EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Thursday 21 September 2017

በውሃው ያስተሳሰረን አባይ በልማቱም ያቆራኘናል!

(በውብዓለም ፋንታዬ)
በአለማችን ከ165 በላይ ዋና ዋና ወንዞች ይገኛሉ፡፡ ከነዚህ መካከል በርዝመት የናይል (አባይ) ወንዝን የሚስተካከል የለም፡፡ በሚይዘው የውሃ መጠን ቀዳሚ ደረጃ የያዘውን የአማዞን ወንዝን እንኳን ናይል በበርካታ ኪሎ ሜትሮች ይበልጠዋል፡፡ ይህ ወንዝ ስያሜውን ‹ኒሎስ› ከሚለው የግሪክ ቃል ያገኘ ሲሆን፤ በአረብኛው ባህር አል ኒል ተብሎ ይጠራል፡፡ ናይል ከመነሻው እስከ መዳረሻው ድረስ ከ6ሺህ 600 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀትን ያካልላል፡፡

ናይል በተፋሰሱ 11 ሀገራትን የሚያቅፍና ከ300 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑት የተፋሰሱ ሀገራት ህዝቦች የጋራ ንብረትና የሚያስተሳስራቸው የተፈጥሮ ኃብት ነው፡፡ ከዓመት እስከ ዓመት መጓዝ የማይሰለቸው ይህ ወንዝ ከመዳረሻው ሜዲትራኒያን ባህር ለመድረስ የሶስት ወራት ጊዜን የሚፈጅበት ሲሆን ወንዙ የአህጉሪቱ አንድ አስርኛውን የቆዳ ሽፋን ይይዛል፡፡ ይህ አለም አቀፍ ወንዝ በበርካታ የተፈጥሮ ኃብቶች የታደለ መሆኑም ይነገርለታል፡፡
ስመ ገናናው ናይል (አባይ) ከሱዳንና ከግብጽ በስተቀር ለበርካታ የተፋሰሱ ሀገራት ህዝቦች እዚህ ግባ የሚባል ጥቅም ሳይሰጥ ቆይቷል፡፡ በውሃው አቅራቢያ የሚኖሩት ህዝቦች አብዛኞቹ በድህነት ውስጥ የሚማቅቁ ናቸው፡፡
የተለያዩ የአለም ሀገራት በሀገር ውስጥ የሚመነጩ ወንዞችንም ሆኑ ድንበር ተሻጋሪ የሆኑ አለም አቀፍ ወንዞችን በጋራም ሆነ በተናጠል በማልማት ጥቅም ላይ በማዋል አያሌ የኢኮኖሚ ትሩፋቶችን ያገኛሉ፡፡ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ቱርክ፣ ብራዚል፣ ቻይናና ህንድ ባስመዘገቡት ፈጣን የኢኮኖሚ ለውጥ በተለይም የመስኖና የኃይል ማመንጫ ግድቦችን ጥቅም ላይ ማዋላቸው ትልቅ ሚና አለው፡፡ በናይል ወንዝ በመጨረሻ የምትጎበኘው ግብጽም በዚሁ ማዕቀፍ ውስጥ የምትመደብ ነች፡፡ በተቃራኒው ኢትዮጵያን ጨምሮ አብዛኞቹ የናይል ተፋሰስ ሀገራት ህዝቦች ግን በውሃ ኃብታቸው ሳይጠቀሙበት ቆይተዋል፡፡
ወንዙ ካለው የውሃ አቅምና ከሚያካልለው ርቀት አንጻር ቢለማ የተፋሰሱን ነዋሪዎች ከድህነት ማላቀቅ የሚችል ቢሆንም ከግብጽና በከፊል ከሱዳን በስተቀር ሌሎች በአቅም ውስንነት፣ በታችኛው ተፋሰስ ሃገራት ጫናና በፖለቲካ መሪዎቻቸው ቁርጠኝነት ማነስ የተነሳ በወንዙ ሳይጠቀሙ ቆይተዋል፡፡
ከተፋሰሱ ሀገራት ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ያላትና ለወንዙ የአንበሳውን ድርሻ (የውሃውን 85 በመቶ) የምታበረክተው ሀገራችን በ2003 ዓ.ም የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጀመርን ስታበስር ከግድቡ የምታገኘው ቀጥተኛ ጥቅም የመኖሩን ያክል የተፋሰሱን አገራት የጋራ ተጠቃሚነትን እንደሚያረጋግጥ በማመን ጭምር ነው፡፡
የግብጽ መሪ የነበረው ገማል አብዱል ናስር በ1970 የአስዋን ግድብን ሲያስገነባ ግብጽን ለማዘመንና “የአፍሪካ ጃፓን” የማድረግ ዓላማ አንግቦ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የሕዳሴው ግድብም በኢትዮጵያ ያለውን የኃይል አቅርቦትን ከማሻሻል ጀምሮ ለወጠነቻቸው የኢኮኖሚ ግቦች መሳካት ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዳለው ኦል አፍሪካ ሪፖርት የተሰኘው ድረ-ገጽ መስከረም 2017 ባሰፈረው ጽሁፍ አትቷል፡፡
