EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Monday 23 October 2017

ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ በሁለቱ ምክር ቤቶች የ2010 ስራ ዘመን መክፈቻ ላይ ያደረጉት ሙሉ ንግግር

የተከበራችሁ የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አባላት፤
የተከበራችሁ መላ የአገራችን ሕዝቦች፤
ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶች፤
ክቡራትና ክቡራን፤
ከሁሉም በማስቀደም ሁለቱ ምክር ቤቶች በ5ኛው የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች፣ ሶስተኛውን ዓመት የስራ ዘመን ለምትጀምሩበት ለዛሬው ቀን እንኳን አደረሳችሁ እያልኩ ከልብ የመነጨ መልካም ምኞቴን በራሴና በኢፌዴሪ መንግስት ስም ለማቅረብ እወዳለሁ፡፡

የተከበራችሁ የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አባላት፤
የተከበራችሁ መላ የአገራችን ሕዝቦችን፤
የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤትነትን ከማንኛውም ግለሰብና የፖለቲካ ሃይል አምባገነንነት አውጥቶ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት ባደረገው ህገ-መንግስታችን እንዲሁም እያበበ በመሄድ ላይ በሚገኘው የፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችን ውስጥ ትልቅ ሚና የሚጫወቱት ሁለቱ ምክር ቤቶቻችን፣ የስራ ዘመን መርሃ ግብር አሀዱ ብለው በሚጀምሩባት በዚህች ቀን፣ አገራችን የተያያዘችውን የህዳሴ ግስጋሴ በተሻለ ፍጥነት በሚያስቀጥሉ ብሎም ወደ ላቀ ከፍታ በሚያሸጋግሯት አበይት ጉዳዮች ላይ ትኩረታችን አድርገን መወያየት እንዳለብን እሙን ነው፡፡
ከዚህ አንፃር ባሳለፍነው ዓመት ያገኘናቸውን ጅምር ድሎችና መልካም ተሞክሮዎችን በምናሰፋበት እንዲሁም አጋጥመውን የነበሩትን ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ችግሮች በሚቀረፉበትና የሕዝባችን የላቀ ተጠሚቃሚነት በሚረጋገጥባቸው ጉዳዮች ላይ ግልጽና ሰፊ ምክክር ማድረግ ይገባል፡፡
የ2010 ዓ.ም ሁለተኛውን ሚሊኒየም አገባደን አዲሱን የኢትዮጵያ ሚሊኒየም ከተቀበልን የመጀመሪያውን አስር ዓመት በድል ያጠናቀቅንበት ዓመት በመሆኑ ታሪካዊ ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡
ሀገራችን በሁለተኛው ሚሊኒየም የመጀመሪያዎቹ ዘመናት አካባቢ ከነበረችበት ገናና የስልጣኔ ማማ እየወረደችና እያሸቆለቆለች ቆይታ በሁለተኛው ሚሊኒዮም ማገባደጃ አካባቢ በውድ ልጆቿ መራር መስዋዕትነት በተከፈተው አዲስ ምዕራፍ የህዳሴ ጉዞዋን ከጀመረች እነሆ ሩብ ምዕተ ዓመት አካባቢ ሆኗታል፡፡ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ተሃድሶ ከጀመረችበትና እጅግ ፈጣን፣ ፍትሃዊ ዘላቂነት ያለው ዕድገት ማስመዝገብ ከጀመረችም ወደ አስራ አምስት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡
አዲሱን የኢትዮጵያ ሚሊኒየም ከጀመርንም ጊዜ አንስቶ በነበሩት የመጀመሪያዎቹ አስር ዓመታት በአማካይ የ10.5 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ በዓለም ፈጣን ዕድገት ካስመዘገቡ ሀገሮች ተርታ በግንባር ቀደም ስፍራ ላይ እንገኛለን፡፡ የአዲሱን ሚሊኒየም ሁለተኛውን አስር ዓመት በተመሳሳይ የዕድገት ፍጥነት ከቀጠልንም መካከለኛ ገቢ ያላት ሀገር እንደምትኖረን እርግጠኛ መሆን ይቻላል፡፡
የተከበራችሁ የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አባላት፣
የተከበራችሁ መላ የአገራችን ሕዝቦች፣
የ2009 ዓ.ም የስራ አፈፃፀማችን የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ሁለተኛው ዓመት የስራ አፈፃፀም ይሆናል፡፡ የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን የመጀመሪያ ዓመት ውጤትም የሚታወቀው በ2009 ዓ.ም በመሆኑ የዚህንም ውጤት አብሮ መመልከቱ የሀገራችንን የዕድገት ግስጋሴ ለመረዳት በእጅጉ ይጠቅማል፡፡
በ2008 ዓ.ም በሀገራችን ከፍተኛ ድርቅ ተከስቶ የነበረም ቢሆን ኢኮኖሚያችን በፈጣን ሁኔታ በማደግ የ80 በመቶ አማካይ ዓመታዊ ዕድገት ማስመዝገቡ ይታወሳል፡፡ በተለይም በዚሁ ዓመት የተከሰተው ድርቅ ለኢኮኖሚው ወደ 37% ድርሻ የሚያበረከተውን የግብርና ዘርፍ ተጨማሪ እሴት በዕቅድ ከተያዘው የ8.2% የዕድገት ምጣኔ በማነስ 2.3% ዕድገት እንዲያስመዘግብ ቢያደርግም የሌሎች ዘርፎች ማለትም የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ከነባር እንዱስትሪዎች የማምረት አቅም መሻሻል እንዲሁም ወደ ማምረት የተሸጋገሩ አዳዲስ የኢንዱስትሪ ኢንቨስትንመንቶች ምክንያት እጅግ ፈጣን ማለትም የ18.4% ዕድገት ማስመዝገብ ተችሏል፡፡
ለኢንዱስትሪ ዘርፍ የ20.6% ፈጣን ዕድገት ከማነፋክቸሪንግ ባሻገር የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዘርፍም የ25% ዕድገት በማስመዝገብ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ የአገልግሎት ዘርፉም ፈጣን ዕድገት በመቀጠሉ የዕድገትና ትራንስፎርሜሸን የመጀመሪያ ዓመትም ኢኮኖሚያችን የሚያጋጥሙትን የተለያዩ ተግዳሮችን የመቋቋም አቅሙ ከፍተኛ እየሆነ መምጣቱን በሚያስመሰክር ፈጣንና ዕድገት ማስመዝገብ መቀጠላችንን አስመስክሮ አልፏል፡፡
የ2009 ዓ.ም የኢኮኖሚ ዕድገት መረጃ በቅርብ የታወቀ በመሆኑ ኢኮኖሚያችን በዓመቱ በአማካይ የ10.9% ማደጉን ያመለክታል፡፡ ይህ ውጤትም ኢኮኖሚያችን በጠንካራ ሁኔታ ማገገሙን የሚያመላክትና በዓመቱ ይገኛል ተብሎ ከተተነበየው የ11.1 በመቶ ጋር እጅግ ተቀራራቢ እንደሆነ ማየት ይቻላል፡፡ በዚህ ዕድገት ግብርናችን የ6.7% እሴት መጨመሩንና ይህም ከተተነበየው የ8.0% ዕድገት በመጠኑ አንሶ የተገኘው የበልግ ግብርናችን በአንዳንድ አካባቢዎች ከድርቅ ክስተት አለመላቀቁና መጤ ተምች በአንዳንድ አካባቢዎች የበቆሎ ምርትን በመጠኑ በመጉዳቱ ነው፡፡
