EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Thursday 28 September 2017

ኮሽ ሲል ፌደራሊዝም የጥላቻ ዘመቻ


(በክሩቤል መርሃጻድቅ)
ሀገራችን እየተከተለችው ባለው ዴሞክራሲያዊ ፌዴራላዊ ስርዓት ላይ የተለያዩ ኃሳቦች ይሰነዘራሉ፡፡ በአንድ በኩል ስርዓቱን የሚያብጠለጥሉ ኃይሎች በተለይም በፖለቲካ ፓርቲና በጋዜጠኝነት ስም የታቀፉ አንዳንድ ወገኖች በስርዓቱ ላይ ‹‹ድሮም ብለን ነበር›› የሚል ይዘት ያላቸው መረጃዎችን ያሰራጫሉ፡፡ በሌላ በኩል የፌደራሊዝም ስርዓቱ ግጭቶችንና ቅራኔዎችን አስወግዶ ሀገሪቱ ሁለንተናዊና ፈጣን ለውጥ እንድታስመዘግብ ያስቻለ ፍቱን መድሃኒት እንጂ የግጭት መንስኤ እንዳልሆነ የሚከራከሩ በርካታ ወገኖች አሉ፡፡

ስርዓቱን የሚተቹ አካላት በአንዳንድ አካባቢዎች አልፎ አልፎ ግጭቶች መከሰታቸውንና በተለይም በቅርቡ በኦሮሚያ እና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ያጋጠመውን ወቅታዊ ችግር አስረጅ በማድረግ ጽፈዋል፤ ብዙ ብለዋል፡፡ እውን ኢትዮጵያ የምትከተለው የፌደራሊዝም ስርዓት የግጭት መንስኤ ወይስ ግጭቶችንና ቅራኔዎችን ያስወገደ ስርአት ነዉ የሚለውን ጥያቄ በማስረጃ አስደግፎ መመለስና ሚዛናዊ አቋም መያዝ ይገባልና ትንሽ ልበል፡፡

ኢትዮጵያ የፌደራሊዝም ስርዓት ለመከተል ተጨባጭ ምክንያቶች አሏት፡፡ ባለፉት ስርአቶች በኢትዮጵያ ተንሰራፍቶ የነበረው የመደብና የብሄር ጭቆና የተለያዩ ቅራኔዎችን ፈጥሮ ሀገሪቱን ለእርበርስ ግጭቶች ዳርጓት ቆይቷል፡፡ ኢህአዴግ ስልጣን ሲይዝ 17 የሚጠጉ የታጠቁ ድርጅቶች መኖራቸው በወቅቱ የሀገራችን አንድነት ምን ያህል በአደገኛ ሁኔታ ውስጥ እንደነበር ለመገንዘብ ያስችላል፡፡

በወቅቱ ኢትዮጵያን ለብተና ዳርጓት የነበረውን በጭቆና ላይ የተመሰረተ አሃዳዊ የመንግስት አወቃቀር ማስቀጠል የማይታሰብ ነበርና ሁሉም ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች አንድነታቸውን ጠብቀው እንዲቀጥሉ የሚያስችል አዲስ አወቃቀር መከተል አማራጭ አልነበረውም፡፡ እናም ለመገንጠል አኮብኩበው የነበሩ ኃይሎችን ጨምሮ ለዘመናት የቀጠለውን የህዝቦች ጥያቄ መልስ ለመስጠት ህገ መንግስታዊ የፌደራሊዝም ስርዓት ሁነኛ መፍትሄ ሆነ፡፡

በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ባለፉት ስርዓቶች ውስጥ በደረሰባቸው ጭቆና ምክንያት ኢትዮጵያዊነታቸውን እንዲጠሉ ሆነው የነበሩ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መብታቸው በህገ መንግስታዊ መንገድ ሳይሸራረፍ እንዲከበር በመደረጉ ለሀገራዊ አንድነታቸው ጠበቃ የሚቆሙ ሆነዋል፡፡ ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር ብቻ ሳይሆን በፌደራል ደረጃም ፍትሃዊና ተመጣጣኝ ውክልና ማግኘት ችለዋል፡፡ በዚህ ሂደት ቋንቋቸውን፣ ባህላቸውንና ሌሎች እሴቶቻቸውን የሚያሳድጉበት መብት ተጎናጽፈዋል፡፡ አካባቢያቸውን እንዲያለሙም ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ በታሪኳ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በፈጣን ሁለንተናዊ ለውጥ ውስጥ የመገኘቷና ፈጣን እድገት ከሚያስመዝግቡ ሀገሮች ተርታ የመሰለፏ ምስጢር የተከተለችው የፌደራሊዝም ስርዓት ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዘቦች በአገራቸው ላይ በነፃነት የመስራት፣ ሃብት የማፍራትና አገራቸውን የመለወጥ ነፃነት በመጎናፀፋቸው ነው፡፡

ባለፉት 13 ዓመታት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በ10ነጥብ5 በመቶ ማሳደግ ተችሏል፡፡ እድገቱ በየደረጃው ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደረገ ስለመሆኑ የነፍስ ወከፍ አማካይ ገቢ በማሳደግና እና ድህነትን በመቀነስ የተጫወተውን ሚና ማየት ይቻላል፡፡ ከ12 ዓመታት በፊት ከፍጹም ድህነት ወለል በታች ይኖር የነበረው ህዝብ 38ነጥብ7 በመቶ ሲሆን በ2009 ዓም መጨረሻ ወደ 23 በመቶ ዝቅ ብሏል፡፡ የነፍስ ወከፍ ገቢ በአማካይ የ13ነጥብ8 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ በ2002 ዓም ከነበረበት የ373 የአሜሪካን ዶላር በ2008 በዓም ወደ 794 አሜሪካን ዶላር ከፍ ብሏል፡፡

ፈጣን ዕድገቱ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰተውን ድርቅ የከፉ ጉዳት ሳያደርስ በራስ አቅም ለመከላከል አስችሏል፡፡ በ2007/08 ዓ.ም በ30 ዓመታት ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ከባድ ድርቅ አጋጥሞ የነበረ ቢሆንም  ድርቁን መቋቋም እንዲቻል አድርጓል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በ2009 ዓ.ም ያጋጠመውን ድርቅም መቋቋም ተችሏል፡፡ ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት በድርቅ ምክንያት ዜጎች እንደ ቅጠል ይረግፉባት በነበረችው ሀገር ዛሬ የሚከሰተውን ድርቅ በሰዎች ብቻም ሳይሆን በእንሳሳት ላይም የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ የሚያደርግ አቅም ተፈጥሯል፡፡

በመሰረተ ልማት መስክ በመንገድ፣ በባቡር፣ በአየር ትራንስርት እንዲሁም በቴሌኮም አመርቂ ስኬት ማስመዝገብ ተችሏል፡፡ የትራንስፖርት መስፋፋት ደግሞ የሰዎችን ሁለንተናዊ ግንኙነት በማቀላጠፍ ፈጣን ልማቱን ይበልጥ እንዲጠናከር አስችሏል፡፡ በኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ ለማድረግ የተከናወኑ ስራዎችም በተመሳሳይ መልኩ አንጸባራቂ ስኬቶች ናቸው፡፡ የሀገሪቱን የኃይል አቅርቦት በብዙ እጥፍ ማሳደግ የተቻለ ሲሆን ሀገራች እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በራሷ አቅም መገንባት ጀምራለች፡፡ ትናንት በድንቁርና እና በረሃብ ትታወቅ የነበረችው ሀገር ያንን አስከፊ ዘመን ተሻግራ አኩሪ የልማት ስራዎችን በማከናወን ላይ ነች፡፡ ጤና፣ ትምህርት እንዲሁም የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲም ለዓለም አርአያ የሆኑ ከፍተኛ ስኬቶች የተመዘገቡባቸው መስኮች ናቸው፡፡

ከላይ የተጠቀሱ አመርቂ ስኬቶች የተመዘገቡት በዋናነት በሀገራችን አስተማማኝ ሰላም በመስፈኑ ነው፡፡ የአስተማማኙ ሰላም መስፈን ምንጭ ደግሞ በህዝቦች መፈቃቀድ የተመሰረተው ዴሞክራሲያዊ ፌደራላዊ ስርዓት ነው፡፡