በተመድ የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም ውስጥ ያገለገሉና በናይል ዙሪያ የትንታኔ ጽሑፎችን በማሰናዳት የሚታወቁት ፕሮፌሰር ሰይፉላዚዝ ሚለስ “ኢትዮጵያ፡ የናይል ውሃ ዲፕሎማሲና የሕዳሴው ግድብ (“Ethiopia: Nile waters diplomacy and the Renaissance dam”) በሚል ርዕስ ባሰፈሩት ጽሁፍ ለቻይናና ለህንድ የኢኮኖሚ እድገት ግድቦች ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውን ጠቅሰው ኢትዮጵያም ለምታልመው እድገት የታላቁ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎች ግድቦች እንደሚያስፈልጓት አስቀምጠዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውሃ ኃብት ይዛ ድሃ መባሏ ትርጉም የማይሰጥ መሆኑን ጠንካራ ትችት ያሰፈረው አፍሪካ ሜትሮ የተባለው ድረ ገጽ በበኩሉ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት የሕዳሴ ግድብን መገንባት መጀመራቸው ከሀገሪቱ አልፎ ለቀጠናው የሚተርፍ የለውጥ ማዕበል እንደሚያቀጣጥል ይጠቅሳል፡፡
የሕዳሴው ግድብ ለኢትዮጵያ ከሚሰጠው ጥቅም በተጨማሪ ለተፋሰሱ ግርጌ ሀገራትም ሆነ ለሌሎች ሀገራት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንደሚያስገኝ ይታመናል፡፡ ግድቡ የሱዳንና የግብጽ የኃይል ማመንጫና የመስኖ ግድቦችን ከጎርፍና በደለል እንደይሞሉ በመከላከል የግድቦቹን እድሜ እንደሚያራዝም ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ በየዓመቱ የሚከሰተው ደለል ለምርት ብክነትና ደለሉን ለማስወገድ ሀገራቱ ለከፍተኛ ወጪ የሚዳርግ ክስተት ሲሆን ችግሩ በሱዳን የሚገኙት የሮዘሪ እና ሴነር ግድቦች አቅም እንዲቀንስ አድርጓል፡፡ ችግሩን ለመፍታትም የሮዘሪ ግድብ በ10 ሜትር ከፍታ እንዲጨመር መደረጉን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በተመሳሳይ የደለል ችግር የአስዋን ግድብ እድሜን ሊያሳጥር እንደሚችልና በየዓመቱ ለ160 ሚሊየን ቶን የደለል ክምችት በግድቡ እንደሚመዘገብ መረጃዎች ይጠቅሳሉ፡፡ የደለሉ 90 በመቶ ደግሞ በአባይ ወንዝ ምክንያት የሚፈጠር ነው፡፡ አፍሪካ ሜትሮ ጥናቶችን ዋቢ በማድረግ “ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ- የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ሽልማት (Grand Ethiopian Renaissance Dam – a Reward to Downstream Countries”) በሚል ርዕስ ባሳፈረው መረጃ እንዳስቀመጠው ግድቡ በዓመት 70 ኪዩቢክ ሜትር ውሃ በዚህ ምክንያት እያጣ እንደሚገኝና ይህ ደለል የግድቡን እድሜ በእጅጉ የሚያሳጥር መሆኑን ይጠቅሳል፡፡ የሕዳሴ ግድብ የደለል ስጋትን በማስወገድ የአስዋን ግድብ እድሜን በመቶዎች ለሚቆጠሩ ተጨማሪ ዓመታት እንዲረዝም የሚያደርግም መሆኑን ያስቀምጣል፡፡
በውሃ ኃብት ዙሪያ መረጃዎችን በየጊዜው የሚያወጣው aquapedia.waterdiplomacy.org የተሰኘው ድረ ገጽ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በወንዙ ምክንያት በጎርፍ የሚጠቃውን መሬት በ2/3ኛ እንደሚቀንስ ያስቀምጣል፡፡ በተለይም በካርቱም አካባቢ የሚከሰተው ጎርፍ እንደሚቀንስና በወንዙ ዳር በሚገኘው አካባቢዎች ላይ የሚከሰተው ጎርፍ ሙሉ በሙሉ እንደሚወገድ አመልክቷል፡፡ ይህ ለግብርና ልማት የሚውለውን መሬት በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችል ከመሆኑም በላይ አመቱን ሙሉ ወቅቱን የጠበቀ የውሃ መጠን እንዲያገኝ ያደርጋል ማለት ነው፡፡
መረጃው እ.ኤ.አ በ2013 በሱዳን ከ300ሺህ በላይ ህዝብን ለጉዳት የዳረገና የ25ሺህ ቤቶች ውድመት ያስከተለውን አስከፊ የጎርፍ አደጋ በማስታወስ፤ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ ተመሳሳይ የጎርፍ አደጋ ሊከሰት እንደሚችልና የሕዳሴው ግድብ ሱዳንን ከዚህ አደጋ ሊታደጋት የሚችል መሆኑን  አስፍሯል፡፡

