EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Saturday 12 August 2017

ማስተማር፣ ማሻሻልና መቅጣት

(በሚሚ ታደሰ)
ከግብር የሚሰበሰበዉ ገንዘብ መጠን እንደየሀገራቱ የልማት ደረጃ፤ የልማት ፖሊሲና የማስፈጸም አቅም የተለያየ ሊሆን እንደሚችል ቢታወቅም ሀገራት ለእድገታቸዉ የሚያስፈልጋቸዉን ወጪ ከሚያገኙበት መንገድ መካከል ዋነኛዉ ከግብር የሚሠበሰብ ገቢ ነዉ፡፡ ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሃብት የሚሰበስቡት ገቢ የየሀገራቱን የልማት መዳረሻ ለማመላከት የሚችል አቅጣጫ ጠቋሚ መሳሪያ ተደርጎም ይወሰዳል፡፡

ደረጃው ቢለያይም በሁሉም የአለማችን ክፍል የገቢ መጠኑን ለማሳደግ በሚሰራው መንግስትና በግብር ከፋዩ ህብረተሰብ መካከል የሚፈጠሩ ቅሬታዎች አሉ፡፡ ያም ሆኖ በአለም ላይ ሰፊ ተቀባይነት ያለው አመለካከት ግብርን መክፈል የዜግነት ግዴታ ብቻ ሳይሆን እያደገ የሄደ ባህል መሆኑ ነው፡፡ መንግስታትም ከሚከተሉት ርዕዮተ ዓለም ጋር የሚጣጣም የግብር ስርዓትን ይዘረጋሉ፡፡
ግብርን በሚገባው መጠን እና በወቅቱ ላለመክፈል መነሻ ተደርገው የሚወሰዱ የተለያዩ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ከነዚህ መካከል አንዳንድ ግብር ከፋዮች በተለያየ መንገድ ከሚያገኙት ገቢ ለመንግስት ግብር መክፈል እንደሚገባቸው መዘንጋታቸዉ ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ሆነ ብለዉ ህገ ወጥ መንገዶችን በመጠቀም የእነሱ ያልሆነን ሃብት ለማካበት የሚከተሉት አካሄድ ነው፡፡ እነኝህን አይነት ተግባሮች በሁሉም ሀገራት በሚባል ደረጃ የሚስተዋሉ ሲሆን መንግስታት ለልማት ሊያዉሉት የሚገባን ከፍተኛ ሃብት ያሳጣቸዋል፡፡ በሀገራችንም በተለይ በዓመቱ መጨረሻ ወራት ላይ የሚታየዉም ከዚህ አለማዊ ሁኔታ የሚለይ አይደለም፡፡
የማንኛውም መንግስት አስተማማኝ የገቢ ምንጭ ኢኮኖሚዉ በሀገር ውስጥ ከሚያመነጨዉ ሀብት ዉስጥ በግብር እና በታክስ የሚሰበሰበዉ ገቢ ነዉ፡፡ ሀገራችን ከሰሀራ በታች ካሉ ሀገራት ግዙፍ ኢኮኖሚ በመገንባት ያለችና ላለፉት አስርት አመታት ፈጣን እድገት ያስመዘገበች ቢሆንም ዛሬም ድረስ ሀገሪቱ የምትሰበስበዉ ገቢ መሰብሰብ ካለበት መጠን አንጻር እጅግ አነስተኛ የሚባል ነዉ፡፡
በሀገራችን የግብር አሰባሰብ አጠቃላይ ሁኔታ የቅርብ ዓመታት መረጃን በማጣቀስ ሲገመገም የወጪ አሸፋፈን ደረጃዉ በ2000 በጀት ዓመት ከነበረበት 50 በመቶ ሰፈ መሻሻል እያሳየ መጥቷል፡፡ ሆኖም ከዚህ ውስጥ ከ50 በመቶ በላይ አስተማማኝ ካልሆነ የጉምሩክ ቀረጥ የሚሰበሰብ መሆኑ በአሉታ የሚታይ ነዉ፡፡ ከገቢ ስርዓቱ ጋር በተያያዘ ዋነኛዉ ችግር ግን እየተሰበሰበ ያለዉ ግብር ከሀገራዊ ጠቅላላ ዓመታዊ ምርት አንጻር እስከ 2008 ዓ.ም ድረስ ከ13 በመቶ አለመዝለሉ ነዉ፡፡ ይህ አሀዛዊ መረጃ የሚያመላክተዉ አድገዋል የሚባሉት ሀገሮች ከሚሰበስቡት ከ25 በመቶ እስከ 45 በመቶና በማደግ ላይ ያሉ ሀገሮች ከሚሰበስቡት ከ18 በመቶ እስከ 25 በመቶ ገቢ አንጻር ሀገራችን ምን ያህል አነስተኛ የገቢ አሰባሰብ እንዳላት ነው፡፡ ከሰሀራ በታች ያሉ ሀገራት ከሚሰበስቡት የ16 በመቶ አማካይ ገቢ ጋር ሲነጻጸርም የእኛ ደካማ ነዉ፡፡
መንግስትና ልማታዊ ነጋዴዉ የአንድ አላማ እኩል ተዋናዮች ናቸዉ፡፡ ሁለቱም ጤናማ የግብይት ስርዓትን መፍጠርና በዚህም ዉስጥ ሀገሪቱ የተያያዘችዉን የህዳሴ ጉዞ በማፋጠን የተሻለች ሀገር ተገንብታ ማየትን ይሻሉ፡፡ በተጨባጭም መንግስት በሁሉም መስኮች ባለፉት ዓመታት ላስመዘገባቸዉ ዘርፈ ብዙ የልማት ድሎች ይብዛም ይነስ ከንግዱ ማህበረሰብ የሚሰበሰበዉ ገቢ የራሱ ድርሻ አለዉ፡፡ ሆኖም በየአመቱ የግብር መሰብሰቢያ ወቅት ሲደርስ በተለይ በተወሰኑ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ዘንድ ተገቢውን ግብር ላለመክፈል የሚታየው ማንገራገር እንደ ባህል እየተወሰደ ያለ ሆኗል፡፡
እንደሚታወቀው ከራሱ ከንግዱ ማህበረሰብ በሚሰበሰበው ገንዘብ የላቀ ተጠቃሚ የሚሆነው ይሄው የህብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ የመንገድ አዉታሮች ግንባታ፣ የቴሌኮሚኒኬሽን መስመር ዝርጋታ፤  የሃይል አቅርቦት፣ ወዘተ… ሁሉ ነጋዴው ታችኛዉ አርሶ አደር ድረስ ወርዶ እንዲገበያይ፤ የንግድ ስርአቱን እንዲያዘምን፣ የአገልግሎትና ምርት አቅርቦት እንዲያድግለት የሚያስችሉት ናቸው፡፡

