EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Saturday 27 May 2017

ለብዙኃነት መከበር ፈር የቀደደ ፌዴራላዊ ስርዓት




ከኤፊ ሰውነት

የአገራችን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በአገራቸው ባይተዋር ተደርገው ይቆጠሩበት የነበረው ያ ከእሬት የመረረ ዘመን ላይመለስ ከተቀበረ ሁለት አስርት ዓመታት አለፉ፡፡ የቁርጥ ቀን ልጆች በከፈሉት መሪር መስዋዕትነት ከእኔ ዘመን ወደ እኛ ዘመን ከተሸጋገርን፤ በመከባበርና በመተባበር ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ስር ሆነን በጋራ መትመም ከጀመርን 26 ዓመታት ተቆጥሩ፡፡ አገራችን ኢትዮጵያም  የጦርነት ታሪኳ ላይመለስ ወደ መቃብር ተወርወሯል፤ የህዳሴ ዘመንም ተበስሯል፡፡ ግንቦት 20፣ 1983 የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የድል ብስራት የተበሰረበት ታሪካዊ ዕለት፡፡ ከህዝብ ወጥቶ ለህዝብ መስዋዕትነት የከፈለው ኢህአዴግ የአገራችንን ህዝቦች የጸረ ጭቆና ትግል በመምራት የህዝብ ትግል ዳር እንዲደርስ በማድረግ ፋና ወጊ ሆኗል፡፡  

አገራችን ኢትዮጵያም አንድነቷ ተጠብቆ፤ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦቿም አንዱ የአንዱን ማንነት አክብረውና ኢትዮጵያዊነትም በግዳጅ የሚቀበሉት ሳይሆን ወደውና ፈቅደው የሚያጣጥሙት ማንነት መሆኑን አምነው የጋራ ቤታቸውን በጋራ እያለሙ ይገኛሉ፡፡ የጋራ ቃልኪዳናቸው በሆነው ህገ መንግስትና የፌዴራል ስርዓት መተዳደር በመጀመራቸው ላለፉት 26 ዓመታት በሁለንተናዊ መልኩ የሚገለፅ ስኬት ባለቤት ለመሆን በቅተዋል፡፡

አገራችን የምትከተለው የፌዴራል ስርዓትም አንዱ ትንሽ ሌላው ትልቅ እየተባለ በብሄሮች መካከል ደረጃ ምደባ የሚቀመጥበት ሳይሆን ሁሉም ተከባብሮ እንደ አገር ጠንካራ ማህበረሰብ የሚሆንበት እድልን የፈጠረ ነው፡፡ የግንቦት 20 ድል ትሩፋት የሆነውና የአገራችን ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ተወያየተው፤ ተከራክረውና ተመካክረው ያፀደቁት ህገ መንግስት ከዚህ በፊት የነበሩ የተዛቡ ግንኝነቶችን ለማረምና በእኩልነትና በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አዲስ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመመስረት የሚያስችላቸውን ራዕይም ይዟል፡፡   

ውድ አንባብያን በአገራችን ታሪክ ሕገ-መንግስት የሚል የተሟላ ስያሜ ባንሰጣቸውም የአገሪቱ የበላይ ሕግ ሆነው ያገለግሉ የነበሩ ሕጎች እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ ፍትሃ-ነገስት እና ክብረ-ነገስት የተበሉ ህጎችን ጨምሮ በ1923 . ስራ ላይ የዋለው የንጉሰ-ነገስት ሕገ-መንግስት፣ ይህንን ሕግ በማሻሻል 1948 . የፀደቀው ሕገ-መንግስት እና በወታደራዊ ደርግ መንግስት ስራ ላይ የዋለው 1980 . ሕገ-መንግስት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የእነዚህ ህገ መንግስቶች ውግንና ግን ለህዝብ ሳይሆን ስልጣን ላይ ለነበረው አካል በሚመች መልኩ የተቀረፀ በመሆኑ የብሄረ ብሄረሰብ መብት ብሎ ነገር የሚታሰብ አልነበረም፡፡ በ1987 የፀደቀውን የኢፌዴሪ ሕገ መንግስት ስናይ ደግሞ ከጅምሩ ህገ መንግስቱን በማረቀቅ ሂደት ውስጥ ህዝቡ በቀጥታ ከመሳተፍ እስከማፀደቅ ድረስ ተሳታፊ የነበረ መሆኑ ለየት ያደርገዋል፡፡ ከዚህ ባለፈ የብሄር ብሄረሰቦች እኩልነት ከቃል ባለፈ በሰነድ ሰፍሮ የሚገኘው በዚህኛው በኢፌደሪ ህገ መንግስት ነው፡፡ የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦችን መብት ያለገደብ እንዲከበር ያደረገና የአንድነታቸው ዋስትና በመሆኑም ዜጎች እንደ ዓይን ብሌናቸው የሚጠብቁትና የሚያከብሩት ህገ መንግስት መሆን ችሏል፡፡