ሆኖም ግን የኢንዱስትሪና የአገልግሎት ዘርፎች እጅግ ፈጣን ዕድገት ያስመዘገቡ በመሆኑ የዕድገት ምጣኔውን ከትንበያው ጋር ተቀራራቢ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በዚህም መሰረት የኢንዱስትሪ ዘርፍ ባጠቃላይ የ18.7% አጅግ ፈጣን ዕድገት ሲያስመዘግብ የትላልቅና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች የ23.2% እና የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የ21% ሁለቱም የኢንዱስትሪ ዘርፎች የላቀ ፍጥነት ያለው ዕድገት አስመዝግበዋል፡፡ የአገልግሎት ዘርፍም አምና ከነበረው ዕድገት በተሻለ ደረጃ የ10.3% ማስመዝገብ ችሏል፡፡
በዚህ ውጤት መሰረትም በ2009 ዓ.ም የኢኮኖሚያችንን ጥንቅርና ድርሻ ስንመለከት ግብርና የ36.3% ከዚህም ውስጥ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የ6.4% እና የአገልግሎት ዘርፍ የ39.3% ድርሻ ነበራቸው፡፡ እነዚህ የድርሻ ሽግሽጉችን በምናይበት ጊዜ ኢኮኖሚያችን ተስፋ በሚሰጥ ደረጃ የመዋቅራዊ ሽግግር ማድረግ መጀመሩን ነው፡፡
ባጠቃላይ በዓመቱ በኢኮኖሚያችን ውስጥ የተካሄደው የኢንቨስትመንት አፈፃፀም ለአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርትና ምርታማነት ዕድገት፣ የስራ ስምሪትና የድህነት ቅነሳ ጋር ተያይዘው ለተቀመጡት ግቦች መሳካት አዎንታዊ አስተዋፅኦ እንደነበራቸው በውል መመልከት ይቻላል፡፡
በዚህም መሰረት በ2010 ዓ.ም ፈጣንና ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲኖረው የ11.1 % ዓመታዊ አማካይ ዕድገት እንዲሆን ይደረጋል፡፡ የኢኮኖሚው ፍትሃዊነት እንዲረጋገጥም ግብርና አሁንም በርካታ የህብረተሰብ ክፍል የሚሳተፍበትና የዕድገታችን ምንጭ በመሆኑ ቢያንስ የ8.0% እንዲያስመዘግብ ይጠበቃል፡፡ ፈጣን ዕድገት ማረጋገጣችን እዚያው ሳለ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ትራንስፎርሜሽን እንዲያቀላጥፍ የኢንዱስትሪ ዘርፍ በተለይም የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ እጅግ ፈጣንና በላቀ ዕድገት ማስመዝገቡን እንዲቀጥል ይደረጋል፡፡ ከጥቃቅን አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች 22.6% አካባቢና ከትልቅ ኢንዱስትሪዎች የ21.8% እና ከኮንስትራንክሽን ኢንዱስትሪ የ23% ዕድገት ይጠበቃል፡፡ የአገልግሎት ዘርፉም የ11.0% ዕድገት እንዲያስመዘግብ ይጠበቃል፡፡
የተከበራችሁ የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴራሽን ምክር ቤቶች አባላት፣
የተከበራችሁ መላ የአገራችን ሕዝቦች፣
ክቡራትና ክቡራን፣
በ2009 ዓ.ም የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚን የመፍጠር ጉዳይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ሲተገበር ቆይቷል፡፡ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን የዋጋ ንረት በነጠላ አሃዝ እንዲገደብ አቅጣጫ መቀመጡም ይታወቃል፡፡ ይህንኑም ለማሳካት በ2009 ዓ.ም የግብርና ምርትና ምርታማነት የማሳደግ የዋጋ ማረጋጊያ የእህል ክምችት መያዝ፣ ከዝቅተኛና የተረጋጋ የዋጋ ምጣኔ ጋር የሚጣጣም የገንዘብ፣ የፊሲካልና የውጥ ምንዛሬ ተመን ፖሊሲዎችን መከተልን እንደ ዋና ዋና የማስፈፀሚያ ስትራቴጂዎች ተወስደው ተሰርቷል፡፡
በዚህም መሰረተ የ2009 ዓ.ም የአስራ ሁለት ወራት ተንከባላይ አማካይ የዋጋ ግሽበት በተያዘው ዕቅድ መሰረት በነጠላ አሃዝ መገደብ የተቻለ ሲሆን ይህም አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 7.2% ተመዝግቧል፡፡ በተጨማሪም ጠቅላላ የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ የዋጋ ግሽበት እንደቅደም ተከተላቸው 7.49% እና 7.1% ሆኗል፡፡ ይህም በበኩሉ የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ እንዲኖር ተግባራዊ የተደረጉ የፊሲካልና የገንዘብ ፖሊሲዎች እንዲሁም የተወሰዱ አስተዳደራዊ ርምጃዎች የተፈለገውን ውጤት ያስገኙ መሆናቸውን ያመለክታል፡፡
ከፊስካል ፖሊሲ አኳያ የአገር ውስጥ የፋይናንስ አቅምን በማጠናር ከታክስና ሌሎች ምንጮች የሚገኙ ገቢዎችን በአግባቡ መሰብሰብ፣ የመንግስትን ወጪዎች ፍትሃዊ የሃብት ድልድልንና ፈጣን ዕድገትን በሚያረጋግጥ መልኩ መፈፀም፣ የታክስና የጉምሩክ ፖሊሲዎች ገቢ ከማስገኘት ባለፈ የኢንዱስትሪ ልማትንና የኤክስፖርት ግኝትን በሚያበረታታ መልኩ ለመቃኘት ጥረት ተደርጓል፡፡ ከዚሁ በተጨማሪም መንግስት የሚወስዳቸውን ብድሮች በአግባቡ ማስተዳደር የሚያስችል የፊሲካል ዲስፒሊን ማስፈንን እንደዋነኛ ስልት በመውሰድም ሲሰራ ነበር፡፡ በተመሳሳይ የመንግስት የበጀት ጉድለት ከአጠቃላይ አገራዊ ምርት ድርሻ ወደ 3% አካባቢ እንዲሆን ታቅዶ የተሻለ አፈፃፀም በመመዝገብ 2.5% እንዲሆን ከመደረጉም ባሻገር አሸፋፈኑም የሀገር ውስጥ ምንጮችን አሟጦ በመጠቀምና የተሻለ ድርሻ እንዲኖራቸው በማድረግ የተፈፀመ ነበር፡፡
በዚህ መሰረት በ2009 ዓ.ም ከታክስና ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች ለመሰብሰብ ከታቀደው 94.3% በመቶ ለማሳካት ተችሏል፡፡ የታክሲ ገቢ ለብቻው በሚታይበት ጊዜ አፈፃፀማችን የ92% አካባቢ ሆኗል፡፡ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ17% አካባቢ ዕድገት የተመዘገበ ቢሆንም ይህ አፈፃፀም ወትሮ ከተለመደው በትንሹ የ98% አፈፃፀም ጋር ሲነፃፀርም  ሆነ ኢኮኖሚያችን ከሚያመነጨው ገቢ ሊሰበሰብ ከሚገባው ጋር ሲነፃፀር አንሶ የሚታይ ነው፡፡
በመሆኑም 2010 ዓ.ም ይህንን ሁኔታ ለመቀየር በአዲስ መልክ ተጠናክሮ የተጀመረውን የታክስ ሰሪፎርም ስራ በተለይም በትልልቆቹ የታክስ ከፋዮች ላይ በማተኮር መስራት እንዳለብን የሚያመላክት ነው፡፡ የታክስ ትራንስፎርሜሽን የሚያተኩርባቸው የውዝፍ ዕዳ አሟጦ የመሰብሰብ፣ የታክሲ ኦዲት ስርዓቱን ዓለም ዓቀፍ ተሞክሮን መሰረት በማድረግ የማዘመንና የስጋት የስራ አመራርን መሰረት ያደረገ እንዲሆን የማድረግ፣ የታክስ መረጃ ስርዓት ላይ ያለውን ችግር ለመቅረፍ የመረጃ ቴክኖሎጅን ስርዓት ባለው መንገድ የመጠቀም፣ እንዲሁም የታክስ አስተዳደር መስሪያ ቤቱን የውስጥ ድርጅታዊ ጤንነት የመጠበቅና የታክስ ሰብሳቢ ሙያተኞችን በመስሪያ ቤቱ የማቆየት ስራ እንዲሁም ውጤት ተኮር የስራ አመራርን የማጎልበት ስራ የሚሰራ ይሆናል፡፡
