EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Saturday 5 August 2017

ፍልስፍና የሚመራው ተግባር


(በእውነቱ ይታወቅ)
የምነገራችሁ በወላይታ ሶዶ ከተማ መርካቶ ክፍለ ከተማ ውስጥ ስለሚገኘው አማኑዔል የአካል ጉዳተኞች የቤትና የቢሮ ዕቃ ማምረቻ ማህበር ነው፡፡ ጥቂት አካል ጉዳተኛ ወጣቶች ኪሳቸው ያላቸውን ሳንቲም አራግፈው ኋላም ከመንግስት በተመቻቸላቸው የ60ሺ ብር ብድር ያቋቋሙት ማህበር አሁን ውጤታማ እየሆነ ሲሆን አባላቱ ብድራቸውን መመለስ ጀምረው የወደፊት እቅዶቻቸውን ለማሳኪያ ጥሪት ለማጠራቀም ደርሰዋል፡፡

እኔ ኮምፒውተሬ ላይ መተየብ የጀመርኩት ግን የእነዚህን ድንቅ ወጣቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ላወጋችሁ አይደለም፡፡ ይልቁንም እጄን በአፌ ላይ እንድጭን ያደረገኝን እነዚህ አካል ጉዳተኛ ወጣቶች የተነሱለትን ክቡር አላማና በእስካሁኑ ጉዟቸው ያስመዘገቡትን ስኬት ላጫውታችሁ እንጂ፡፡
አንድ የስራ ባልደረባዬ እንደነገረኝ የማህበሩ መስራች መለሰ እዮብ በከተማዋ በሚገኘው የሶዶ ክርስቲያን ሆስፒታል ውስጥ እየኖረ በዛው ይሰሩ የነበሩ የውጭ ሃገር ዜጎች በሚሰጡት ድጋፍ ብቻ ኑሮውን ይገፋ የነበረ አካል ጉዳተኛ ወጣት ነው፡፡ ይህ ግን የእሱ እጣ ፈንታ እንዳልሆነ የተረዳው ወጣት መለሰ የእሱ አይነት አካል ጉዳተኞችን አሰባስቦ ከተደጋፊነት ወደ ደጋፊነት ወዳሸጋገራቸው የስራ መስክ ተሰማሩ፡፡
ተደራጅተው ወደዚህ ስራ ሲገቡ እንፈታዋለን ብለው ከንፈራቸውን የነከሱበት ችግር መላ የአካባቢያቸውን አካል ጉዳተኞችና በየሆስፒታሎች የሚታከሙ ሕመምተኞችን እለት ከእለት የሚገጥሟቸውን ችግሮች ናቸው፡፡ እናም የማህበሩ የፈጠራ ስራ የሚመነጨው ሌሎችን ካጋጠማቸው ችግር እንጂ የአባላቱን የገንዘብ ችግር ወይም የግል ህይወታቸውን ለማሻሻል የሚያስችላቸውን የገንዘብ ትርፍ ለማሰባሰብ አይደለም፡፡ ይህንንም በአይኔ ካየሁት ስራቸው የተወሰኑትን አብነት በመጥቀስ እመሰክራለሁ፡፡
እነዚህ ወጣቶች በአካባቢያቸው ያሉ እግር ጉዳተኞች ያለባቸውን የክራንች ችግር ለመፍታት በአነስተኛ ወጭ በወርክሾፓቸው ክራንች ማምረት ችለዋል፡፡ እነሱ በተለያየ ርዝማኔ የሚያመርቱት ክራንች ጫፍ ላይ የሚታሰረው ጎማ የሚሰራው በአቅራቢያቸው ከሚገኝ የመኪና ጎማ በመሆኑ በርካሽ ዋጋ ለተገልጋዮች ማቅረብ ችለዋል፡፡ በፋብሪካዎች ተመርቶ ወደ ሃገር ውስጥ ይገባ የነበረው ክራንች መርገጫ ጫፍ ላይ የሚታሰረው ጎማ ከአንድ ወር ያልዘለለ እድሜ ሲኖረው እነሱ የሚያመርቱት ግን በዋጋ ከመርከሱ ባለፈ እስከ አንድ አመት የማገልገል ጥንካሬም አለው፡፡
በተጨማሪም በመደበኛ ባለሁለት እግር የሞተር ተሸከርካሪዎች ላይ የራሳቸውን ፈጠራ አክለው ሞደፊክ በመስራት ባለ ሶስት እግር ተሸከርካሪ ፈጥረዋል፡፡ የዚህም ዋና አላማ አካል ጉዳተኞች ሳይቸገሩ እንዲንቀሳቀሱ ማስቻል ነውና በእግር ይሰሩ የነበሩትን ማርሽና ፍሬን በእጅ የሚሰሩ አድርገው መቀየርም ችለዋል፡፡ በዚህ የተነሳም እነርሱ የሚያመርቷቸውን ሞተሮች የእግር ጉዳት ያለባቸው ሰዎች በቀላሉ ሊያሽከረክሯቸው፤ ወደ ማንኛውም አካባቢ ሊንቀሳቀሱባቸው ይችላሉ፡፡