አገራችን ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ዓመታት ፌዴራላዊ በሆነ የመንግስት አወቃቀር ውስጥ በመተዳደር ላይ ትገኛለች፡፡ በህገመንግስቱም የፌዴራል መንግስት አወቃቀርን ከነስልጣን ክፍፍሉ በግልፅ በማስቀመጥ ስልጣን ከአንድ ማዕከል የሚወርድ ሳይሆን ሁሉም ክልል ራሱን በራሱ የሚያስተዳድርበት፣ ሃብቱን ጥቅም ላይ የሚያውልበት፣ ለዚህም የሚያግዘውን ተቋም የሚያደራጅበት መብት ከማጎናፀፉ ባሻገር የሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትም ህዝቡ ራሱ መሆኑ በግልፅ ሰፍሮ ይገኛል፡፡

አገራችን በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት ገና በአፍላ ዕድሜ ውስጥ ያለች መሆኑ ይታወቃል፡፡ የፌዴራል ስርዓቱም የተሸጋገረው ፍፁም አምባገነንና ስልጣን በአንድ ማዕከል ውስጥ ከተሰበሰበበት አህዳዊ ከሆነ የመንግስት አስተዳደር ነው፡፡ አገራችን የፌዴራላዊ የመንግስት አወቃቀር መከተሏ የአማራጭ ጉዳይ ብቻም ሳይሆን እንደ አገር ሳትበታተን እንድትቀጥል ለማድረግ ብቸኛው አማራጭም ስለሆነም ጭምር ነው፡፡ 

የፌዴራል ስርዓቱ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች እርስ በእርሳቸው እንዲተዋወቁ፣ ቱባ ባህሎችና እሴቶች እንዲታወቁ እና እንዲበለጽጉ እድል ከመፍጠሩ ባሻገር በፌዴራል ደረጃ የስልጣን እርከን ጭምር ውክልና እንዲኖራቸው ያደረገ ነው፡፡ ህገ መንግስቱ ለህዝብ ተወካዮ ምክር ቤት እያንዳንዱ ብሄርና ብሄረሰብ ብሄረሰብ ባለ መቀመጫ ባለው የህዝብ ቁጥር ልክ የሚወሰን ለ100ሺ ህዝብ አንድ ተወካይ እንዲኖር ከማድረጉ  በተጨማሪ በቁጥር አናሳ የሆኑ ብሄረሰቦች 23 ተጨማሪ መቀመጫ እንዲኖራቸው ተደርጓል፡፡
 
የፌዴራላዊ ስርዓት ሁለት አልያም ከሁለት በላይ መንግስታት የራስና የጋራ አስተዳደርን ባጣመረ መልኩ የሚመሰረት አጋርነት ነው፡፡ በዓለማችን ነባራዊ ሁኔታ ከአፍሪካ እስከ ሰለጠነው አውሮፓ ድርስ በርካታ ቁጥር ያላቸው አገራት የፌዴራል ስርዓትን እንደሚከተሉ ይታወቃል፡፡ አንዳንድ አገራት መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥን፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ማንነትን ማዕከል ያደረገ አልያም ሁለቱንም ያጣመረ ስርዓት ይከተላሉ፡፡ የአገራችን ኢትዮጵያ የፌዴራል መንግስት አወቃቀር በህገ መንግስቱ በግልፅ እንደተመላከተው የመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣በማንት፣ ቋንቋ፣ ስነልቦናዊ አንድነትና የህዝብ ይሁናታን ማዕከል ያደረገ ነው፡፡  ብሄሮች ብሄረ ሰቦችና ህዝቦችም  ቁጥራቸው በዛም  አነሰም መብታቸው  በህገ መንግስት እውቅና እንዲያገኝና እንዲከበር  ተደርጓል፡፡ 

የአገራችን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የጋራ ሰነድ በሆነው ህገ መንግስት አንቀፅ 39 ንዑስ አንቀፅ 2 እና 3 ላይ ይህ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ “ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ በቋንቋው የመናገር፣ የመጻፍ፣ ቋንቋውን የማሳደግ እና ባሕሉን የመግለጽ፣ የማዳበርና የማስፋፋት እንዲሁም ታሪኩን የመንከባከብ መብት አለው፡፡” አንቀፅ 3 “ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ ራሱን የማስተዳደር ሙሉ መብት አለው፡፡ ይህ መብት ብሔሩ፣ ብሔረሰቡ፣ ሕዝቡ በሰፈረበት ክልል ራሱን የሚያስተዳድርበት መንግስታዊ ተቋማት የማቋቋም እንዲሁም በክልልና በፌዴራል አስተዳደሮች ውስጥ ሚዛናዊ ውክልና የማግኘት መብትን ያጠቃልላል፡፡” ሲልም ያስቀምጣል፡፡ 

