EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Thursday 28 September 2017

የባለድርሻዎች ውይይት - ለትምህርት ጥራት


(በኤፊ ሰውነት)
የተለያዩ አካላት ትምህርት ዓለምን የመለወጥ አቅም ያለው መሳሪያ እንደሆነ በተለያየ አጋጣሚ ሲናገሩ ይሰማል፡፡ በህዝቦችና በአገራት መካከል የስልጣኔ ልዩነት እንዲፈጠር ያደረገውም እያንዳንዱ ግለሰብም ሆነ አገር ለትምህርት በሚሰጠው ትኩረት፤ ትምህርትን ለማስፋፋትና በትምህርት ለማነፅ ባለው ቁርጠኝነት መሆኑን የዓለም ነባራዊ ሁኔታ ያሳያል፡፡ ዓለም ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪነታቸው የሚነገርላቸው የአገር መሪዎችም በተለያየ አጋጣሚ ለህዝባቸው ንግግር ሲያደርጉ የትምህርትን አስፈላጊነት ሳይጠቅሱት አላለፉም፡፡

የነጻነት መሪው ኔልሰን ማንዴላ “ትምህርት አለምን ለመቀየር ከሚያስችሉ መሳሪያዎች ሁሉ ከፍተኛውን አቅም ያለው ነው፡፡” በማለት ከላይ ያነሳሁትን ሃሳብ ቃል በቃል ገልፀውታል፡፡ በተመሳሳይ ዓለም ለህዝብ ባላቸው ክብርና በነፃነት ታጋይነታቸው ከሚያከብራቸው ህንዳዊው ማህተም ጋንዲ የማይዘነጉ ንግግሮች ውስጥ የትምህርትን አስፈላጊነት የገለፁበት ተጠቃሽ ነው፡፡ “ፍፁም የሆነ ሰላም ለዓለም እንዲሆን የምንሻ ከሆነ ህፃናትን በሚገባ በማስተማር መጀመር አለብን፡፡” በሚል ትምህርት በእርግጥም ዓለምን የመለወጥ ኃይል ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ጓድ መለስ ዜናዊም በአንድ ወቅት ባደረገው ንግግር “የድህነት ተራራ የሚናደው በእውቀት ጥይት ነው፡፡ በማለት የትምህርትን ሃያልነት አመልክቷል፡፡ በአጠቃላይ ትምህርት የሁሉ ነገር መሰረት መሆኑን ዓለም የሚስማማበት ጉዳይ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡

ኢህአዴግ አገራችን ከድህነትና ከኋላ ቀርነት መላቀቅ የምትችለው በትምህርት የዳበረ ማህበረሰብ በመገንባት እንደሆነ በፅኑ የሚያምን ድርጅት ነው፡፡ በዚህም አገራችን ኢትዮጵያ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንግስት በተመራችባቸው ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ውጤታማ የሆነ የትምህርት ስርዓት በመዘርጋት በቀደሙት ስርዓቶች የቅንጦትና ጥቂቶችን ብቻ ባለ እድል ያደርግ የነበረውን የትምህርት ስርዓት ከመሰረቱ በመቀየር ለሁሉም ዜጋ በፍትሃዊነት የሚደርስበትን ሁኔታን ማመቻቸት ችሏል፡፡ ይህም ዛሬ ላይ እንደአገር ለተመዘገበው ሁለንተናዊ እድገት መሰረት ለመሆን በቅቷል፡፡ ጥቂት ዓመታትን ወደ ኋላ ተመልሰን በአገራችን የትምህርት ልማት ዘርፍ የተመዘገበውን ውጤት ብቻ ብንመለከት ኢህአዴግ የሚመራው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት ለትምህርት የሰጠውን ትኩረት ለመመዘን በቂ ነው፡፡

አሮጌውን ዓመት ሸኝተን አዲሱን ዓመት ከተቀበልን ውለን አድረናል፡፡ በአገራችን ባህል አዲስ ዓመት የዘመን መለወጫን ለማክበር ከሚደረገው ሽርጉድ ባልተናነስ ቤተሰብ በትምህርት ጉዳይ ውይይት የሚያደርግበት፤ ደብተሩ፣ እስክርቢቶው፣ የደንብ ልብስ የሚዘጋጅበት፤ መምህራን የአመት እቅዳቸውን የሚያወጡበት፣ ተማሪው ዓመቱን እንዴት በስኬት እንደሚያጠናቅቅ በልበ ሙሉነት ለቤተሰቡ ቃል የሚገባበት፤ በአጠቃላይ ለተማሪውም፣ ለወላጅም ለመምህራንም የዝግጅት ምዕራፍ ጊዜ ነው፡፡ በተመሳሳይ ሁሉም የትምህርት ባለድርሻ አካላት ስለ ነገ ተቀራርበው የሚወያዩበት፤ ትውልድ የሚቀረፅበት የእውቀት ማዕድ የሚታፈስበት ትምህርት ቤትን በጋራ ለማቅናት  የመማር ማስተማር ሂደቱንም ለማሳለጥ የሚያስችል ሁኔታን ለመፍጠር የሚመካከሩበት ወር መሆን ከጀመረም ውሎ አድራል፡፡

