EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Thursday 17 August 2017

የኢትዮጵያን ህዳሴ ከዳር ለማድረስ የታላቁን መሪ 13ት መገለጫዎች እንላበስ!!




                                                    



                                               
     ከታጋይ ሓዱሽ ካሡ
ዘንድሮ ማለትም ነሐሴ 15/2009 ዓ.ም. የታላቁ መሪ ታጋይ መለስ ዜናዊ አምስተኛው/5ኛው/ የመስዋእትነት ዕለት “የሃሳብ ድህነትን ታግሎ ያሸነፈ መሪ” በሚል መሪ ቃል ይዘከራል፡፡ ከይዘት አኳያ መሪ ቃሉ ብዙ ቁም ነገሮችን ያካተተ ቢሆንም ከዚህ ጽሑፍ ግብ አኳያ በቅጥሉ እንደሚከተለው ቢባል ብዙም ችግር አይኖረውም የሚል እምነት አለ፡፡ ይኸውም ከሁሉም በላይ ታላቁ መሪ ታጋይ መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያን የብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እስር ቤት አድርጓት የቆየውን ጨቋኝ ኋላቀር ሥርዓት ከእነ ግሳንግሱ እንዲወገድ በመታገሉና ከትግል አጋሮቹ ጋር ሆኖ በሳል አመራር በመስጠቱ ደርግ ከ26 ዓመታት በፊት ግብዓተ መሬቱ እንዲፈፀም የላቀ አስተዋፅኦ ማድረጉን ያመለክታል፡፡ ፋሽስታዊ ወታደራዊ የደርግ አረመኔያዊ አገዛዝ አፋኝ መዋቅሩ፣ በኢህአዴግ መሪነት፣ በኢትዮጵያ ህዝቦች መራራ ትግልና መስዋዕትነት ሥርዓተ ቀብሩ ከተፈፀመ ማግስት ጀምሮም ታላቁ መሪ ታጋይ መለስ ዜናዊ በኢትዮጵያ ለ100 ዓመታት ያህል የነበሩትን የትምክህትና የጠባብነት አስተሳሰቦች፣ ኋላቀር የጥፋትና የበታኝ ኃይሎች አማራጮች መሆናቸውን በተጨባጭ በማሳየት፣ ከኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እንዲነጠሉ ሰፊ የሃሳብ ትግል አድርጓል፡፡ በዚህ ዙሪያ የተደረገው የሃሣብ ትግልም ተጨባጭ ውጤት አስመዝግቧል፡፡ 

 
ይኸውም ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነትን መሠረት ያደረገው ዴሞክራሲያዊና ፌዴራላዊ ሥርዓት ለአደሲቷ ኢትዮጵያ ዘላቂ ዋስትና መሆኑን በገሃድ አሳይቷል፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችም ላለፉት 26 ዓመታት በመፈቃቀድና በመከባበር ላይ የተመሠረተ ዴሞክራሰያዊ አንድነት እውን አድርገው በጋራ ለዘላቂ ጥቅማቸውና ህልውናቸው ተንቀሳቅሰዋል።፣ የኢትዮጵያ ህዳሴ መሃንዲስ፣ ታላቁ መሪ ታጋይ መለስ ዜናዊ፣ የኢትዮጵያ ዋነኛ ጠላት ድህነት ነው የሚለውን አስተሳሰብ በብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ ማኖር ችሏል፡፡  በአሁኑ ወቅት ድህነትን ለማሸነፍ ፋኖ ተሰማራ አያስፈልግም፤ የድህነት ተራራ የሚናደው በዕውቀት ነው በማለት የቀየሰውን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ኢትዮጵያውያን ቀንና ሌሊት በመውተርተር ላይ ናቸው፡፡ በውጤት ደረጃም ኢትዮጵያ በአጠቃላይ ባለፉት 26 ዓመታት በተለይም ባለፉት 15 ዓመታት፣ ማለትም ለ13 ተከታታይ ዓመታት መሠረተ ሰፊ፣ ፈጣን  እና እያንዳንዱ ዜጋ በየደረጃው ተጠቃሚ የሆነበት ዙሪያ መለስ ባለ ሁለት አሃዝ የማህበረ - ኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ ከአፍሪካ ቀዳሚ ኢኮኖሚ ካላቸው አገሮች አንዷ ሆናለች፡፡ 