ከዚህ መነሻ ባለፉት 26 ዓመታት ሁለንተናዊ በሚባል ደረጃ አንደነታችንን በማጠናከር በአገራችን ሁሉም ክልሎች ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎ እያደገና የህዝቦች ተጠቃሚነትም እየጎለበተ መምጣት ችሏል፡፡ ባለፉት ዓመታት የተስፋፉት መሰረት ልማቶች የህዝባችንን ኢኮኖሚያዊ ትስስር አጠናክረውታል፡፡
በግንቦት 20 ድል የተጎናፀፍነው ትሩፉት የሁላችንም ነው፡፡ከበርካታ ውጣ ውረድ በኋላ በአገራችን በግንቦት 20 ድል ማግስት ስልጣን የህዝብ ሆኗል፡፡ በመሆኑም ግንቦት 20 ሲከበር ሁሉም ብሄሮችና ብሄረሰቦች መብታቸው በእኩልነት እንዲከበርና ፍትሃዊ ተጠቃሚነታቸውም እንዲረጋገጥ ያስቻለውን ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በመጠበቅ ሊሆን ይገባል፡፡ ከዚህ ባሻገር ሁሉም ዜጋ በሕገ መንግስቱና ዓላማዎቹ ላይ የጋራ አቋምና ወጥ አመለካከት በመያዝ የአገራችንን ራዕይ ማሳካት ላይ ማተኮር ይገባዋል፡፡ ሁሉም ዜጋ ለዴሞክራሲያዊ አንድነት መትጋት፣ ብዝሃነትን ማክበርና ለብዝሃነት ዋጋ መስጠት ብሎም መከባበር ላይ የተመሰረተ አንድነት ላይ መስራት የሚገባው ይሆናል፡፡ ለዚህ የምናደርገው ርብርብ ነው ሄዶ ሆዶ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመገንባት የሚያስችለን፡፡    
የህዝች መብት ሳይሸራረፍ የሚያከብር ስርዓት ተገንብቶ ህዝቦች ፊታቸውን ወደ ልማት በማዞራቸው  አገራችን ሁለንተናዊ ፈጣን ልማት እንድታስመዘግብ አድርጓታል፡፡፡፡ የኢኮኖሚያዊ አቅሟ እየጎለበተና በዓለም አቀፍ ደረጃም እውቅና እያገኘ መጥቷል፡፡ የህብረተሰባችን ኢኮኖሚያዊ ትስስርም ተጠቃሚነትም ከጊዜ ወደ ጊዜ መልካም በሚል ደረጃ እየጎለበት ይገኛል፡፡ ህዝባችን አገራዊ የሆኑ የልማት አጀንዳዎች ዙሪያ ከራሱ እየቀነሰም ጭምር ቀጣይ የሆነውን ለውጥ በማጤን እየተረባረበ ይገኛል፡፡ ይህ መጎልበት ይገባዋል፡፡ አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ ለውጥ ማምጣት የሚችለው በዚህ መንገድ የተሳትፎና የተጠቃሚነት ጉዳይ እየሰፋ ሲመጣ ነው፡፡ ምርታማነት ሲሰፋ ገበያ ይፈልጋል፤ ገበያ ደግሞ ከአገር ውስጥ ወደ አህጉር ከዛም ወደ ዓለም እየሰፋ የሚሄድ ነው፡፡ በመሆኑም እንደ አገር እያንዳንዱ ማህበረሰብ የሚፈጥረው የኢኮኖሚ አቅም አንዱ ለሌላኛው ክልል ህዝብ አቅምና ሃብት የሚሆንበትን እድል የሚያሰፋ በመሆኑ ለዚህ መትጋት ያስፈልጋል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ አንድ ሳልገልፅ የማላልፈው ነጥብ አለ፡፡ አንዳንድ ሃይሎች  የፌዴራል ስርዓቱ እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዳላሰፈነና አገሪቷንም የመበታተን አደጋ ውስጥ እንደከተታት ሲገልፁ ይሰማል፡፡ እውን በኢትዮጵያ እኩልነት የለም? የአገሪቱስ አንድነት እንዴት ይገለጻል? የሚለውን ለመመለስ በቅድመ 1983 ዓም የነበረውን ሁኔታ መገንዘብ ይገባል፡፡ 17ጠመንጃ ያነገቡ ኃይሎች ለመገንጠል ሲታገሉ የነበሩት ከ1983 ዓም በፊት እንጂ ዛሬ አይደለም፡፡ በርካታ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ኢትዮጵያውነታቸው በግዳጅ የተጫነባቸው ሸከም እንደሆነ ይሰማቸው የነበረው ከሩብ ክፍለ ዘመን በፊት እንጂ ዛሬ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ የመበታተን አደጋ ውስጥ መግባት የትናንት   እንጂ የዛሬ ታሪክ አይደለም፡፡
