EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Saturday 18 November 2017

ያልተንበረከኩት

(በሚሚ ታደሰ)
ያልተንበረከኩት
ስንቶች ተኮላሽተዉ ከአረንቋዉ ዘቀጡ፤
ስንቶች ተሸንፈዉ ከጎዳና ወጡ፤
ጥቂቶች ቆራጦች ያልተንበረከክነዉ፤
ነገ እልፍ እንሆናለን ታሪክ ምስክር ነዉ፡፡

የኢትዮጲያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) ነሐሴ 26 ቀን 1967 ዓ.ም ተመሰረተ፡፡ ፓርቲዉ በወቅቱ የነበረዉን የመብት እና የእኩልነት ጥያቄን ለመመለስ መደራጀቱ በተለይም በአብዛኛዉ በወጣቱና በተራማጅ ሀይሉ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረዉ አድርጎታል፡፡
የፓርቲው አመራሮች በተለይም በከተሞችና በምሁሩ ዘንድ ባገኙት ህዝባዊ ተቀባይነት እና ድጋፍ የልብ ልብ ተሰምቷቸው ደርግን በአጭር ጊዜ ለዛውም በከተማ አመፅና በመፈንቅለ መንግስት ማስወገድ ይቻላል የሚል ድምዳሜ ላይ ደረሱ፡፡ የተወሰኑ ልዩነት ያላቸውን አመራሮችም አፈንጋጭ እያሉ በመፈረጅና በማፈን በአቋራጭ ደርግን ለመጣል የያዙትን እቅድ ለማሳካት ተረባረቡ፡፡
ኋላ ግን ደርግና ደርግን በሂስና ምክር ማስተካከል ይቻላል በሚል እምነት ከጎኑ የተሰለፉ የወቅቱ ፓርቲዎች በወሰዱት የጭፍጨፋ እርምጃ ኢህአፓ እጅጉን ተዳከመ፡፡ ኢህአፓ በአጉል ጀብደኝነት እራሱን በራሱ ሲያጠፋ ያዩ የድርጅቱ አባላት ህጸጾችን በማረም ለህዝቡ ትክክለኛ መብት በተጠናከረ የድርጅት እንቅስቃሴ እርማት ወስደን መንቀሳቀሰ ይኖርብናል ቢሉም ቀስ በቀስ በአመራሩ ሃይል እየተወገዱ ሄዱ፡፡
በኢህአፓ መሽመድመድ ዉስጡ የቆሰለዉ ሀይል ቀጣዩ ስልታችን የሚለዉ የዉስጡ ጥያቄ እያሳሰበዉ፤ የመጣበትን መንገድ እያሰበ ሳለ ሌሎች አዳዲስ ሀይሎች ከዉስጡ ተወለዱ፡፡ ኢህአፓ ከእንግዲህ አብቅቶለታል፤ በዴሞክራሲያዊ ትግል የጠራ መስመር የጨበጠ ሌላ ድርጅት መመስረት ያስፈልጋል ያሉና ደርግ ሊወድቅ የሚችለው በተራዘመ የገጠር የትጥቅ ትግል ብቻ ነው ብለው ያመኑ ጓዶች ለሌላ አዲስ ትግል ራሳቸውን አዘጋጁ፡፡
ያም ሆኖ መንገዱ የተቃና አልሆነላቸውም፡፡ ቁጥራቸው እየተመናመነ ፈተናም እየፀናባቸው ሄደ፡፡ ከላይ የቀረበዉ ስንኝ በየመንገዱ እየካዱና እየተንጠባጠቡ ለወጡ አባላት እና ያኔ በህዝቡ ውስጥ ያሉ መሰረታዊ የእኩልነት እና የመብት ጥያቄዎችን ከግብ እናደርሳለን ላሉ ተራማጅ የህዝብ ልጆች የተቋጠረ ታሪካዊ ስንኝ ነዉ፡፡