አንዳንድ አካል ጉዳተኞች ከሚቀመጡበትና ከሚንቀሳቀሱበት ዊልቼር ተነስተው መፀዳጃ ቤት ለመጠቀም ስለማይችሉ የሌላ ሰው ከፍተኛ ድጋፍ ሲያስፈልጋቸው እናያለን፡፡ ብዙዎቻችን ከንፈር እየመጠጥን፣ አንዳንዶቻችን ደግሞ እያገዝናቸው አልፈን ይሆናል፡፡ አማኑዔሎች ግን ለእነዚህ ወገኖች ችግር ዘላቂ መፍትሄ መፍጠርን እንጂ ጊዜያዊ ድጋፍ መፈለግን አልመረጡም፡፡ እናም አካል ጉዳተኞች በተቀመጡበት ሆነው የሚፀዳዱበትን ዌልቼር እዛው ወርክሾፓቸው ውስጥ ማምረት ጀምረዋል፡፡ በመሆኑም መሰል ችግር ያለባቸው አካል ጉዳተኞች ከወንበራቸው ታቅፎ በማውረድ መፀዳጃ ቤት የሚያስቀምጣቸው፤ ከተፀዳዱ በኋላ ደግሞ መልሶ ወንበራቸው ላይ የሚያወጣቸው ሰው ሳያስፈልጋቸው መፀዳዳት የሚችሉበትን ሁኔታ ፈጥረዋል፡፡ ለአካል ጉዳተኞች የሚሆን የመፀዳጃ ቤት ወንበር/መቀመጫም ሰርተዋል፡፡
“የሌሎች አካል ጉዳተኞች ችግር የራሳችንም ችግር በመሆኑ ችግሩን ብቻ ሳይሆን መፍትሄውንም ከማንም የበለጠ እኛ እናውቃለን” የሚል ፍልስፍና ያላቸው እነኝህ ወጣቶች ሌሎች አካል ጉዳተኞችም እንደ ምግብ ዝግጅትና የቆዳ ስራዎች ባሉ የተለያዩ የሙያ መስኮች ተሰማርተው ራሳቸውን እንዲችሉ በመደገፍ ላይ ናቸው፡፡ በራሳቸው ወርክሾፕ ለሌሎች አካል ጉዳት ለሌለባቸው ወጣቶችም የስራ እድል ፈጥረዋል፡፡
እነ መለሰ የአካል ጉዳት ላለባቸው ብቻ ሳይሆን በጊዜያዊነት በሆስፒታሎች የሚታከሙ ሰዎች ለሚያጋጥሟቸው ችግሮችም መላ አላጡም፡፡ ለአብነት እግራቸውን በጀሶ የሚያሳስሩ ህመምተኞች የሚያደርጉት ጫማ ከቀላል ቁሶች ሰርተዋል፡፡ ጫማው የታሰረው ጀሶ ያለጊዜው እንዳይሰበር እና እንዳይቆሽሽ የሚያደርግ በመሆኑ ምርታቸው በአካባቢው ባለው የሶዶ ክርስቲያን ሆስፒታል ተቀባይነት አግኝቷል፡፡
ከውጭ ሀገር ከሚገቡት ይልቅ ጠንካራና ለአጠቃቀም ቀላል የሆኑ ስትሬቸር እና የህክምና አልጋም ማምረት ጀምረዋል፡፡ እስካሁን 60 አልጋ ለኦቶና ሪፈራል ሆስፒታል ሰርተው አቅርበዋል፡፡ በአንድ ወቅት የመለሰ ክራንች ተሰብሮ ይደግፈው ለነበረው የሶዶ ክርስቲያን ሆስፒታል ደግሞ 30 አልጋ አቅርበዋል፡፡
የመስሪያና መሸጫ ቦታ እስኪመቻችላቸው እንኳን ሳይጠብቁ በራሳቸው ቤት ተከራይተው ስራ የጀመሩት እነዚህ ወጣቶች በዙሪያቸው ካሉ ሌሎች ሰዎች ያጋጥማቸው የነበረውን ከአመለካከት ችግር ጋር የተያያዙ መሰናክሎችን ጭምር በማለፍ አሁን የስኬትን መንገድ ጀምረዋል፡፡ ምርጥ ተሞክሯቸው ግን በሁሉም አካባቢዎች ሊሰፋ የሚችልና የሚገባው ተግባር ነው፡፡

የዚህ የአካል ጉዳተኞች ማህበር 15 አባላት በሙሉ የድርጅታችን ደኢሕዴን/ኢሕአዴግ አባላት ናቸው፡፡ የወጣቶቹን መልካም ተሞክሮ በስፍራው ተገኝቶ የጎበኘው የኢሕአዴግ ወጣቶች ሊግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴም ተሞክሮውን በመቀመር ወደሌሎች አካባቢዎች ለማስፋት ይሰራል፡፡

2 comments:

  1. የነዚህ ወጣቶች ምርጭ ተሞክሮ መስፋፋት አለበት !!!

    ReplyDelete
    Replies
    1. በብሎግና በፌስቡክ የመረጃ ተደራሽነታቹ በጣም ደስ ይላል !! በርቱ እኛም ከጎናቹ ነን !!

      Delete