ይህንንም በማድረግ በዘርፉ የሚታየውን ያለአግባብ የመጠቀም ዝንባሌና ተግባር እንዲሁም ሙስና የታክስ ከፋዮን ህብረተሰብ በስፋት በማሳተፍ መታገልና የአስተዳደር ስርዓቱን ማጎልበት የሚኖርብን ይሆናል፡፡ በትልልቅ ታክስ ከፋዮች ትኩረት ማድረጋችን እንደተጠበቀ ሆኖ በተለይም በኮንስትራክሽን ዘርፍ እንዲሁም በማኑፋክቸሪንግና ሌሎች የታክስ እፎይታ ጊዜ ከተጠቀሙ በኋላ በህጉ መሰረት የማይከፍሉ ታክስ ከፋዮች ላይ ትኩረት ሰጥተን የህግ ማስከበሩን ስራ አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡ በሀገሪቱ ባሉ ዋና ዋና ከተሞች ንግድና አገልግሎት ተብሎ የተገነቡ ህንፃዎች አካባቢ ከኪራይ ጋር በተያያዘ የሚካሄደውን ማጭበርበርና ታክስ ስወራም እንደዚሁ ትኩረት ሰጥተን ህጋዊ መስመር ለማስያዝ የሚሰራ ይሆናል፡፡ መንግስት የተጀመረውን የልማት ስራ ለማስቀጠልና ብቁ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለው አቅም ከሀገር ውስጥ ሃብት ለማሟላ የተያዘው ውጥን እንዲሳካ የሀገር ውሰጥ የታክሲ ገቢ መሰብሰብ ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው ነው፡፡
በዘንድሮ ዓመት የ“ሐ” የግብር ከፋዮች የታክስ ግምት በተመለከተ የተከሰተው የግምት መዛባትና በአንዳንድ ታክስ ከፋዮች አካባቢ የተከሰተ የዕቃ መሰወር ዓይነት ችግር እንዳይከሰትና የታክስ አከፋፈሉ ተገማች እንዲሆን በጥናት ላይ የተመሰረተና የታክስ ከፋዮች ራሳቸው የተሳተፉበት የመፍትሄ አቅጣጫ ለመቀየስ የሚሰራ ይሆናል፡፡ ይህንን በማድረግም መዝገብ የማይዙ የታክስ ከፋዮች ጋር የሚገጥመውን ውዝግብ ለማስቀረት ጥረት ይደረጋል፡፡
የ2009 ዓ.ም የተጠቀምነው የገንዘብ ፖሊሲና የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ልማት ትኩረት ያደረጉት የገንዝብ አቅርቦትና ዝውውር ሚዛናዊ እንዲሆን፣ የተረጋጋና በነጠላ አሃዝ የተገደበ የዋጋ ግሽበት እንዲኖር ማድረግና የተረጋጋና የውጭ ንግድን የሚያበረታታ የውጭ ምንዛሬ ፖሊሲን መከተል እንዲሁም የፋይናንስ ተቋማት የታቀደውን መዋራዊ ሽግግር እንዲያግዙ ማስቻል ላይ ነበር፡፡
የተረጋጋ የወጭ ንግድን የሚያበረታታ የውጭ ምንዛሬ ፖሊሲን ከማስፈፀም አኳያ በ2009  ዓ.ም ከሞላ ጎደል የተረጋጋ ተመን የነበረ ቢሆንም ቀጥለን እንደምናየው ለባለፉት ሶስት ተከታታይ ዓመታት ኤክስፖርታችን ባለበት በመቆሙ ምክንያት የውጭ ምንዛሬ አቅርቦቱንና ፍላጎትን ለማሟላ ከፍተኛ እጥረት አጋጥሞን ነበር፡፡ ስለሆነም የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ እንዲኖር ከማድረግ አኳያ ሀገራችንን የገጠማት ዋነኛ ፈተና የኤክስፖርት ገቢያችንን በፍጥነት በማሳደግ የሚፈለገውን የውጭ ምንዛሬ በከፊልም ቢሆን በማግኘት እየሰፋ የመጣውን የውጭ ንግድ ሚዛን ማጥበብ ነው፡፡ በመሆኑም የ2010 ዓ.ም ዕቅድ ዋነኛ ትኩረትም የኤክስፖርት ምርትና ግብይት ጉዳይ የሞት ሽረት ጉዳይ ተደርጎ መወሰድና በኤክስፖርት ገቢያችን 80% አስተዋፅኦ የሚያበረክቱትን ቡና፣ ሰሊጥ፣ ጥራጥሬ፣ ቅመማ ቅመም፣ አበባና የቁም እንስሳት በመጠንና በጥራት በማሳደግ ከፍተኛ ለውጥ በማምጣት ላይ ሊሆን ይገባል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ በማዕድን ዘርፍ ወርቅና ሌሎች ጌጣጌጥ ማዕድናት እንዲሁም እየተስፋፉ የመጡትን ኢንዱስትሪ ፓርኮች ማዕከል በማድረግ የማኑፋክቸሪንግ ምርቶች ኤክስፖርት በፍጥነት እንዲያድግ በማድረግ ላይ ይሆናል፡፡ ይህንንም ለማበረታታት የውጭ ምንዛሬ ተመን ላይ በጥናት ላይ የተመሰረተ ማሻሻያዎች የሚደረጉ ይሆናል፡፡
የሀገራችን የፋይናንስ ኢንዱስትሪ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ትራንስፎርሜሽን የሚያግዝበት አንዱና ዋናው መንገድ ቁጠባን በማበረታታትና የፋይናንስ አቅርቦትን በማሳደግ ነው፡፡ ባንኮቻችን በግሉ ዘርፍም ሆነ ለመንግስት የልማት ድርጅቶች የኢንቨስትመንት ፋይናንስና የስራ ማስኬጃ በማቅረብ ትልቅ ሚና እየተጫወቱ ይገኛል፡ የባንኮች ተቀማጭ በዓመቱ ውስጥ በ23% ያደገ ሲሆን ለዚህ ውጤት መገኘት ባንኮች በርካታ ቅርንጫፎችን በመክፈት ለሕዝቡ ተደራሽ መሆን በመቻላቸው ነው፡፡ የፋይናንስ ተቋማት አትራፊነትም ወትሮ ከሚታወቀው ምጣኔ በላይ መሆኑ የተረጋገጠ በመሆኑ የሀገራችን ባንኮች እጅግ አትራፊ ሆነው ቀጥለዋል፡፡ ይህም ጤናማ የፋይናንስ ተቋማት ስርዓት እየተዘረጋ መሆኑን ያመለክታል፡፡ በሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን መጨረሻ ቁጠባ ከሀገር ውስጥ አጠቃላይ ምርት ያለው ድርሻ ወደ 29% እንዲያድግ የፋይናንስ ተቋማት የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማድረግ የፖሊሲ ድጋፎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ ይሆናል፡፡
የተከበራችሁ የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አባላት፣
የተከበራችሁ መላ የአገራችን ሕዝቦች፣
ክቡራትና ክቡራን፣
የሀገራችንን አምራች ዘርፎችን በማጎልበት በጥራት፣ በምርታማነትና በተወዳዳሪነት የላቀ ዕድገት እንዲመጣ በትኩረት ሲሰራ ነበር፡፡ በዚህም መሰረት የስትራቴጂያዊ የምግብ ሰብሎች ምርትና ምርታማነት በማደጉ ምክንያት ከአምናው ጋር ሲነፃፀር ወደ 9. በመቶ የሚጠጋ ዕድገት ለማስመዝገብ ተችሏል፡፡ የምርታማነት ዕድገትን በተመለከተም በአማካይ ወደ 8.4% ማሳደግ ተችሏል፡፡ ሆኖም ለምርታማነት ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያበረክተው የምርጥ ዘር አቅርቦት በታሰበው ልክ ባለመሆኑ ምንም እንኳ የአፈር ማዳበሪ አቅርቦት ከዕቅዱ ጋር የተመጣጠነም ቢሆን የምርታማነት ዕድገቱ የታሰበውን 12% ያህል ዕድገት ሳያስመዘግብ ቀርቷል፡፡ በመሆኑም በ2010 ዓ.ም ስራችን ለአርሶ አደሩና ከፊል አርሶ አደሩ የምንሰጠው የኤክስቴሽንን አገልግሎት ከተሟላ የምርጥ ዘር አቅርቦትና እንደዚሁም የተሟላ የቴክኖሎጂ ምክረ ሃሳብ መሰረት እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት መደረግ ያለበት ይሆናል፡፡