አንዳንድ የወደቀው ስርዓት አቀንቃኝ የሆኑ ኃይሎች ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን የማብጠልጠል አካሄድ ሲያካሄዱ ይታያል፡፡ እነዚህ ኃይሎች ከዚህ በፊት የነበሩ ስርዓታት የብሄር እኩልነትን የማይቀበሉ፤ በአንድ አገር ውስጥ አንዱ ዜጋ ሌላው ባይተዋር ሆኖ የሚኖሩባት አገር የነበረች በመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር አስጨናቂ የሆነበትና ሄዶ ሄዶ መፈንዳት ደረጃ የደረሰበት ሁኔታ እንደነበር አጥተውት አይደለም፡፡፡፡ ዛሬ እንዳለፉት ጨቋኝ ስርዓቶች እኩልነትና መብት ስትፈለግ የሚሰጥ አልያም የሚነፈግ ችሮታ ሳይሆን በህግ መንግስቱ ማዕተም ሆኖ የሚቀመጥ ሁሉም የሚቀበለው የበላይ ህግ መሆን ችሏል፡፡ ከላይ እስከ ታች ባሉ እርከኖች ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ በማድረግ የጭቆና በር ተዘግቷል፡፡ አብሮነታችን ከምን ጊዜውም በላይ እንደሚጠቅመን የተረዳ ማህበረሰብ መፍጠር ተችሏል፡፡ የሃይማኖት፣ የብሄርና መሰል ብዝሃነትን ባከበረ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ውስጥ መሆናችን ፋይዳው የላቀ መሆኑን የመገነዘብ ደረጃው ከፍ ብሏል፡፡ ይህ በይበልጥ እየተጠናከረ መሄድ እንዳለበት ግን እሙን ነው፡፡
አንድ በቁጥር ትልቅም ይሁን አናሳ ብሄር ብቻውን ተነጥሎ መድመቅ አይችልም፡፡ መድመቅ የሚቻለው በዴሞክራሲያዊ አንድነት ውስጥ ሆኖ በጋራ መትመም ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ይህን በመሰረቱ የተረዳው የአገራችን ህዝብም በዚህ መንፈስ መንቀሳቀስ ከጀመረ ውሎ አድሯል፡፡ ለዛም ነው የአገራችንን መረጋጋትና ሰላም የማይወደው ሃይል በየጊዜው እንደ እስስት እየተቀያየረ የሚመጣውን የተሳሰተ መንገድ ወደ ጎን በመተው ልማቱ ላይ ብቻ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ያለው፡፡
በእርግጥ አንዳንዴ የሚፈጠሩ ችግሮች የሉም ማለት አይቻልም፡፡ ችግሩ የቱንም ያህል ቢሆን ግን በህዝባችን መሃል ያለውን የጠበቀ ግንኙነት የሚሰብር ነው የሚል መነሻ የለኝም፡፡ አንዳንድ ሃይሎች ግጭት ለመቀስቀስና አንዱን በሌላው ላይ ለማነሳሳት የፌዴራል ስርዓቱን ከማብጠልጠልና አጀንዳ ከማድረግ የተለየ ሌላ መንገድ የሌላቸው በመሆኑ ሲዘምቱበት ይስተዋላል፡፡ ለእኔ ጉዳዩን ወደ ኋላ ሄዶ ከመመዘን ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ አዲስ ናት፡፡ በህዳሴ ጉዞ ላይ ያለች፡፡ ነገን አልፎ መሻገር በሚችል ህዝባዊ ድርጅት፣ ፖሊሲና ስትራቴጂ እየተመራች ያለች አገር ናት፡፡ ዛሬ ሌላ ቀን ነው፡፡ የእኛ ብዝኃነት ሌላው እንደሚለው ዛሬ የተፈጠረ ሳይሆን ተፈጥሯዊና ድሮም የነበረ ዛሬም የቀጠለ ነው፡፡ ልዩነቱ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ብዝኃነታችን እውቅና ተሰጥቶት ሁሉም ራሱን መግለፅ የሚችልበት ስርዓት ተፈጥሯል፡፡ ይህ እውነታ እንደተጠበቀ ሆኖ ዴሞክራሲያዊ አንድታችንን የማጎልበት ኃላፊነት የሁሉም ዜጋ ነውና ለዚህ እንትጋ መልዕክቴ ነው፡፡  ግንቦት 20ን ስናከበርም ነገን አሻግረን እየተመለከትን ለነገም እየተጋን ሊሆን ይገባል ባይ ነኝ፡፡ ሰላም!

No comments:

Post a Comment