EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Monday 27 November 2017

አባይን የመጠቀም መብታችን

(በስንታየሁ ግርማ)
ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝ የሚሰጣቸውን ትሩፋቶች የመጠቀም ህጋዊና ተፈጥሯዊ መብቶቿ የተጠበቁ ናቸው። ይሁንና አንዳንዶች ይህ መብት ለግብፅ ብቻ የተሰጠ ይመስላቸዋል። ምንም እንኳን አሁን እየተሻሻለ የመጣ የግንዛቤ ደረጃ ቢኖርም በርካታ ግብፃውያን አባይን በተመለከተ ያላቸው መረጃና ከዚህ ተነስተው የሚወስዱት አቋም የተዛባ ነው። የአባይ/ናይል ወንዝ የተፈጠረው ለእነሱ ብቻ እንደሆነ፣ በወንዙ ውሃ በብቸኝነት መጠቀም ታሪካዊና የማይገሰስ መብታቸው እንደሆነ እና የተፋሰሱ የላይኛው ሀገራት የወንዙን ውሃ መጠቀም እንደማይችሉ አድርገው የማየት አዝማሚያ ይታይባቸዋል። በእኛ በኢትዮጵያውያን ዘንድም የአባይ ወንዝን በመጠቀም ረገድ ፅኑ ፍላጎትና ጠንካራ አቋም ቢኖርም በህግና በመርህ ደረጃ ያሉንን አንፃራዊ ብልጫዎች ላይ በቂ ግንዛቤ የለም። በመሆኑም ከአለም አቀፍ ህግና ተቀባይነት ካላቸው መርሆዎች አኳያ ወንዙን የመጠቀም መብታችን ምን ይመስላል የሚለውን ማየት ተገቢ ይሆናል።

አንዳንድ ግብፃውያን የቅኝ ግዛት ጊዜ ውሎችን በመጥቀስ በአባይ/ናይል አጠቃቀም ላይ አለም አቀፍ ህግ የሚደግፈውና መብት የሚያጎናፅፈው እኛን ነው ይላሉ። የአባይ/ናይል ወንዝን በተመለከተ የመጀመሪያው ስምምነት የተካሄደው እ.ኤ.አ በ1891 ነበር። በዚህ ስምምነት መሠረት ጣሊያን በአትባራ/ተከዜ ወንዝ ላይ ግድብ ላለመስራት ከእንግሊዝ ጋር እንደተስማማች የሚያትቱ አሉ። ፕሮፌሠር አሊ አብደላ አሊ ግን ሥምምነቱ በግልፅ ቋንቋ ያልተቀመጠ ነው ይሉታል።
ሁለተኛው ስምምነት እ.ኤ.አ በ1902 በእንግሊዝ፣ በጣሊያን እና በኢትዮጵያው መሪ አፄ ሚኒሊክ መካከል ተፈርሟል የሚባለው ስምምነት ነው። በዚህ ስምምነት መሠረት አፄ ሚኒሊክ የአባይን ወንዝ እንዳይፈስ ላለማስቆም መስማማታቸውን የሚያስቀምጡ አሉ። ይህ ስምምነት በወቅቱ በእንግሊዝ መንግስት የዘውድ ም/ቤት ስላልፀደቀ ተቀባይነት የለውም የሚሉ አሉ። የዚህ ስምምነት የእንግሊዝኛ እና የአማርኛ ፍቺዎች የተለያዩ በመሆናቸው ኢትዮጵያም እንዳላፀደቀችው ፕሮፌሠር አሊ ተናግረዋ።
በሌላ በኩል ግብፃውያን የ1929 እና የ1959 ስምምነቶች በአባይ/ናይል ወንዝ ላይ በብቸኝነት ለመጠቀም ታሪካዊ መብት ያስገኙላቸው እንደሆኑ ይከራከራሉ። በእነዚህ ስምምነቶች መሠረት፡-
·         ግብፅ እና ሱዳን አንድ ጠብታ ውሃ እንኳን ሳያስቀሩ ሙሉ በሙሉ በራሳቸው ተከፋፍለውታል።
·         ሌላ ይገባኛል የሚል ሀገር ከመጣም በእነሱ ፈቃደኝነት ላይ ተመስርቶ ከሁለቱ ሀገራት እኩል እንዲቀነስ ተስማምተዋል።
·         በላይኛው ተፋሰስ ሀገራት በአባይ/ናይል ወንዝ ላይ የሚሠራን ግድብ በተመለከተ ግብፅ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ተሰጥቷታል።