የዋና ዋና ሰብሎች ምርታማነትና የምርት ዕድገት እንዲጨምር የራሱን የማይተካ ሚና የሚጫወተው የግብርና ሜካናይዜሽን መሆኑ ይታወቃል፡፡ በ2009 ዓ.ም ከግብርና ማካናይዜሽን አኳያ የአነስተኛ እርሻ መሳሪያዎች አቅርቦትና የሰውና የእንስሳት ጉልበትን ምርታማና የሚያደርጉ ቴልኖሎጂዎች አርሶ አደሩ እንዲጠቀም ለማድረግ በተሰራው ሰራ መልካም ውጤቶች መገኘት ጀምረዋል፡፡ ስለሆነም በ2010 ዓ.ም የአጨዳና መውቂያ፣ የዘር መዝሪያና ተከላ እንዲሁም የማሳ ማዘጋጃ መሳሪያዎች በነፍስ ወከፍና በቡድን ለማቅረብ ሀገር በቀል ማፋኑክቸሪንግ ኢንዱስሪዎችና ከቴክኒክና ሙያ የተመረቁ ወጣቶች ተሳትፎ እንዲጎለብትና መልካም ተሞክሮዎቹ እንዲሰፉ ለማድረግ የሚሰራ ይሆናል፡፡
ግብርናችንን ይበልጥ ለማዘመን ከተያዙ ስራዎች መካከል አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ የላቀ ዋጋ የሚያስገኙ ሰብሎችና የእንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ላይ እንዲሰማሩ የማድረግ ስራ አንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ በዚህም መሰረት በአርሶ አደሩም ሆነ በግል ባለሃብቱ ዓመቱን በሙሉ የመስኖን ውሃ በመጠቀም የሚመረተው የሆርቲካልቸር ምርት በመጠኑ በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል፡፡ የ2009 ዓ.ም አፈፃፀም የሚያሳየውም የአትክልት፣ ፍራፍሬና ስራ ስር ሰብሎች የምርት ጭማሪ ወደ 38% መድረሱን ነው፡፡ ይህ መልካም ውጤት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በዚህ ዘርፍ አሁንም እንቅፋት ሆኖ የሚገኘው የጥራት አመራረት ስርዓት የማስፈንና ከፊሉን ኤክስፖርት ለማድረግ የሚያስችል የሎጂስቲክስ አቅርቦት የማሻሻል እንዲሁም የአርሶ አደሩንና የግል ባለሃብቱን የማምረት ቅንጅት ወይም አውትግሮወር (Outgrower) ስርዓት ማጎልበት ይሆናል፡፡ በ2010 ዓ.ም እነዚህን ማነቆዎች መፍታት መጀመር ያለብን እና ከዘርፉ በ2009 ዓ.ም የተገኘውን 220 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላት ኤክስፖርት ወደ 400 ሚሊዮን ዶላር ለማሳደግ እንሰራለን፡፡
ከሆርቲካልቸር ሰብሎች በተጨማሪ የላቀ ዋጋ የሚያስገኙት ቡናና ሻይ፣ የቅባት እህሎች፣ ጥራጥሬና ቅመማ ቅመም ሰብሎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሰብሎች የላቀ ዋጋ ማስገኘታቸው ብቻ ሳይሆን እዚያው ሳሉ የኤክስፖርት እንዲሁም የኢንዱስትሪ ግብአት ሰብሎችም ጭምር ናቸው፡፡ በሰብሎቹ በአማካይ ከ15% እስከ 20% የሚሆን የምርታማነት ዕድገት እንዲመጣ የሚሰራ ይሆናል፡፡ ይህንን በማድረግም የቁም እንስሳትን ኤክስፖርት ጨምሮ በአጠቃላይ ከግብርና ዘርፍ ወደ 4.0 ቢሊዮን ዶላር ኤክስፖርት ገቢ እንደኖረን በትጋት የሚሰራ ይሆናል፡፡
የእንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት የላቀ ዋጋ የሚያስገኙ የግብርና ልማት ስርዓት ውስጥ የሚመደብ ነው፡፡ ይህ  ሊሆን የሚችለው ግን የአመራረት ስዓቱ ከሃላቀር ባህላዊ የአመራረት ስርዓት ደረጃ በደረጃ ወደ ዘመናዊ የአረባብና የዝርያ ማሻሻል፣ የእንስሳቱን ጤና መጠበቅና ጥራትና ቁጥጥር ማሳደግ እንዲሁም ዘመናዊ የእንስሳት መኖ አመራረት ስርዓት ውስጥ ሲገባ ነው፡፡ በዚህ ዙርያ በአርሶ አደሩም ሆነ በአርብቶ አደሩ አካባቢ ሊሰፋ የሚችሉ ምርጥ ተሞክሮዎች የተገኙ በመሆኑ የ2010 ዓ.ም ዕቅድ እነዚህን ምርጥ ውጤቶች በማስፋት ላይ ያተኮረ ይሆናል፡፡
የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ፈጣንና የላቀ ዕድገት እንዲያረጋግጥ ማድረግ የኢኮኖሚያችንን መዋቅራዊ ትራንስፎርሜሽን ለማረጋገጥ ቀዳሚ ስራ ነው፡፡ በዚህም መሰረት ትኩረታችንን የሰው ጉልበትን በስፋት የሚጠቀሙና ኤክስፖርት መር የሆኑ ቀላል የማኑፋክቼሪንግ ኢንዱስትሪዎች ላይ በማድረጋችን የሀገር በቀል ኩባንያዎችና የተመረጡ ስመ ጥር የሆኑ የውጭ ኩባንያዎች በዘርፉ በስፋት መሰማራት ጀምረዋል፡፡ ይህንኑ ጅምር ይበልጥ ለማስፋፋትና ለማጠናከር የሀገር በቀል ኩባንያዎች ከኮንስትራክሽንና ሪልእስቴት፣ ከንግድና አገልግሎት ዘርፎች ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲገቡ አስፈላጊውን ድጋፍ በተከታታይና በጥራት መስጠት የሚገባን ይሆናል፡፡ ከዚሁ በተጨማሪም የክልል መንግስታት ትኩረት ሰጥተው እየሰሩበት ካለው ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ እንዲሁም ከመካከለኛ ወደ ትላልቅ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ሽግግር እንዲከናወን መትጋት ያለብን ይሆናል፡፡ በዚህም መሰረት ቅድሚያ ትኩረት በተሰጣቸው የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ የምግብና መጠጥ  እንዲሁም ሌሎች አግሮፕሮሰሲንግ ፋብሪካዎች ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋና የነባር ፋብሪካዎች የአቅም አጠቃቀም እንዲሻሻል የሚሰራ ይሆናል፡፡ ሌሎች ማለትም የፋርማስቲካል፣ የኬሚካልና የኮንስትራክሽን ግብአቶች ማምረቻ ኢንዱስትሪዎች እንዲሁም የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ እና የኤሌክትሪካልና ኤሌክትሮኒክስ ኢንዱስትሪዎች በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ የሆነ ምርት ነገር ግን የኢምፓርት ዕቃዎች በመተካት ላይ በማተኮር እንዲሰሩ እየተሰጣቸው ያለ ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡  
መንግስት የኢንዱስትሪ ፖርኮችን ልማት እንደ አንድ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ማስፈፀሚያ መሳሪያ አድርጎ እየተጠቀመ ያለ በመሆኑ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎችን የመሬት፣ የመሰረተ ልማት፣ በአንድ መስኮት አገልግሎት አሰጣጥና ለሀገር በቀል ኩባንያዎች ደግሞ የፋይናንስ፣ የክህሎትና የኢንዱስትሪ አመራር ችሎታ እንዲሁም የገበያ ትስስር ችግራቸውን በሚፈታ መንገድ በመቃኘት ውጤታማ መሆን ጀምሯል፡፡ ይህንን ጅምር ይበልጥ በጥራት የማስፋፋት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