ከዚህ ባሻገር ታላቁ መሪ ታጋይ መለስ ዜናዊ፣ የኒዮ-ሊበራል አስተሳሰብ፣ በአጠቃላይ ለአፍሪካ አማራጭ እንዳልሆነና የከሰረ ርዕዮት መሆኑን በጥልቅ ምርምርና ትንተና አስደግፎ በዓለም አደባባይ ሽንጡን ገትሮ በመታገል ዕርቃኑን አውጥቶታል፡፡  ታላቁ መሪ ታጋይ መለስ ዜናዊ  ዓለም ያጋጠማትን የአካባቢ አየር ብክለት መንስኤውንና መፍትሄውን በሳይንሳዊ ትንተና አስደግፎ የዓለምን መሪዎች በአስተሳሰብ ታግሎ ያሸነፈና ተጨባጭ ውጤት ያመጣ ለዘመናችን የሚመጥን ድንቅ ሰብዕና ያለው መሪም ነበር። የታላቁ መሪ ታጋይ መለስ ዜናዊ 5ኛው የመስዋዕትነት ዓመት ለማሰብ የተቀረፀው “የሃሳብ ድህነትን ታግሎ ያሸነፈ መሪ” የሚለው ገለፃም ከላይ የተገለፁት ዋና ጉዳዮች ለማመላከት ታስቦ ሊሆን ይችላል፡፡

ታላቁ መሪ ታጋይ መለስ ዜናዊ፣ በአጠቃላይ አፍሪካ፣ በዋነኛነት ኢትዮጵያ ከገባችበት የድህነት አረንቋ ተላቃ ከፍተኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ መሰለፍ የምትችለው፣ በኒዮ-ሊበራል አስተሳሰብ እና የኪራይ ሰብሳቢነት የፖለቲካል ኢኮኖሚ ሳይሆን፣  በዴሞክራሲያዊና ልማታዊ አስተሳሰብ ስትመራ መሆኑን በተጨባጭ አሳይቷል፡፡ ይኸውም ታላቁ መሪ ታጋይ መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት 45 እና 50 ዓመታት ከፍተኛ ገቢ ካላቸው አገሮች እንዴት እንደምትደርስ፣ በጥልቅ ሣይንሳዊ ትንተና ተንተርሶ የኢትዮጵያ የህዳሴ ጉዞ ሦስት መዳረሻ ምዕራፎችን እና መሠረታዊ አቅጣጫዎችን  አመላክቷል፡፡ 
                                                  



ሆኖም የኢትዮጵያ ህዳሴ በቀላሉ የሚደረስ አይሆንም፡፡ ብዙ ውጣ ውረድና ከፍ ዝቅ ያጋጥማል።  ከፍተኛ የሆነ የዕውቀት፣ የጉልበት፣ የገንዘብ ወዘተ  መስዋዕትነት ይጠይቃል፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያን የህዳሴ ጉዞ ለማሳካት በቅድሚያ ኪራይ ሰብሳቢነትን አምርሮ የሚጠላና በተግባር የሚታገል፣ በዋነኛነት ደግሞ ዴሞክራሲያዊና ልማታዊ አስተሳሰብን በእምነት ተቀብሎ ትግሉን ወደፊት የሚያስቀጥል ተራማጅ ኃይል መፍጠር ይጠይቃል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በጊዜ የለንም እምነት (Sense of urgency) ቀንና ሌሊት ሠርቶ የሚያሠራ፣ በሳል አመራር የግድ ይላል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን የታላቁን መሪ ታጋይ መለስ ዜናዊ ለጋሲን ከደሙ አዋህዶ በማራቶን የዱላ ቅብብል ሩጫ፣ የኢትዮጵያን የህዳሴ ጉዞ ዳር የሚያደርስ ትውልድ ማነፅ ያስፈልጋል፡፡