·         ሁለቱ ሀገራት በሌሎች ሀገሮች በወንዙ ላይ የሚሠሩ ስራዎችን  ለመከታተል የሚችሉበት የቴክኒክ ቡድን ለማቋቋም ተስማምተዋል።
እነዚህን ስምምነቶችና የሚያካትቷቸውን ሃሳቦች ከአለም አቀፍ ህግ እና ከመርህ አንፃር ያላቸውን ተቀባይነት ማየት ተገቢ ነው። እዚህ ላይ ግን ከሁሉ አስቀድሞ ግብፅ እና ሱዳንም ቢሆኑ በሁለቱ ስምምነቶች እኩል ተጠቃሚ ናቸው ብሎ መውሰድ የሚቻል እንዳልሆነ መረዳት ያስፈልጋል። በ1929 ስምምነት ግብፅ ሱዳንን አላማከረችም። ምክንያቱም በወቅቱ ሱዳን የግብፅ አንድ የግዛት አካል ተደርጋ ስለምትወሰድ ነበር። በ1959 ስምምነት ደግሞ የሱዳን የውሃ ባለሙያዎች አስተያየት በተገቢው መንገድ ግምት ውስጥ ሳይገባ የሱዳን የወቅቱ ባለስልጣናት ከግብፅ ሊመጣ የሚችልን ጫና በመስጋት ብቻ እንደፈረሙት ፕሮፌሰር አሊ ታሪክን በመጥቀስ አብራርተዋል።
እነዚህ ሁለት ስምምነቶች የታችኛው የተፋሰስ ሀገራት በተለይም የ86 በመቶ ውሃ ምንጭ የሆነችውን ኢትዮጵያ ሀሳብ ያላካተቱና የስምምነቱም አካል ያላደረጉ ናቸው። አንድ ስምምነት አለም አቀፍ ህግ ሊሆን የሚችለው እና ተቀባይነት የሚያገኘው ደግሞ ስምምነቱን በፈረሙት እና ባፀደቁት አካላት መካካል ብቻ ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያም ሆነች ሌሎች የተፋሰሱ ሀገራት ባልተካተቱባቸው በሁለቱ ስምምነቶች የመገዛት ግዴታ የለባቸውም።
ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን በተመለከተ በአሁኑ ሰዓት ተቀባይነት ያላቸው መርሆዎች እኩል ተጠቃሚነት እና ከፍተኛ ጉዳት ያለማድረስ የሚሉት መርሆዎች ናቸው። በእነዚህ መመዘኛዎች መሠረት የ1929 እና የ1959 ስምምነት ከ11 የተፋሰሱ ሀገራት ዘጠኙን ያገለሉ በመሆናቸው እና ከላይ የተጠቀሱትን መርሆዎች የሚጥሱ በመሆናቸው ወደ አለም አቀፍ ፍ/ቤት ቢኬድ እንኳን ተቀባይነት አይኖራቸውም። ስምምነቶቹ በይዞታቸው የእኩል ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሳይሆኑ የሚያገልሉ (discriminatory) በመሆናቸው በአለም አቀፍ ህግ አይደገፉም። ለነገሩ ጉዳዩን ወደ ፍ/ቤት ሄዶ ለመከራከር ቢፈለግም ቅድሚያ ከኢትዮጵያ ጋር መስማማትንም ግድ ይላል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለመጓጓዣነት የማይውሉ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን አጠቃቀም በተመለከተ በግንቦት 1997 (እ.ኤ.አ) ባወጣው ኮንቬሽን መሠረት ሁሉም የተፋሰሱ ሀገርት ወንዙን በሚጠቀሙበት ጊዜ የእኩል/ፍትሃዊ/ሚዛናዊ አጠቃቀም መርህን በዋነኝነት መከተል እንዳለባቸው ያስቀምጣል። ይህን መርህ አንዳንዶች ለሁሉም ሀገራት እኩል ማከፋፈል ነው በማለት ይተረጉሙታል። ይህ ግን በአብዛኛው ተቀባይነት የለውም። በኮንቬንሽኑ መሠረት የእኩል/ፍትሃዊ/ሚዛናዊ መርህ የሚከተሉትን ጉዳዮች የሚያካትት ነው።
