EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Thursday 5 October 2017

የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል…

(በኤስሮም ፍቅሩ)

ከአዲስ አበባ በደቡብ ምስራቅ 45 . ርቀት ላይ በምትገኘው በውቢቷ ቢሸፍቱ ከተማ ላይ የመስቀል በአል ካለፈ በኋላ በሚመጣው የመጀመሪያው እሁድ አንድ ክብረ በአል ላይ ለመታደም ከተለያዩ አካባቢዎች ህዝብ እንደ ጉድ ይተማል፡፡ የቢሸፍቱ ከተማ በመስከረም አደይ ተውባ ምድርና ሰማዩዋን የእርጥብ ቄጤማ ሽታ ያውደዋል፡፡ የሀገር ሽማግሌ፣ አባ ገዳዎች የበአሉ ፊሽካ ተነፍቶ ኦያ ማሬዎ እያሉ ፈጣሪያቸውን እያመሰገኑ በቢሸፍቱ ከተማ ላይ በኩራት ለመታየት ይጓጓሉ፡፡

ህፃናት በአሉ ከመድረሱ በፊት የተገዛላቸውን የበአል ልብስ ለብሰው በእናትና አባታቸው ትከሻ ላይ እሽኮኮ ተደርገው የሆራ ሀይቅን አማትረው እያዩ ለመቦረቅ ቀናትን እየቆጠሩ ይጠብቁታል፡፡ በክረምቱ ጊዜ ከትምህርት ገበታ ላይ ተነስተው የእረፍት ጊዜያቸውን ለማሳለፍ ወደ ቀያቸው የተመለሱ የዩንቨርስቲ ተማሪዎች ወደ ዩንቨርስቲ መመለሻ ጊዜያቸው ሲደርስ ለሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻቸውና እህቶታቸው የበአሉ አንድምታ ምን ይመስል እንደነበር ቀርፀው ለማሳየት  በታላቅ ጉጉት ይጠብቁታል፡፡ ጎረምሶችና ኮረዶችም ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ የሚለውን አባባል ለእሬቻ ያልሆነ ቀሚስ በሚለው ቀይረው እሬቻ የሚለግሳቸውን የትዳር ስጦታ ለመቀበል በተለያዩ አልባሳት አሸብርቀው ይዘጋጃሉ፡፡ እናቶችም ፀጉራቻውን በለጋ ቂቤ አስውበው ሀገርን ሰላም አድርጎ፣ ወንዝ እና ከብቱን ባርኮ፣ ፀደይን ያሳያቸውን አምላካቸውን ለማመስገን የሆራ ሀይቅ ላይ የሚደፉትን ቅቤ አቅልጠው በእንቅብ ሞልተዋል፡፡

ምን አለፋችሁ፣ እሬቻ የሁሉም ኦሮሞዎች፣ ሁሉም ኦሮሞዎች ሁሉ ነገራቸውን የሚሰጡት የተከበረ በዓል ነው፡፡

ዘንድሮም የቅዳሜ ለሊት አልፎ እሁድ መነጋጋት ሲጀምር በታላቅ ጉጉት ሲጠበቅ የነበረው ኢሬቻን ለመታደም ከማለዳው ጀምሮ በርካቶች ወደ ሀይቁ መትመም ጀመሩ፡፡ ቢሾፍቱ አየሯ በቂቤ፤ በቡና፤ በእጣንና በሽቶ መአዛ ታፍና ልትፈነዳ ደርሳለች፡፡ በተለምዶ ሚሴንሳ ተብለው የሚጠሩት ምእመናን የበአሉ ተካፋዮች እርጥብ ሳር ይዘው ፈጣሪያቸውን እያመሰገኑ ˝ቢይ ቴኛ ነጋ ሀታቱ˝ (ሀገር ሰላም ይሁን) ˝ጃለል ኑራቲ ሃደንገላኡ˝  (ፍቅር ይፍሰስብን) እያሉ ከወዲያ ወዲህ ይዘዋወራሉ፡፡

የኦሮሞ ህዝብ እምነቱን አክባሪ፤ ጨዋ እና ምስጉን  ህዝብ መሆኑን ባስመሰከረበት በዘንድሮው የኢሬቻ ክብረ በአል ላይ 5 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ስርዓቱን ታድሟል፡፡ በአሉ ያለ ምንም የፀጥታ ችግር መከባበር በታየበት ሁኔታ ሃይማኖታዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ ተካሂዷል፡፡ የዛሬ ዓመት ፀረ ሰላም ሃይሎች ተገቢ ባልሆነ ሁኔታ የበአሉን ድባብ ወዳልተፈለገ ሁኔታ አስቀይረው የሰው ህይወት ዋጋ የተከፈለበት ጊዜ እንዳይደገም ለማድረግ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎችና ወጣቶች የነበራቸው ሚና ከፍተኛ ነበር፡፡ ህዝባዊ ክብረ በአሎችን ከታሰበላቸው አላማ ውጪ እንዲውሉ ማድረግ ከፀፀት ውጪ ትርፍ እንደሌለው ቀድሞውንም የተረዳው ጨዋው የኦሮሞ ህዝብ በአሉን አክብሮ ለቀጣይ ዓመት ሰላም ያድርሰን ተባብሎ ተመራርቆ ተሸኛኝቷል፡፡

በፌስቡክ መሽጎ የተፈነከተ እየፈለጋችሁ ፎቶ ላኩልን ሲል የነበረው እሳት ቆስቋሹ ፅንፈኛ ዲያስፖራም በሌሎች ደም የፖለቲካ አላማውን ለማራመድ የነበረው ሀሳቡ ሳይሰምር በአሉ በሰላም ተጠናቋል፡፡ የዘንድሮ የኢሬቻ በአል ለአምናው ሁከትና ግርግር ታላቅ ምላሽን የሰጠ፤ ከፀረ ሰላም  ሃይሎች ሁከት እና ድርጊት ትርፍ እንደማይገኝ ያሳየ፤ ህዝቡን በራሱ ጉዳይ ላይ ባለቤት ማድረግ ከተቻለ በመሰል ዝግጅቶች ብቻ ሳይሆን በሌሎች የልማት ስራዎችም ስኬታማ መሆን እንደሚቻል አስተምሮ ያለፈ ክብረ በአል ሆኗል፡፡

በተጨማሪም ሀገራችን ያሳለፈችው የጥልቅ ተሀድሶ ሂደት ችግሮችንና አለመግባባቶችን የቀረፈ እንደሆነ ያሳየን ሲሆን ህዝቡም ቅሬታዎቹ እየፈቱለት ሲያይ በእምነትና በባህሉ ላይ ድርድር እንደሌለው የኢሬቻ በአል ለአለም አሳይቷል፡፡

No comments:

Post a Comment