የተከበራችሁ የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አባላት፣
የተከበራችሁ መላ የአገራችን ሕዝቦችን፣
ክቡራትና ክቡራን፣
የመሰረተ ልማት ክፍተቶችን መሙላትና የአገልግሎት አቅርቦት ጥራትን ማሳደግ የኢኮኖሚያችንን ተወዳዳሪነት ከሚወስኑ ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡ ይህንኑ በመገንዘብ መንግስት የመሰረተ ልማት ክፍተቶችን ለመሙላ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በ2009 ዓ.ም በገጠር ትራንስፎርሜሽን ትልቁን ሚና የሚጫወተውን የገጠር መንገድ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በተሰራው ስራ ወደ 75% የሚሆኑ የገጠር ቀበሌዎች እርስ በርስ  ከዋና ዋና መንገዶች እንዲገናኙ የሚያደርግ የገጠር መንገድ ተገንብቷል፡፡ የመንገዶቹን እንክብካቤ በቀጣይነት ከሰራን የአርሶ አደሩንና አርብቶ አደሩን ምርቶች ወደ ገበያ ለማውጣትና ወደ አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ የሚቀርቡ ግብአቶችንና አገልግሎቶችን ለማድረስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡ በ2010 ዓ.ም የተጀመረውን የገጠር ተደራሽነት መንገድ ስራ ወደ 85% ለማድረስና በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ሁሉን ቀበሌዎች ለማዳረስ የሚሰራ ይሆናል፡፡
በ2009 ዓ.ም ዋና ዋና መንገዶችን ማጠናከርና ደረጃ ማሻሻል፣ አገናኛ መንገዶችን ግንባታና ደረጃ ማሻሻያ ስራ ከዕቅዱ 97% ማሳካት ተችሏል፡፡ ወደ 8% የሚሆኑ መንገዶች አነስተኛ አፈፃፀም የታየባቸው በመሆኑ ኮንትራቱን አቋርጦ ለሌላ ኮንትራክተር ለመስጠት እየተሰራ ይገኛል፡፡ ባጠቃላይ ግን የመንገዶች ፕሮጀክቶች አፈፃፀም በሚታይበት ጊዜ በአብዛኛው በታቀደው መሰረት የፕሮጀክት አፈፃፀሙ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ከ2010 ዓ.ም ትኩረት የሚሆነው የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን የማስጨረስና የአዳዲሶቹን የመጀመርያ ስራ እንደተጠበቀ ሆኖ የመንገዶች ልማት አካሄዳችንን በህገ መንግስቱ በተቀመጠው የፌዴራልና የክልል መንዶች ክፍፍል መሰረት የፈዴራል ስርዓት የሚከተሉ ሀገሮች ልምድ በመውሰድ የፌዴራልና የክልል መንገዶች ለመለየት የተጀመረውን ጥናት በማጠናቀቅ ወደ ትግበራ የሚገባ ይሆናል፡፡ በዚህም መሰረት የፌዴራልና የክልል ያልተምታታ የስራ ድረሻ የሚኖር ይሆናል፡፡
የባቡር መሰረተ ልማት ግንባታ እጅግ ግዙፍ ፋይናንስ የሚጠይቅ በመሆኑ በቅርቡ የተጠናቀቀውን የአዲስ አበባ ጅቡቲ መስመር ወደ ተሟላ ስራ እንዲገባ የማድረግና በግንባታ ሂደት ላይ ያሉትን የማስቀጠል ስራ የ2010 ዋና ዕቅድ ይሆናል፡፡ አዳዲስ ግንባታዎችን ለማስጀመር የሚያስችል ፋይናንስ ማግኘት ያልተቻለ በመሆኑ ይሄው እስከሚስተካከል ድረስ በዘንድሮ ዓመት አዳዲስ ግንባታዎች የሚጀመሩበት ሁኔታ አይኖርም፡፡
በኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር እጅግ ተፈላጊና ወሳኝ መሰረተ ልማቶች ውስጥ የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ዋናውና ወሳኙ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በዚህም መሰረት በቅርቡ የተጠናቀቀውን የጊቤ 3 ሃይል ማመንጫ በሙሉ አቅሙ እንዲሰራ ማድረግ፣ ስልሳ በመቶ የደረሰውን የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ማፋጠን፣፡ የገናሌ 3 ግድብን አጠናቅቆ ሃይል ማመንጨት መጀመር እንዲሁም የኮይሻ ግድብ፣ የመልካ ሰዲ ተርሚናል ማመንጫ፣ የአሉቶ ጂኦተርማል ማመንጫ፣ የረጲ ባዮማስ ማመንጫ፣ የአይሻ የንፋስ ሃይል ማመንጫ ስራዎች በዕቅዳቸው መሰረት ስራቸው እንዲፋጠን በዘንድሮ ዓመት ትኩረት የተሰጣቸው ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡
መንግስት ከሚያከናውነው የሃይል ማመንጫ ስራ በተጨማሪ በቅርቡ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ያፀድቀዋል ተብሎ በሚጠበቀው የመንግስትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት (Pivate Public Partnership) (PPP) ህግ መሰረት ለመጪው ጊዜ ኢኮኖሚያችን የሚፈልገውን ሃይል ከወዲሁ ለማዘጋጀት የግል ዘርፍ በሃይል ማመንጨቱ ስራ እንዲሳተፍ የመጋበዝና የማሳተፍ እንዲሁም በጅምር ላይ ያሉትን ወደ ስራ እንዲገቡ በትኩረት የሚሰራ ይሆናል፡፡
የሃይል ማስተላለፊያና ሰብስቴሽን ሰራዎች እንዲሁም የሰብስቴሽኖች አቅም የማጎልበት ስራ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ክላስተሮችንና ሌሎች የልማት ማዕከላትን መሰረት አድርጎ የሚሰራ ይሆናል፡፡
የኤሌክትሪክ ማከፋፈልና አገልግሎት አቅርቦት ላይ የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ እንዲያስችል ያልተማከለ የኤሌክተሪክ አገልግሎት አቅራቢ ድርጅቶችን ክልሎች እንዲያቋቁሙ በማድረግና አቅማቸውን በማሳደግ ወደ ስራ እንዲገቡ ይደረጋል፡፡ ይህንንም መሰረት አድርጎ የገጠር ኤሌክትሪክ ተደራሽነት ስራ ከግሪድ ውጭ ባልተማከለ ሁኔታ ከታዳሽ ሃይሎች የማቅረብ ፕሮጀክቶች በዘንድሮ ዓመት ወደ ስራ እንዲገቡ ይደረጋል፡፡
የዲጂታል መሰረተ ልማት አቅርቦትን በተመለከተ የማምረቻና የንግድ ስራዎች፣ የመማር ማስተማር አገልግሎት፣ የመንግስት የአገልግሎት አሰጣጥ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆን የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ የግል ባለሃብቶች በአይሲቲ ሶፍትዌር ግንባታ እንዲሁም በአይሲቲ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ እንዲሳተፉ ለማድረግ የተጀመረው ስራ ፍሬ እያፈራ ያለ በመሆኑ ይህንንም ማጠናከርና ስፋቱም እንዲጨምር ተደርጎ ይሰራል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ በገጠር ማዕከላት የኢንተርኔትና የመረጃ ፍላጎትን ለማርካት በያንዳንዱ ቀበሌ የሕዝብ ኮሙኒኬሽን ማዕከል ለማደራጀት የተጀመረው ስራ እስካሁን ወደ 12% የሚሆኑ ቀበሌዎችን ያዳረሰ ሲሆን በ2010 ዓ.ም ይህንን ሽፋን ወደ 40% ለማድረስ የሚሰራ ይሆናል፡፡