ለመሆኑ የታላቁ መሪ ታጋይ መለስ ዜናዊ ለጋሲ ሲባል ምን ማለት ነው?! በእርግጥ የታላቁ መሪ ታጋይ መለስ ዜናዊ ፖለቲካዊ ማንነት፣ ስብዕና እና ለጋሲ በተሟላ አኳኋን በቃላት ለመግለፅ አስቸጋሪ ነው፡፡ ሆኖም ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ ለ40 ዓመታት ያህል ያደረገው የትግልና የድል የህይወት ጉዞው፣ ተጠቃልሎ በሁለት ዓበይት ጉዳዮች ቢገለፅ የሚበዛው ሊስማማበት ይችላል፡፡ ይኸውም ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ 1ኛ/ በአራቱም የዓለም ማዕዘናት ያሉት ህዝቦች መካከል ያለው ግንኙነት ጤናማና በፅኑ መሠረት እንዲገነባ ማለትም ጨቋኝና ተጨቋኝ፣ የበላይና የበታች፣ በዝባዥና ተበዝባዥ ሥርዓት ተወግዶ ሁሉም ህዝብ በእኩልነት ታይቶ ፍትሃዊ ተጠቃሚ እንዲሆን፣  እንዲሁም በሰዎች እና በተፈጥሮ መካከል ሚዛናዊ ግንኙነት እንዲኖር ዕድሜ ልኩን የታገለ እና ያታገለ በሳል የፖለቲካ መሪ ነው፣ ቢባል ሃቁን መናገር እንጂ ማጋነን አይሆንም፡፡ እነዚህ ሁለት ዓበይት ጉዳዮችም ጠቅለል ተደርገው በ13 ዋና ዋና መገለጫዎች እና ባህሪያት ሊገለፁ ይችላሉ፡፡ 

የታላቁ መሪ ታጋይ መለስ ዜናዊ አሥራ ሦስት/13/ መገለጫዎችና ባህሪያትን የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች፣ በዋነኛነት ወጣቱ ትውልድ ሊወርሳቸው የሚገቡ ናቸው፡፡ የታላቁ መሪ ታጋይ መለስ ዜናዊ ፖለቲካዊ ስብዕናውንና ማንነቱን የሚያመለክቱ 13ቱ ዋና ዋና መገለጫዎችና ባህሪያቱ  በሚከተለው መልኩ ሊቀመጡ ይችላሉ፡፡ “1ኛ/ ታጋይ መለስ ዜናዊ የላቀ ህዝባዊ ውግንና ያለው መሪ 2ኛ/ ታጋይ መለስ ዜናዊ አይበገሬ የፅናት ተምሳሌት 3ኛ/ ታጋይ መለስ ዜናዊ ሳይንሳዊ ተራማጅ አስተሳሰብና ተግባርን የሚያራምድና የሚቀበል መሪ 4ኛ/ ታጋይ መለስ ዜናዊ  በመርህና በህግ የበላይነት የሚያምን መሪ 5ኛ/ ታጋይ መለስ ዜናዊ  ባለ ትልቅ ራዕይ መሪ 6ኛ/ ታጋይ መለስ ዜናዊ  በትልቁ የሚያስብና በትልቁ ለመተግበር የሚተጋ መሪ     7ኛ/ ታጋይ መለስ ዜናዊ  ሁሌም ነገሮችን በሳይንሳዊ ዕውቀት ላይ ተመስርቶ የመመልከት ብቃት ያለው መሪ      8ኛ/ ታጋይ መለስ ዜናዊ  ለዴሞክራሲ የቆመ መሪ 9ኛ/ ታጋይ መለስ ዜናዊ  ተማሪም፣ አስተማሪም፣ ተመራማሪም 10ኛ/ ታጋይ መለስ ዜናዊ የልማት አርበኛ 11ኛ/ ታጋይ መለስ ዜናዊ  ለሰላም የቆመ መሪ 12ኛ/ ታጋይ መለስ ዜናዊ  ሕገ መንግሥት አክባሪና አስከባሪ 13ኛ/ ታጋይ መለስ ዜናዊ  ሰብአዊ፣ ፍትሃዊና ሩህሩህ መሪ፡፡”  ተብለው ሊገለጽ ይችላል፡፡ 
                                      