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የሚያበረክተው ሌላኛው ጠቀሜታ በትነት (evaporation) ምክንያት የሚባክነውን የናይልን ወንዝ ውሃ ለመቆጠብ የሚረዳ መሆኑ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ካለው የአየር ሁኔታ ጋር በተያያዘ እንዲሁም ወንዙም የሚፈስበት አብዛኛው ክፍል ጠባብና ሸለቋማ ስለሆነ የሚከሰተው የትነት መጠን ከሱዳንና ከግብጽ በእጅጉ ያነሰ ይሆናል፡፡

በአስዋን ግድብ ላይ የተገነባው ሰው ሰራሽ የግድቡ ውሃ ማቆሪያ የሆነው የናስር ሃይቅ ውስጥ ከሚከማቸው ውሃ ውስጥ 12 በመቶ በትነት ይባክናል፡፡ ይህንን እውነታ በአሌክሳንዳሪያ ዩኒቨርሲቲ የሃይድሮሎጂ ምሁር የሆኑት ፕሮፌሰር ሀተም አዋድም ይጋራሉ፡፡ በተለይም በነሓሴ መጨረሻና መስከረም ወር መጀመሪያ አካባቢ ወደ ሃይቁ የሚገባው ከፍተኛ መጠን ያለው ውሃ ለትነት እንደሚዳረግና ውሃውን በሕዳሴ ግድብ ማቆር መፍትሄ እንደሚሆን ይጠቅሳሉ፡፡ ይህም አስዋን ግድብ የሚደርሰውን የውሃ መጠን በየዓመቱ በ5በመቶ እንዲጨምር ያደርጋል፡፡ በተጨማሪም ግድቡ በደረቃማ ወቅት ላይ የውሃውን አነስተኛ የፍሰት መጠንን በማስተካከል ካርቱም የሚደርሰውን ውሃ በአምስት እጥፍ እንዲጨምር ይረዳል፡፡

የግድቡ ሌላኛው ጠቀሜታ በቀጠናው የኢኮኖሚ ትስስርን ለመፍጠርና ለማጠናከር ዓይነተኛ ሚና የሚጫወት ግድብ ነው፡፡ ግድቡ ኃይል ማመንጨት ሲጀምር ጅቡቲ፣ ሱዳንና ኬንያን ጨምሮ ለተለያዩ ሀገራት በሽያጭ መልክ ኃይል እንዲያገኙ ያስችላቸዋል፡፡ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እንዲኖር በማድረግ በሀገራት ኢንዳስትሪዎች እንዲስፋፉና የኢኮኖሚ እድገትና ለውጥ እንዲመጣ ያስችላል፡፡ በአጠቃላይ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አፍሪካውያን ተያይዘው ወደ ብልጽግናው ማማ የሚያደርጉትን ጥረት የሚያግዝ ግዙፍ የእድገት ሞተር ነው ማለት ይቻላል፡፡

ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመሰረተ ድንጋይ ሲጥሉ “የወንዙ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት የግድቡን ግንባታ ወጪ አስተዋጽኦ ማድረግ ነበረባቸው” ያሉትም ግድቡ ለታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት የሚሰጠውን ከላይ የተጠቀሱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡

No comments:

Post a Comment