ግብርን በፈቃደኝነትና ታማኝነት የመክፈል ባህልን ማሳደግ ኢኮኖሚዉ የሚያመነጨዉን ገቢ በብቃት ለመሰብሰብ እንደሚያስችል ይታመናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሰፊና ተከታታይ የአስተምህሮ ስራዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ተገቢዉን ግብር የማይከፍሉትን በቅድሚያ ማስተማርና ማስገንዘብ ልማታዊ አቅጣጫ የሚይዙበትን መንገድ ማመቻቸት ለነገ የማይባል ስራ ነዉ፡፡ ይህ መሰረታዊና ዋነኛ ስልት ሆኖ እያለ ግብር የሚደብቁ ህገ ወጥ ነጋዴዎችንና ኮንትሮባንዲስቶችን ለይቶ ማንገዋለል፣ በህግ መጠየቅ እና የተወሰደዉንም እርምጃ ለሌላዉ ማስተማሪያ ማድረግ ይገባል፡፡ ይህም የሚሳካዉ ራሱን የንግዱን ማህበረሰብና አጠቃላይ ሕዝቡን በንቃት በማሳተፍ ነው፡፡ 
በተጨማሪም በግብር ሰብሳቢዉ አካልም ላይ የተጠያቂነት ስርዓት መዘርጋት አለበት፡፡ ሌላኛዉ ተግባር በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያሉ ክፍተቶችንና የአቅም ውስንነቶችን መሙላት ነው፡፡ ግብር መሰብሰብ በዓመቱ መጨረሻ የሚሰራ ደራሽ ስራ ሳይሆን የየእለት ተግባር መሆን ነዉ ያለበት፡፡ 

No comments:

Post a Comment