረጽ ያስቻሉ፤ የህብረቱ 50ኛ ዓመት ወርቅ ኢዩበልዩ በዓል ለአፍሪካ ተስፋ በሠነቀ መልኩ እንዲከበር ያደረጉ ናቸው። በአባይ ወንዝ አጠቃቀም የተነሳ ከግብጽ ጋር ያለን የሻከረ ግንኙነት በመሰረታዊነት እንዲቀየር፣ ጽንፍ የያዙ የግብጽ ፖለቲከኞችን በበሰለ ዲፕሎማሲ አደብ ያስገዙና የህዳሴው ግድብ ግንባታ ለአንዲት ደቂቃ እንኳን ሳይቋረጥ እንዲቀጥል በሳል አመራር የሰጡ ጀግና ናቸው።
የአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ አርዓያነት ለስልጣን ባላቸው አቢዮታዊ አመለካከት እና ለሃገራቸው እድገት በተጫወቱት ትልቅ የመሪነት ሚና ብቻ ሳይሆን በአህጉራችን ባልተለመደ መልኩ በስራ ዘመናቸው እራሳቸውና ባለቤታቸውንም ጭምር ከሙስናና ብልሹ ተግባሮች በማራቃቸው ጭምር የሚገለፅ ነው።
በአጠቃላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ስልጣን መልቀቅም መምራት እንደሆነ አትርሳ የሚለውን የማንዴላ አመራር ጥበብን ተግባራዊ በማድረግ በኢትዮጵያ የመንግስታት ታሪክ ውስጥ የፖለቲካ ጨዋታውን ቀያሪ በመሆን ደማቅ አስተዋፆ ያደረጉ የኢትዮጵያ ልጅ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ በይፋ ለወከለው ህዝብ አሳውቆ ሥልጣን መልቀቅ በራሱ ታሪክ ነውና ታሪክ ሲዘክራቸው የሚኖር ታላቅ መሪ ሆነዋል፡፡

2 comments:

  1. keep it up mama.....it is good looking!!!!!
    we have agreat respect to our hero pm hailemariam desalgn

    ReplyDelete