ለተከበራችሁ የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አባላት፣
የተየከበራችሁ መላ የአገራችን ሕዝቦች፣
ክቡራትና ክቡራን፣
የሰው ሃብታችን የተማረ፣ ክህሎት ያለውና ከቴክኖሎጂ ጋር የተዋወቀ እና የሚጠቅም እንዲሆን የትምህርትና ስልጠና ፕሮግራሞችን በሁሉም እርከኖች የትምህርት ተሳትፎ በማሳደግ ረገድ መልካም ውጤቶች ተገኝተዋል፡፡ በዚህ ዙሪያ እንደ እጥረት ወስደን በፍጥነት ማሻሻል የሚገባን የመዋዕለ ህፃናት ትምህርትና የገጠሩን ትራንስፎርሜሽን በማቀላጠፍ ዙርያ ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያበረክተው የተቀናጀ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት አካባቢ ነው፡፡
በአጠቃላይ ትምህርት፣ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠናም ሆነ የከፍተኛ ትምህርት ላይ ልዩ ትኩረት መስጠት የሚገባን በትምህርት ጥራት ዙሪያ መሆን እንዳለበት ተወስኖ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ ከዘንድሮ ዓመት ጀምሮ ዩኒቨርሲቲዎችን የማስፋፋት እና የህንፃዎችን ግንባታ ስራ ገታ አድርገን የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና በያንዳንዱ ወረዳ እንዲስፋፋ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲዎች የላብራቶሪ፣ የወርክሾፖች፣ ሌሎች ግብአቶች የማሟላት ስራ ላይ ትኩረት ይሰጣል፡፡ ከሁሉም በላይ ለትምህርት ጥራት ወሳኙን ሚና የሚጫወቱት መምህራን በመሆናቸው በመምህራን የኑሮ ሁኔታ፣ ክህሎትና የስራ ዲስፕሊን እንዲሁም የስራ አካባቢ ማሻሻል ላይ ትኩረት ሰጥተን መስራት የሚገባን ይሆናል፡፡ ከዚሁ ባልተናነሰ ሁኔታ መልካም ዜጋ በማነጽ ትልቁን ድርሻ በወሰደው የስነ ዜጋና የስነ ምግባር ትምህርት ዙሪያ በጥናት የተለዩትን ጉድለቶች በማስተካከል ትምህርቱ በጥራት እንዲሰጥ የሚሰራ ይሆናል፡፡ በትምህርት ሴክተሩ ከላይ እስከታች የውጤታማነት ስኬት ወይም ዴሊቨሮሎጂ (Deliverology) ፅንሰ ሃሳብ ተግባራዊ ለማድረግ የተጀመረውን ስራ በጥራት እንዲፈፀምም የሚደረግ ይሆናል፡፡  
በ2009 ዓ.ም በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም በመታገዝ ፍትሃዊ፣ ተደራሽ፣ እንዲሁም ጥራቱን የጠበቀ መሰረታዊ ጤና አገልግሎት ለመስጠት የሰራነው ስራ ውጤታማ ነበር፡፡ የእናቶችንና የህፃናት ጤና አገልግሎት እንዲሁም ተላላፊ በሽታዎች የመከላከልና ቁጥጥር ስራ የበለጠ ጥራቱ የተጠበቀ እንዲሆን ከምናደርገው እንቅስቃሴ ባሻገር ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች የሚሞተው ሰው ቁጥር እጅግ እየጨመረ የመጣ በመሆኑ በ2010 ዓ.ም  ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን የመከላከል ስራ ህብረተሰባዊ ንቅናቄ እንዲፈጠር የምንሰራ ይሆናል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ ደግሞ ጥራቱ የተጠበቀ የሆስፒታል አገልግሎት መሰጠቱን የማረጋገጥ፣ እንዲሁም ከመድሃኒት አቅርቦት ጋር የተያያዘ አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል ትኩረት ይደረጋል፡፡ በተጨማሪም የግሉ ዘርፍ በተለይም በከተሞች አካባቢ በጤና መስክ አገልግሎት በመስጠት የሚኖራቸውን ሚና ይበልጥ ለማጠናከርና ለማስፋት እንዲሁም የሚሰጡት የጤና አገልግሎቶች ጥራታቸውን የጠበቁ እና ሁሉንም ወገኞች የሚያረኩ እንዲሆኑ ተገቢው ድጋፍ፣ የክትትልና ቁጥጥር ስርዓት እንዲዘረጋ ይደረጋል፡፡
የተከበራችሁ የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አባላት፣
የተከበራችሁ መላ የአገራችን ሕዝቦች፣
ክቡራትን ክቡራን፣
2010 ዓ.ም የመንግስት የማስፈፀም አቅም ለመገንባትና የሕዝቡን ተሳትፎ ባለቤትነት ለማጎልበት እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ ልማታዊነትንና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ከፍተኛ ጥረት የሚደረግበት ዓመት ነው፡፡ ይህንን ሁኔታ ለመፍጠር 2010 ዓ.ም የተሃድሶ እንቅስቃሴያችን ይበልጥ ጥልቀት እንዲኖረውና የስርዓቱ አደጋ የሆነውን ያለውድድርና አለአግባብ የመጠቀም እንዲሁም የሙስና ዝንባሌና ተግባር ለመቆጣጠር የጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ ታውጆ መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ የተደረገበት ዓመት ነበር፡፡ ሕዝባችን በየህብረተሰብ ክፍሉ በስፋት እንዲወያይና የትግሉ ባለቤት እንዲሆን በተሰራው ስራ መልካም ውጤቶች ማየት ጀምረናል፡፡ እነዚህ ጅምር ውጤቶች እንዲሰፉና ጥራት ያላቸው እንዲሆኑ ማድረግም የ2010 ዓ.ም ዋናው ስራችን ይሆናል፡፡
መላው የፖለቲካ አመራሮች እና የመንግስት ሰራተኞች በሕዝብ የተሰጣቸውን ሃላፊነት እና በሙያቸው ለማገልገል በተሰለፉበት ሁሉ በቅንነት፣ በትጋትና በታማኝነት እንዲያገለግሉ ለማድረግ፣ ስለሚሰሩበት ስራ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸውም ለማድረግ ሰፋፊ ስልጠናዎች ተሰጥተዋል፡፡ ለስራ መነሻ የሚያገለግል መግባባትም ተፈጥሯል፡፡ ይህንኑ መነሻ ተይዞ በተግባር ሂደት ይበልጥ አቅማቸው እየጎለበቱ እንዲሄድ የሚሰራ ይሆናል፡፡
አላግባብ የመጠቀምና ሙስና ጐልቶ በሚታይባቸው የታክስ ስርዓት፣ የመንግስት ወጪ አስተዳደር፣ ግዥና የኮንስትራክሽን ኮንትራት አስተዳደር፣ የመሬት ልማትና አቅርቦት እንዲሁም የመሬት አስተዳደርና ግንባታ ፈቃድ አሰጣጥ፣ በውድድር ላይ የተመሰረተ የንግድ ስርዓትና ፀረ ኮንትሮባንድ ንግድ እንቅስቃሴ፣ ቀልጣፋና ውጤታማ የፍርድ ስርዓትና የፖሊሲ አገልግሎት እንዲሁም የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች ዙሪያ የተጀመሩት የሪፎርም ስርዓቶችም በአንዳንድ ቦታዎች ውጤታማ መሆን የጀመሩ ሲሆን ባብዛኛው ቦታዎች ላይ ግን በዝግጅት ላይ ያሉ እና መጓተት የሚታይባቸው በመሆኑ በ2010 ዓ.ም  ፍጥነታቸውንና ጥራታችውን በመጨመር የተሟላ ትግበራ ውስጥ የሚገባበት ዓመት ይሆናል፡፡