በዚህ አጋጣሚ፣ ባለፉት ዓመታት የታላቁ መሪ የታጋይ መለስ ዜናዊ ለጋሲ ለማስተዋወቅ የጣሩት ሁሉ ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል፡፡ ለምን ቢባል በዋነኛነት ታላቁ መሪ ታጋይ መለስ ዜናዊ ከተሰዋበት ማግስት ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ አንዳንድ ፀሐፊዎች፣ የታላቁ መሪ ታጋይ መለስ ዜናዊ ለጋሲን መነሻ አድርገው፤ የትግል ህይወቱን የሚያወሳ ታሪክ በመጽሐፍ መልክ አዘጋጅተው ለአንባቢ ጀባ ማለት ጀምረዋል፡፡ ይህ በጎ ሥራቸው ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ነገር ግን አሁንም የታላቁ መሪ ታጋይ መለስ ዜናዊ ፖለቲካዊ ህይወትን የማስተዋወቅ ጉዳይ ገና መቼ ተነካ እና የሚያሰኝ ሁኔታ ነው ያለው፡፡ እናም ፀሐፍት ሆይ እውነተኛው ታሪክ ሳይደበዝዝ ለትውልዶች ለማስተላለፍ ተነሳሱ፡፡ 

እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ አለ፡፡ ይኸውም የታላቁ መሪ ታጋይ መለስ ዜናዊ ለጋሲ ሲባል፣ የታጋይ መለስ ዜናዊን ተክለ ስብዕና ለማጉላት አይደለም፡፡ ይልቁንም የታጋይ መለስ ዜናዊ ለጋሲ ሲባል በአራቱም የኢትዮጵያ አቅጣጫ ማለትም በገጠርና በከተማ ለፍትህ፣ ሰላም፣ ለዴሞክራሲና ለልማት ሲሉ ውድ ህይወታቸውን መስዋዕት ያደረጉ የህዝብ ልጆች ገድልና ታሪክ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ለዚህም ነው ቀጣይ ትውልድ ሊወርሰው ይገባል የሚባለው፡፡

በመሆኑም በዋነኛነት ኢትዮጵያ አገራችን ከስምንት/8/ ዓመታት በኋላ ማለትም እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ2017 ዓ.ም. ዝቅተኛ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለመድረስ ያስቀመጠችውን ራዕይና ግብ ለማሳካት፣ በአጠቃላይ ደግሞ ከ45 እና 50 ዓመታት በኋላ ካደጉት አገራት ተርታ የሚያሰልፋት የከፍተኛ ገቢ እርከን ለመድረስ የሚያስችላት፣ የኢትዮጵያን ህዳሴ በድል ለማጠናቀቅ፣ የታላቁ መሪ ታጋይ መለስ ዜናዊ ሌጋሲ 13ቱ ዋና ዋና መገለጫዎችና ባህሪያትን መላበስ  አስፈላጊ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡

“የሃሳብ ድህነትን ታግሎ ያሸነፈ መሪ” እሴቶችና ሌጋሲ ጨብጠን ህዳሴችን እናሳከለን!!
ቸር ይግጠመን!!
     


No comments:

Post a Comment