በማንኛውንም የዕድገት ሂደት መልካም አጋጣሚዎች እንዳሉ ሁሉ ተግዳሮቶችም አሉ፡፡ በሀገሪቱ ተከስቶ የነበረውን የመበታተን አደጋ ያስቀረው የፌደራሊዝም ስርዓት በርካታ ችግሮችን እየፈታ እዚህ የደረሰ ቢሆንም ተግዳሮቶች ሊያጋጥሙት እንደሚችሉ እሙን ነው፡፡ ዋናው ጉዳይ ችግሮች የሚፈቱበት አግባብ ምን መሆን አለበት የሚለው ነው፡፡ በአንድ በኩል ማንኛውንም ውሳኔዎች የህዝቡን ፍላጎት ማእከል ያደረጉ እንዲሆኑ ማድረግ ሲሆን ለችግሮቹ በሕገ መንግስቱ መሰረት መፍትሄ መስጠትም ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው፡፡

አልፎ አልፎ እያጋጠሙ ያሉ ግጭቶች መከሰት ያልነበረባቸውና ዳግም እንዳይከሰቱ ተገቢውን ትምህርት የሚወሰድባቸው ቢሆንም ችግሮቹ በማንኛውም ታዳጊ ስርዓት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ናቸው፡፡ የወሰን እና የማንነት ጥያቄዎችን የፌደራል ስርዓቱ የፈጠራቸው ችግሮች አስመስሎ የሚደረገው  ዘመቻ ሌላ ተልዕኮ ያለው ነው፡፡

ሁሌም ነገሮችን በሚዛናዊ ዕይታ ማየት የተሳናቸው ኃይሎች ሶስት የጋራ ባህሪዎች ይገልጿቸዋል፡፡ አንደኛው ከ1983 ዓ.ም በፊት በየአካባቢው የነበሩ ግጭቶችን ይክዳሉ፡፡ ሀገሪቱን ለብተና ዳርጓት የነበረውን ጨቋኝ አሃዳዊ ስርዓት በማንቆለጳጰስ ትናንት በህዝቦች ላይ ያደረሰውን በደል ማንሳት አይፈልጉም፡፡ ሁለተኛዉ የፌደራል ስርዓቱ ያስገኛቸውን መልካም ስኬቶች በማጥላላት አልፎ አልፎ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ብቻ በማጉላትና በማውገርገር ላይ የተጠመዱ ናቸው፡፡ በሶስተኛ ደረጃ ይህን ስርዓት ከመተቸት የዘለለ አማራጭ የመንግስት አወቃቀር ሲያቀርቡ አይታዩም፡፡


የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በመፈቃቀድ ላይ የመሰረቱት ዴሞክራሲያዊ ፌዴራላዊ ስርዓት እኩል የመልማትና አንድነታቸውን የማጠናከር ዕድል አጎናጽፏቸዋል፡፡ ስርዓቱ ገና አዳጊ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሚያጋጥሙ አንዳንድ ችግሮች ለቀጣይ ትምህርት የሚሆኑ ስርዓቱንም የሚያጠናክሩ ናቸው እንጂ የመጣንበትን መንገድ አስትተው ወደኋላ የሚቀለብሱ አይደሉም፡፡ እናም ኮሽ ባለ ቁጥር የችግሩን መንስኤ በአግባቡ አይቶ ምክንያታዊ ሃሳብ ከመሰንዘር ይልቅ በጭፍን ጥላቻ የፌደራል ስርዓቱ ላይ የሚደረገው ዘመቻ እውነታው በብዙሃኑ ህዝብ ዘንድ ያለ በመሆኑ ትዝብት ውስጥ ከመክተት ባለፈ ፋይዳ የሌለውና ቀደም ባሉ ዓመታት የትምክህትና የጥበት ኃይሎች በስርዓቱ ሲያደረጉት የነበረውን የማጥላላት ዘመቻ ለማጠናከር የሚቀርብ መሆኑ የሚረጋግጥ ነው፡፡ የፌደራል ስርዓቱ የአብሮነት ዋስትናና የስኬቶቻችን ምንጭ እንጂ የግጭት መንስኤ አይደለም፡፡

No comments:

Post a Comment