1)   የጂኦግራፊ፣ የሃይድሮ ግራፊክ፣ የሃይድሮ ሎጅክ፣ የአርኪዮሎጂክ እና ሌሎች የተፈጥሮ ሁኔታ መመዘኛዎች
2)   በተፋሰሱ የሚገኙ ሀገራት ያላቸው የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ፍላጎት፣
3)   አንድ ሀገር ውሃውን ሲጠቀም በሌላኛው ተፋሰስ ሀገር ላይ ያለው ተፅዕኖ፣
4)   በጥቅም ላይ የዋለ እና ገና ያልተጠቀሙበት እውቅ የውሃ አቅም፣
5)   ውሃውን ለመጠበቅ፣ ለመከላከል፣ ለማበልፀግ የሚያደርገው አስተዋጾ እና ለዚህ የሚውለው ወጪ፣
6)   አማራጭ የውሃ ምንጮችን።
በዚህ ኮንቬንስን አንቀፅ 6 መሠረት ሀገራት የውሃ ሃብታቸውን መጠቀም ሲፈልጉ ከላይ የተጠቀሱትን ጉዳዮች ግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚገባቸው ተቀምጧል። በእነዚህ መመዘኛዎች ላይ ያልተመሰረተ የድንበር ተሻጋሪ ወንዝ አጠቃቀም በድርጅቱ ተቀባይነት አይኖረውም። ስለሆነም በዚህ ኮንቬንሽንም የታችኞቹ የተፋሰስ ሀገራት የብቻ ተጠቃሚነት ፍላጎት የሚደገፍ አይደለም። ይልቁንም ለእነዚህ መመዘኛዎች የሚቀርበው የቅኝ ግዛት ወቅት ውሎች ሳይሆኑ የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት መሆኑን ነው የሚያረጋግጠው።
ስለሆነም ለግብፅ እና ለሱዳን ዘላቂ ጥቅም ተመራጭ የሚሆነው መንገድ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነቱን መፈረም ነው። ለነገሩ ስምምነቱን 2/3ኛው ነፃ አባል ሀገራት ካፀደቁት አለም አቀፍ ተቀባይነት እና አስገዳጅነት ያለው ህግ ይሆናል። ለመጀመሪያም ጊዜም ናይልን በተመለከተ አለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው ህግ ይሆናል። ስምምነቱን ኢትዮጵያ አጽድቃዋለች።
በ1997 የተመድ ኮንቬክሽን መሠረት ከእኩል ተጠቃሚነት በተጨማሪ የከፋ ጉዳት ያለመድረስ መርህ ሌላኛው መመዘኛ ነው። የህዳሴውን ግድብ በተመለከተ በግብፅ ላይ ትርጉም ያለው ጉዳት እንደማይደርስ በተደጋጋሚ ኢትዮጵያ አስቀምጣለች። ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን በጋራ ያቋቋሙት የሦስትዮሽ የቴክኒክ ኮሚቴ የህዳሴው ግድብ አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እና በታችኛው የተፋሰስ ሀገራት የጎላ ጉዳት እንደማያደርስ አስታውቋል።