ሁሉም እንደሚገነዘበው በትምህርት ልማት ዘርፍ ለተመዘገበው ስኬት የትምህርት ባለድርሻ አካላት ሚና የላቀ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንትም ለትምህርት ልማት ስኬት መሰረት የሆኑ መምህራንና ወላጆች በአንድ ተሰባስበው የትምህርት ልማት ስራቸውን በማጠናከር የትምህርት ዘመኑን ውጤታማ ማድረግ ስለሚቻልበት ሁኔታ መክረዋል፡፡ አመቱ ጥራት ያለው ትምህርት ለሁሉም የሚሰጥበት እንዲሆን የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት፣ የትምህርት ቤቶችን ችግር አቅማቸውን አስተባብረው ለመፍታት፣ ባለፈው አመት የታዩ ጉድለቶችን ለማረም ቃል የገቡበት ነው ውይይቱ፡፡

እንደ ድህነት አንገት የሚያስደፋ ምንም ነገር እንደሌለ በተደጋጋሚ ይገለፃል፤ ከድህነት የተላቀቀ ህዝብና አገር ማየት ደግሞ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ምኞት መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ በመሆኑም ሁሉም ዜጋ የትምህርትን ጉዳይ በልዩ ሁኔታ በማየትና በመደገፍ ከአደጋም ጭምር በመጠበቅ የነገዋን የበለፀገችና ባለብሩህ ተስፋ አገር የመፍጠር ዓላማውን ለማሳካት የበኩሉን አስተዋፅኦ ማድረግ ከሁሉም የሚጠበቅ ይሆናል፡፡ ከሰሞኑ እየተደረገ ያለው ውይይትም ዓላማውን ማሳካት የሚችለው የትምህርት ተቋማትን ከስኬታማነት ሊያደናቅፉ የሚችሉ አዋኪ ነገሮችን በተባባረ ክንድ በማስወገድና ሰላማዊ የሆነ የመማር ማስተማር ሁኔታ እንዲፈጠር በመስራት ብቻ ነው፡፡

መምህራን አገሩን የሚወድ ለአገሩና ለቤተሰቡ የሚጠቅም ትውልድ በመገንባት ሂደት ውስጥ እያንዳንዱን የትምህርት ጊዜ በውጤታማነት በመጠቀም የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡ የትምህርት ልማት ስራ መንግስት ብቻውን የሚሰራው ስራ አለመሆኑ ይታወቃል፡፡ ትምህርት ቤቶች ያለወላጆች፣ መምህራንና ተማሪዎች ውጤታማ ተሳትፎ ባዶ መሆናቸው ግልፅ ነው፡፡ በመሆኑም ወላጆች ልጆቻቸውን በስነምግባር እንዲታነፁ፣ ተወዳዳሪና ነገን መመልከት የሚችሉ እንዲሆኑ በማድረግ በኩል እንዲሁም የትምህርት ተቋማትንም ለመማር ማስተማር ሂደት ምቹ እንዲሆኑ በማገዝ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡

በተመሳሳይ መምህራንም ራሳቸውን በስነምግባር በማነፅ ለተማሪዎቻቸው በተግባር አርዓያ መሆን አለባቸው፡፡ ለስራቸውም በቂ ዝግጅት በማድረግ አገራዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡ ተማሪዎችም የትምህርት ቤቱን ሁለንተናዊ ገፅታ በመቀየር ለመማር ማስተማር ሂደት ምቹ እንዲሆን በመስራትና ሰላማዊ የሆነ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲፈጠር መንግሰት በሚያደርገው እንቅስቃሴ ላይ በግንባር ቀደምትነት በመሳተፍ ነገ አገር ተረካቢ መሆናቸውን ከልብ በመገንዘብ ለራሳቸው፣ ለቤተሰቦቻቸውና ለአገር የሚጠቅሙ ዜጎች እንዲሆኑ ኃላፊነት በተሞላበት መንፈስ መንቀሳቀስ የሚገባቸው ይሆናል፡፡ ራሳቸውን ከአልባሌ ቦታዎችና ከሱስ መጠበቅም ተማሪዎችን ግድ የሚላቸው የወቅቱ ፈተና ነው፡፡


በተለያየ አጋጣሚ እንደሚስተዋለው አፍራሽ ኃይሎች ትምህርት ቤቶች ላይ ያነጣጠረ አፍራሽ መልእክት በማሰራጨት ሲጠመዱ ይሰተዋላል፡፡ አለመረጋጋቶች ሲከሰቱም ትምህርት ቤቶች የአፍራሽ ኃይሉ ዓይን የሚያርፍባቸው ሆነው ይገኛሉ፡፡ ይህ መቼም ቢሆን በአገራችን ሰላማዊ የሆነ ሁኔት እንዲፈጠር የማይሹና ትርምስ እንዲፈጠር የሚጥሩ አካላት አገራችንን ወደ ቁልቁለት ለመወርወር የሚያደርጉት አሳፋሪ ድርጊት በመሆኑ የትምህርት ባለድርሻ አካላት በአንድነት ሊያወግዙት ይገባል፡፡ ተማሪዎችም ሁሌም ቢሆን ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ የሚፈታ፤ የወደፊቱን መመልከት የሚችል ትውልድ አካል በመሆን ወደ ስኬት ከሚወስዳቸው መንገድ ላይ የሚቆመውን ኃይል መመከት ይኖርባቸዋል፡፡ በመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ ችግሮች ሲያጋጥሙ ባለድርሻ አካላተት ሰሞኑን እንዳደረጉት በውይይት በመፍታት የትምህርት ዘመኑን የተቃና ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

No comments:

Post a Comment