ክህደት፤ ተስፋ መቁረጥ እና ስደት በአብዛኞች አእምሮ ዉስጥ እንደ አማራጭ በተቀመጠበት በዛ ከባድ ወቅት ሀቀኞቹ የኢትዮጲያ ልጆች፤ የኢህአፓ መክሰም የለዉጥ ጭላንጭላቸዉን ፍጹም ሳያደበዝዘዉ፤ ለነበሩ ተግዳሮቶች ሳይንበረከኩ፤ መስራች ጉባኤያቸዉን በህዳር 7 1973.ዓ.ም አካሄዱ፡፡ ለተከታታይ ቀናት በቀጠለዉ ዉይይትም በበርካታ ጉዳዮች ስምምነት ላይ ተደርሶ ህዳር 11 ቀን 1973 ዓ.ም በተክራርዋ የያኔው የኢትዮጲያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢህዴን) የአሁኑ የብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ተወለደ፡፡
ኢህዴን/ብአዴን ይበልጥ ተደራጅቶ የትጥቅ ትግሉን ቀጠለ፡፡ ከጭቁን የአማራ ህዝብ አብራክ የወጡ ጥቂቶች ነገር ግን ቆራጥ ታጋዮችን ይዞ አምባገነኑን ደርግ የመፋለሙን ሂደት አፋፋመዉ፡፡ ነጻ በወጡ አካባቢዎች ህዝቡ እራሱን በራሱ ያስተዳድር እና የመሬት ክፍፍልም ያደርግ ጀመረ፡፡
ኢህዴን/ብአዴን በሀገራችን ዉስጥ ያሉ በርካታ ብሄር ብሄረሰብ ተወላጆችን አቅፎ አምባገነኑን ስርአት እስከወዲያኛዉ ገርስሶ ለመጣል ሰፊ ትግል አካሂዷል፡፡ በየአካባቢዉ ያለዉን ህዝብ በማንቃትና በማደራጀት ለትጥቅ ትግሉ እንዲሰለፍ ማድረግ ችሏል፡፡ ከመላ የኢትዮጵያ ህዝቦች ትግል ጋር ተዳምሮም አምባገነኑን ስርዓት ገርስሷል፡፡
እነሆ ዛሬ ሰአታት ለቀናት፤ ቀናት ለወራት ቦታቸዉን እየለቀቁ መንጎዳቸዉን ቀጥለዋል፤ ተራማጁ ብአዴንም በዘመን ቀመር ውስጥ በርካታ ፈተናዎችን በመጋፈጥ ወርቃማ የድል ችቦዎችን ለኩሷል፡፡ ብአዴን በክልሉ ብሎም በመላዉ ኢትዮጲያ ባለፉት 26 አመታት በተለይም ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ለተመዘገቡ ሁሉን አቀፍ፤ተከታታይ እና አንጸባራቂ ድሎች የበኩሉን የአመራርነት ሚና አበርክቷል፡፡
በብአዴን በሚመራው የአማራ ክልል ባለፉት 26 አመታት የአማራ ዴምክራሲያዊ ብሄርተኝነት እንዲያብብ እና እንዲዳብር ዘርፈ ብዙ ተግባራት ተከናዉነዋል፡፡ የዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት እሳቤ ተግባራዊ ሲደረግ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት፤ እንዲሁም የዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት አስተሳሰብ እና ተግባራዊ የአፈጻጸም ስኬቶችን አሟልቶ በመያዝ፤ በህዝቦቿ መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተች፤ ያደገችና ህዝቦቿ በፍትሀዊነት ተጠቃሚ የሚሆኑባትን አገር ለመገንባት ብአዴን ዛሬም እንደ ትላንቱ በመረባረብ ላይ ይገኛል፡፡ የዘንድሮዉን የምስረታ በአል ሲያከብር እነዚህን ድሎቹን ማስቀጠልና ወቅቱ የሚጠይቀውን አመራር ለመስጠር የሚችልበትን ቁመና በመላበስ መሆን አለበት እላለሁ፡፡

መልካም የምስረታ በዓል!!

No comments:

Post a Comment