እንደውም የግድቡ ስራ ሲጀመር ታላቁ መሪ ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊ ግድቡ የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች ካነሱ በኋላ ፍትሃዊ አጠቃቀም ቢሰፍን ኖሮ ከግድቡ ወጪ ሱዳን 20 በመቶ ግብፅ 30 በመቶ ሊሸፍኑ ይገባ ነበር ብለዋል። ባለሙያዎች እንደሚገልፁት በኢትዮጵያ የሚሠራ ግድብ ትነትን በመቀነስ ተጨማሪ ውሃ ያስገኛል። በኢትዮጵያ የሚሰራ የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ የታችኛውን ተፋሰስ ሀገራት ከጎርፍ እና በደለል ከመሞላት ይከላከላል። የተመጠነ የውሃ ፍሠት አመቱን ሙሉ እንዲኖር ያስችላል። ለተፋሰሱ ሀገራትም በተመጣጣኝ ዋጋ የሃይል አቅርቦት ያስገኝላቸዋል። እንደውም አንዳንድ የዘርፉ ባለሙያዎች የአባይን ወንዝ በዘላቂነት ለመጠቀም ውሃው የሚከማችበትን እንደ አስዋን ግድብ ከፍተኛ ትነት ካለበት ግብፅ እና ሱዳን ይልቅ ወደ ቀዝቃዛው የኢትዮጵያ ክፍል የማሸጋገር ስትራቴጂን መከተል ይገባል ሲሉ ይመክራሉ።
ይህ እንዳለ ሆኖ የከፋ ጉዳት አለማድረስ የሚለው መርህ ለእኩል ተጠቃሚነት መርህ ተገዢ እንደሆነ አለም አቀፍ ልምድ ያሣያል። በዳንቡ ወንዝ አጠቃቀም ላይ ውዝግብ በመነሳቱ ሀንጋሪ እና ስሎባኪያ ጉዳዩን ለአለም አቀፍ ፍ/ቤት አቅርበውት ነበር። ፍ/ቤቱም የእኩል ተጠቃሚነት መርህን ሁለት ጊዜያት ያክል በመጥቀስ ብይን ሰጥቷል። ነገር ግን ጉዳት አለማድረስ መርህን ፍ/ቤቱ አልተጠቀመበትም። ይህ የሚያሳየው ቅድሚያ የእኩል ተጠቃሚነት መርህ፣ በመቀጠል ደግሞ የከፋ ጉዳት ያለመድረስ መርህ የሚታዩ መሆኑን ነው።
ሌላው በአንዳንድ ግብፃውያን የሚቀርበው የመከራከሪያ  ነጥብ 55.5 ቢሊዮን ኪዪብ ሊትር ውሃ የመጠቀም ታሪካዊ መብት የሚሰጣቸው ስምምነት ተለምዷዊ አለም አቀፍ ህግ ሆኗል የሚል ነው። ይሁንና አንድ ስምምነት ተቀባይነት የሚያገኘውና በአለም አቀፍ ህግም ተቀባይነት የሚኖረው ተቃዋሚ ወገን ሳይኖር ሲቀር ነው። ኢትዮጵያ ግን በአባይ ወንዝ ላይ የመጠቀም መብት እንዳላት ለግብፅ እና ለሌሎችም በየጊዜው ከማሳወቋም በላይ ቀኝ ገዢዎች እና ግብፅ ኢትዮጵያን በማግለል የተዋዋሏቸውን ስምምነቶች እንደማትቀበላቸው በተደጋጋሚ ለሀገራቱ እና ለአለም አቀፍ ተቋማት (ለሊግ ኦፍ ኔሽን እና ለተ.መ.ድ) በፅሁፍ ስታስታውቅ ቆይታለች። በተለይም የአፄ ሚኒሊክ እና የአፄ ሃይለሥላሴ ተቋውሞዎች በፅሁፍ ጭምር ሰፍረው ይገኛሉ። ስለዚህ ታሪካዊ መብት እና ልማዳዊ ህግ የሚለው ኢትዮጵያ ተቋውሞዋን የገለፀችበት ስለሆነ በአለም አቀፍ ህግ ተቀባይነት አይኖረውም።

ሲጠቃለል የአባይን ወንዝ በተመለከተ ለኤሌክትሪክም ሆነ ለሌላ አገልግሎት ማዋልን አለም አቀፍ ህጉ ኢትዮጵያን የሚደግፍ እንጂ የሚከለክል አይደለም። አንዳንድ ግብፃውያን የ1929 እና የ1959 ስምምነትን በመጥቀስ በአለም አቀፍ ህግ ተቀባይነት ያለው መብት አለን የሚል ድምዳሜ ላይ የሚደርሱባቸው ስምምነቶችም ሌሎችን ያገለሉ እና የእኩል/ፍትሃዊ/ሚዛናዊ አጠቃቀም መርህን የሚጥሱ በመሆናቸው ተቀባይነት እንደሌላቸው መገንዘብ ይቻላል። በመሆኑም ለሀገራቱ የሚሻለው ስልት ነባራዊ እውነታውን መቀበል እና በጋራ መልማት ነው።

No comments:

Post a Comment