EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Wednesday 9 August 2017

ግብር የዜግነት ግዴታ ብቻ ሳይሆን ባህልም መሆን አለበት!

(በወጋገን አማኑዔል)         
በተደጋጋሚ እንደሚገለፀው ከግብር የሚሰበሰብ ገቢ መሰረት ልማት መገንባትን ጨምሮ የአንድ ሀገር ዜጎችን ሁለንተናዊ ፍላጎት ለማሟላትና ሀገራዊ እድገትን ለማፋጠን ወሳኝ ነው፡፡ በአውሮፓና በአሜሪካም ሆነ በአጭር አመታት ፈጣን እድገት በማስመዝገብ ወደበለፀጉ ሀገራት በተሸጋገሩ እንደ ደቡብ ኮሪያና ሲንጋፓር ባሉ የኢስያ ሀገራት ግብርን በወቅቱ መክፈል የዜግነት ግዴታ ብቻ ሳይሆን ባህላቸው መሆኑን እንመለከታለን፡፡

የሀገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ ስናየው ግን ከግብር የሚሰበሰበው ገቢ በጣም ትንሽ የሚባልና ለኢኮኖሚው የሚያደርገው አስተዋፆ ውስን መሆኑ ብቻ ሳይሆን ግብር በመክፈል ረገድ ሰፋ ያለ የአመለካከት ዝንፈት የሚንፀባረቅበት ነው፡፡
እንደሚታወቀው መንግስት ተቀጣሪ ሰራተኞች ጉልበታቸውንና እውቀታቸውን ሸጠው ከሚያገኙት ክፍያ የተወሰነው ግብር በአግባቡና በወቅቱ ይሰበስባል፡፡ ከአምራቾችና ሻጮች የሚሰበሰበው ግብር ግን በየወቅቱ የንትርክ አጀንዳ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ እነዚህ ወገኖች ከሚያገኙት ትርፍ ላይ ተተምኖ የሚጣለውን የግብር ምጣኔ በዜግነት ግዴታነት ተቀብሎ መክፈል ላይ እንዲሁም በግብር ተቀባዩም በኩል በአግባቡና በወቅቱ በመሰብሰብ ረገድ ያሉት ክፍተቶች በርካታ ናቸው፡፡
በእኔ እይታ የታክስ አሰባሰብ ስርዓቱ ካለበት ኋላቀር አሰራር መላቀቅ ይጠበቅበታል፡፡ የካሽ ሬጅስተር ማሽኖች በሰፋትና በተመጣጣኝ ዋጋ ለንግዱ ማህበረሰብ ተደራሽ መሆን አለባቸው፡፡ ያደገው አለምና በማደግ ላይ ያሉም ሆነው በዘርፉ ከእኛ የተሻለ አፈፃፀም ያላቸውን ሀገራት ተሞክሮ በማጥናት ወደ ዘመነው አሰራር መሸጋገር አለብን፡፡
በተመሳሳይ አሁን ግብር በመክፈል ረገድ እየታየ ያለውን የአመለካከት ችግር በመቅረፍ ግብር የመክፈል ባህላችን ለማሳደግ መስራት ይኖርብናል፡፡ “ደረሰኝ ትፈልጋለህ ወይ?” እና “እባክህ ያለ ደረሰኝ ሽጥልኝ” እየተባለ ከሚጠየቅበት የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባር ውስጥ ፈጥኖ መውጣት ይገባል፡፡  ይህ ደግሞ ሰፊ የአስተምህሮ ስራዎችን በተቀናጀ መልኩ መፈፀምን ይጠይቃል፡፡
በአጠቃላይ ነጋዴው ክፈል እየተባለ ያለው ዜጎች ለመንግስት እንዲሰጥላቸው እሱ ጋር ያስቀመጡትን ገንዘብ በመሆኑ ለግብር የሚያወጣውን ብር የራሱ አድርጎ መቁጠር አይገባውም፡፡ ዜጎችም ለነጋዴው ብሩን የሚሰጡት የወል ጥቅማቸው በመንግስት በኩል እንዲፈፀምላቸው በመሆኑ እንደ ብክነት መቁጠር የለባቸውም፡፡
ይህን ተግባር ለመፈፀም የተቋቋመው የመንግስት አካልም ስራው በጥድፊያና በግምት የሚሰራ ሳይሆን በእውቀት፣ በመረጃና በመተማመን መሰራት የሚገባው መሆኑን ተረድቶ አሰራሩን ቀጣይነት ባለው ሂደት ለማዘመን መዘጋጀት፤ ይህንንም በተግባር ማሳየት ይኖርበታል እላለሁ፡፡

ግብር መክፈል የዜግነት ግዴታ ብቻ ሳይሆን ባህል መሆን አለበት!

No comments:

Post a Comment