በነዚህ ዘርፎች በሙስና ተግባር ላይ የተሰማሩ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና ተባባሪዎቻቸውን በህግ እንዲጠየቁ ለማድረግ የተጀመረው ስራም በ2010 ዓ.ም በጥናት ላይ ተመስርቶ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡  
የሪፎርም ሰራዎቹ ልማታዊነትን በማጎልበት፣ በአሰራር ስርዓቶች ውስጥ ግልፅነት እንዲፈጠር ሃላፊዎችም ሆኑ የመንግስት ሰራተኞች ስራቸውን በግልፅ አውቀው ባስገኙት ውጤትና ለሕዝቡ በፈጠሩት እርካታ ልክ የሚመዘኑበት ስርዓት እንዲተገበር የተቀረፁ በመሆናቸውና በሙከራ ደረጃ ውጤታማ መሆናቸው የተረጋገጠ ስለሆነ እነዚህን አጠናክረን ለመተግበር የምንረባረብበት ዓመት ነው፡፡ ውጤታማነትና ስኬት ወይም ዴሊቨሪ ፅንሰ ሃሳብን ተግባራዊ ለማድረግ በተጀመረባቸው ዘርፎች በሙሉ ከወዲሁ መልካም ውጤት ማየት የተጀመረ በመሆኑ አጠናክረንም እንቀጥላለን፡፡
ሕዝቡ ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎውን ለማሳደግ በተደራጀ ሁኔታ በለውጥና በልማት ቡድኖች፣ በፎረሞች፣ በብዙሃን ማህበራትና በሙያ ማህበራት ባጠቃላይ በሲቪል ማህበራት አማካይነት በቀጥታ ከሚያደርገው ተሳትፎ ባሻገር በተወካዮቹ አማካይነት በሕዝብ ም/ቤቶች የሚያደርገውን ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎውም እየጎለበተ መጥቷል፡፡ ይህ ተሳትፎው ወደ ታችኛው እርከን በሚወርድበት ጊዜ ይበልጥ መጠናከር ሲገባው ላልቶ የሚገኝባቸው ቦታዎች በርካታ በመሆናቸው በ2010 ዓ.ም የሕዝብ ም/ቤቶች ሕዝቡን ወክለው አስፈፃሚውን አካል የሚቆጣጠሩበት ሁኔታ ተጠናክሮ መሰራት ያለበት ይሆናል፡፡ ከዚሁም ባሻገር የተከበረው ም/ቤትም ፈጣንና ፍትሃዊ ልማታችንን የሚደግፉ፣ መልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲያዊ የሕዝብ ተሳትፎ ይበልጥ እንዲጎለብት የሚያደርጉና የፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችን በተጠናከረ መሰረት ላይ እንዲገነባ የሚያስችሉ አዋጆችንና ፖሊሲዎችን ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ እነዚህ ውስጥም ባለፈው ዓመት የምርጫ ስርዓታችንን በተመለከተ ሊደረግ የታሰበው ማሻሻያም ውይይት ሲካሄድበት የቆየ ሲሆን በዘንድሮ ዓመት ለተከበረው ም/ቤት ቀርቦ በ2010 ዓ.ም ለሚደረገው አጠቃላይ ምርጫ እንዲደርስ የሚደረግ ይሆናል፡፡  
በ2010 ዓ.ም በመላው ሀገሪቱ የሚካሄደው የአካባቢ እና ማሟያ ምርጫ ዴሞክራሲያዊነቱን ጠብቆ ነፃ፣ ፍትሃዊና በሕዝቡ ዘንድ ተአማኒነትን ያተረፈ ሆኖ እንዲጠናቀቅ መንግስት አስፈላጊውን ሁሉ የሚያደርግ ይሆናል፡፡
ከዴሞክራሲ ተቋማት መካከል በፖርላሜንታዊ ስርዓት ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱት የፖለቲካ ፓርቲዎች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ በሀገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ እንዲጎለብት የፖለቲካ ምህዳሩም ይበልጥ እንዲሰፋ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ እና ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጀመሩት ውይይትና ድርድር በተስማሙበት መርህ እና መርሃ ግብር መሰረት አየተጓዘ ይገኛል፡፡ መንግስት ሁሉም ያገባኛል የሚሉ በህጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሳተፉ ሁሌም በሩን ክፍት አድርጎ ለሂደቱ ስኬታማነት የሚሰራ ይሆናል፡፡
የሚዲያ ተቋማትም በሀገራችን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የበኩላቸውን በጎ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ተከታታይ ውይይቶችና ሴሚናሮች የተካሄዱ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የተጀመረውን የሚዲያ ሪፎርም ስራ ሁሉ ተሳትፈውበት የተሳካ እንዲሆን በ2010 ዓ.ም ተጠናክሮ የሚሰራ ይሆናል፡፡
በ2010 ዓ.ም መጀመሪያ ጀምሮ የተለያዩ ጥገኛ አስተሳሰቦች የወለዷቸው የፀረ ሰላም ሃይሎችም የተጠቀሙበት አለመረጋጋት በሀገራችን ተፈጥሮ የአስተቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ ይታወሳል፡፡ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት ከሕዝባችን ጋር ባደረግናቸው መጠነ ሲፊ ውይይቶችና በተደረሰው መግባባት መሰረት የሀገራችን ሰላምና ፀጥታ ወደ ተረጋጋ ሁኔታ በመመለሱም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ ተደርጓል፡፡ ይህንን ሰላማችንን አሁንም አጠናክረን ማስቀጠል ይገባናል፡፡ ለግጭቶች ምክንያት የሆኑ ያልተፈሩ የድንበር ማካለል ጉዳዮችን ከሞላ ጎደል በሁሉም አካባቢ ለመፍታት የተቻለም ቢሆንም አሁንም በኦሮሚያና በኢትዮ ሱማሌ አካባቢ ቅሪት ያልተስተካከሉ አፍራሽ አመለካከቶች የወለዷቸው ግጭቶች ተከስተው የሰው ህይወት በአሰቃቂ ሁኔታ ያለፈበትና ንብረቶች የወደሙበት ሁኔታ መኖሩ ይታወቃል፡፡ ይህ ሁኔታ በፍፁም መወገዝ ያለበትና መንግስት ፀጥታውን ከማስከበር ባሻገር አጥፊዎችን ወደ ህግ ለማቅረብ ሳይታክት እየሰራ ይገኛል፡፡ በ2010 ዓ.ም እንደዚህ አይነት በሕዝቦች መካከል ለዘመናት የቆየውን አንድነት የሚያፈርስ አካሄድ በጭራሽ ሊፈቀድ የማይገባው በመሆኑ የሁለቱም ክልል የሀገር ሽማግሌዎች፣ ባህላዊ መሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶችና ሴቶች እንዲሁም መላው የሁለቱ ክልል ሕዝቦች ሁኔታው ወደ ነበረበት እንዲመለስና የተፈናቀሉ ወገኖቻችንም መልሶ አንዲቋቋሙ ለማድረግ ከመንግስት ጎን እንዲቆሙ በዚህ አጋጣሚ ጥሪዮን ለማቅረብ እወዳለሁ፡፡ በሂደቱ የተጎዱ ዜጎች ቤተሰቦችም መጽናና እንዲሆንላቸው እመኛለሁ፡፡
በሀገራችን የህዳሴ ጉዞ ውስጥ ልዩ ትኩረት የሚሰጣቸውና የማይተካ ሚና የሚጫወቱ የህብረሰብ ክፍሎች መካከል ወጣቶችና ሴቶች ግንባር ቀደሞች ናቸው፡፡
ባለፈው ዓመት የወጣቶችን እኩል ተሳታፊነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በይበልጥ የማረጋገጥ ጉዳይ ከስራዎች ሁሉ አውራ ስራ ተደርጎ እንቅስቃሴ እንዲደረግበት ተወስኖ ነበር፡፡ በዚህም መሰረት በሀገራችን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ጉዞ የማይተካ ሚናቸውን እንዲጫወቱና በሂደቱም ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል የወጣቶች የዕድገትና የለውጥ ስትራቴጅና ማስፈፀሚያ ፓኬጅ ተከልሶ እንዲዘጋጅ ተደርጓል፡፡ በዝግጅቱ ሂደትም የወጣቶች የነቃ ተሳትፎ እንዲኖር ተደርጓል፡፡ ይህንኑ ፓኬጅ ወደ ስራ ለማስገባት የሚረዱ የተለያዩ ማኑዋሎችና ተዘጋጅተው የስራ መመሪያ እንዲሆኑም ተደርጓል፡፡ ስልጠናም ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ይህንን የለውጥና ዕድገት ፓኬጅ ወደ ስራ ለማስገባት የፌዴራል መንግስት ከመደበው 10 ቢሊዮን ብር የወጣቶች ፈንድ በተጨማሪም ክልሎችም በተመሳሳይ መልኩ በድምሩ ወደ 10 ቢሊዮን ብር መድበዋል፡፡ በድምሩ በፈንዱ ከሚንቀሳቀሰው 20 ቢሊዮን ብር ውስጥ ወደ ስራ የማስገባቱ ሂደት በዝግጅት ምዕራፍ መጓተት ምክንያት የዘገየ ቢሆንም ወደ ግማሽ ያህሉ በዓመቱ መጨረሻ ወደ ስራ በመግባቱ ለሁለት ሚሊዮን አካባቢ ወጣቶች ስራ ለመፍጠር ተችሏል፡፡ ካሉን የወጣት ስራ -አጦች ቁጥር አኳያ ብዙ መስራት ያለብን በመሆኑ በ2010 ዓ.ም መልካም ውጤቶቹና በሂደቱ ያጋጠሙንን ተግዳሮቶችና እንቅፋቶች ገምግመን ከምናገኘው ልምድ በመነሳት የተሻለ አፈፃፀም እንዲኖረን የሚጠበቅበት ዓመት ይሆናል፡፡ ከስራ ዕድል ፈጠራው ባሻገር ከወጣቶች የስብዕና ግንባታ ጋር የተያያዙ ስራዎች በራሳቸው በወጣቶቹ ተሳትፎና ባለቤትነት ውጤታማ እንዲሆኑ የምንሰራበትም ዓመት ይሆናል፡፡
ሴቶች በሀገራችን በሚካሄዱ በተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች በባለቤትነት በመሳተፍ በፀረ-ድህነት ትግላችን የማይተካ ሚናቸውን መጫወት ጀምረዋል፡፡ የገጠር ሴቶች ከመሬት ባለቤትነት የጋራ መብት መጎናፀፍ ባሻገር ወደ 25 ሚሊዮን የሚጠጉ ሴቶች በግብርናው ስራ ውስጥ በጓሮ አትክልት፣ በዶሮ እርባታ፣ በንብ፣ ማነብ፣ በማድለብና በመሞከት እንዲሁም በመስኖ እርሻ በመሳተፍ ተጠቃሚ መሆን ጀምረዋል፡፡ ይህ ጅምር ስራ ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ባሻገር በቤተሰብ የአመጋገብ ስርዓት በተለይም በህፃናት የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ላይ ለውጦች እንዲታዩ የራሱን በጎ ሚና ተጫውቷል፡፡
የጤና ኤክስቴንሽን ስርዓታችን የጀርባ አጥንት የሆኑት ሴቶች በመሆናቸውም ሀገራችን በእናቶችና ህፃናት ሞት መቀነስ በዓለም የተመሰከረለት ውጤት እንድታገኝ አስችሏታል፡፡ በጡትና ማህፀን ካንሰርን ጨምሮ በቤተሰብ ምጣኔ፣ በአመጋገብ ስርዓትና በተላላፊ በሽታዎች ዙሪያ የተሰጡ ስልጠናዎችም ውጤታማ መሆን ጀምረዋል፡፡
በሴቶች የትምህርት ተሳትፎ አኳያም በአንደኛ ደረጃ የተመጣጠነ ደረጃ የተደረሰም ቢሆን በ2ኛ ደረጃና ዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ መሻሻሎች ቢኖሩም ወደተፈለገው ደረጃ ለማድረስ በብርቱ መስራት የሚገባን ይሆናል፡፡ ሴቶች በተግባራዊ የተቀናጀ የጎልማሶች ትምህርት አኳያ ለራሳቸው ካገኙት ዕውቀትና ክህሎት ባሻገር በልጆቻቸው ትምህርት ተሳትፎና ጥራት ላይ የበኩላቸውን ሚና መጫወት ጀምረዋል፡፡ የጎልማሶች ትምህርት ተሳትፎ ገና ከግማሽ ያልዘለለ በመሆኑና የተሟላ ተፅእኖ መፍጠር ባለመቻሉ ይህንን ለማሳደግ መስራት የሚገባን ይሆናል፡፡
የተከበራችሁ የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴራሽን ምክር ቤቶች አባላት፣
የተከበራችሁ መላ የአገራችን ሕዝቦች፣
ክቡራትና ክቡራን፣
በመጨረሻም ሀገራችን የመረጠችውና በዓለም ህብረተሰብም ሃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ የዓለም ዜግነታችንን የገለፅንበት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂያችንን በየክፍላተ ኢኮኖሚው ዕቅድ ውስጥ ገብቶ እንዲተገበር እያደረገች ትገኛለች፡፡ በስትራቴጅያችን እንደተቀመጠውም ከቤት እንስሳት፣ ከአፈር መከላትና ከደን መጨፍጨፍ፣ ከሃይል ምንጭ ቴክኖሎጂ፣ ከትራንስፖርት፣ ከኢንዱስትሪና ከከተሞች የሚለቀቀውን የሙቀት አማቂ ጋዝ ለመቀነስ ከፍተኛ ጥረት ስናደርግ ቆይተናል፡፡ ውጤቶችንም አግኝተንባቸዋል፡፡
የአገራችንን ስትራቴጂ ከማንም ቀድመን በይፋ ለዓለም ህብረተሰብ ያስተዋወቅንበትም ዋናው ምክንያት ማንም እንኳን ሀገራችን ለዓለም የአየር ንብረት ለውጥ የምታበረክተው አስተዋፅኦ እዚህ ግባ የሚባል ባይሆንም ተጎጅነታችንን ለመቀነስ ሀላፊነት የሚሰማቸው የበለፀጉና በፍጥነት እያደጉ ያሉ ሀገሮች የስትራቴጅያችንን ማስፈፀሚያ ሃብት እንዲለግሱን ለማድረግ ነበር፡፡ በዚህ መሰረትም በ2009 ዓ.ም ወደ 110 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቶ ወደ ስራ እንዲገባ ተደርጓል፡፡ ይህም ሂደት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የአየር ንብረት ዲፕሎማሲ ስራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡ ሀገራችን በዓለም ዓቀፍ መድረክ ያላት ተሰሚነት ጐልብቶ በመቀጠሉ በአሁኑ ወቅት ሁለት ታላላቅ የአለም አቀፍ የአየር ንብረት ዲፕሎማሲ መድረኮችን በሊቀመንበርነት እየመራች ትገኛለች፡፡ በ2010 ዓ.ም የሀገራችንና የሌሎች ታዳጊ ሀገሮችን መብትና ጥቅም የሚያረጋግጡ ስራዎችን መተግበርን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡
ለተከበሩ የሁለቱ ም/ቤቶችም የ2010 ዓ.ም ውጤታማና መልካም የስራ ዓመት እንዲሆንላችሁ እየተመኘሁ የኢፌዴሪ መንግስትም የተጀመረውን የህዳሴ ጉዞ ከዳር እንዲደርስ አስፈላጊውን ሁሉ የሚያደርግ መሆኑን እገልፃለሁ፡፡

አመሰግናለሁ!!

No comments:

Post a Comment