EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Tuesday 18 April 2017

ለአድሎ በር የዘጋ ፌዴራላዊ ስርዓት




በክሩቤል መርሃጻድቅ 
በአንድ ወቅት በዓለም ከነበሩ ታላላቅ ስልጣኔዎች መካከል ትመደብ የነበረችው ኢትዮጵያ ስልጣኔዋ ተንኮታኩቶ እንዲወድቅና ለዘመናት ለቀጠለ የማያባራ ግጭትና የእርስበርስ ጦርነት የተጋለጠችው ብዙሃነትን በአግባቡ ማስተናገድ ባለመቻሏ ነው፡፡ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በገዥዎች የተነጠቁ መብቶቻቸውን ለማስመለስ ታግለዋል፡፡ ለአብነት በ1960ዎቹ በኢትዮጵያ ውስጥ በተደረገው ህዝባዊ ትግል ይነሱ ከነበሩ ህዝባዊ ጥያቄዎች አንዱ የብሄር እኩልነት ነበር፡፡ 

በተመሳሳይ ሁሉንም መብቶች አፍኖ የነበረውን አምባገነኑን የደርግ ስርዓት ለማስወገድ በርካታ ኃይሎች የትጥቅ ትግል ጀምረው የነበሩ ቢሆንም ትክክለኛ ህዝባዊ ዓላማና የትግል መስመር ይዞ የተነሳው ኢህአዴግ ህዝቡን በትክክለኛው ህዝባዊ ዓላማ በማሰባሰብ ትግሉን መርቶ አምባገነኑን የደርግ ስርዓት አስወገዷል፡፡ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በከፈሉት ክቡር መስዋዕትነትም መብቶቻቸውን ያለገደብ ያጎናጸፈና የቃል ኪዳን ሰነዳቸው የሆነውን የዴሞክራሲያዊ  ህገ መንግስት ባለቤት ለመሆን በቅተዋል፡፡ ከዚሁ በመነጨ አዲስ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትም መገንባት ችለዋል፡፡

ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት የነበሩ ጨቋኝ ስርዓቶች ይከተሉት በነበረው የተሳሳተ ሀገራዊ ፖሊሲ በህዝቦች መካከል ቅራኔ እንዲፈጠር አድርገው ቆይተዋል፡፡ እናም አዲስ የጸደቀው ህገ መንግስት በቀጣይነት ለህዝቦች አንድነትና እኩልነት ዋስትና መስጠት ነበረበት፡፡ ህዳር 29 ቀን 1987 ዓም በጸደቀው ህገ መንግስት መግቢያ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መጪው የጋራ ዕድላቸው መመስረት ያለበት ከታሪካቸው የወረሱትን የተዛባ ግንኙነት በማረምና የጋራ ጥቅማቸውን በማሳደግ ላይ መሆኑን ያስቀመጠውም ለዚሁ ነው፡፡ 

በህገ መንግስቱ አንቀጽ 39 ደግሞ የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብት አጎናጽፏቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በህገ መንግስቱ ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብትም ተቀዳጅተዋል፡፡ 

በዚህ መሰረት ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሀብታቸውን፣ ጉልበታቸውን እና እውቀታቸውን አቀናጅተው በጸረ ድህነት ትግሉ ላይ በመረባረብ ላይ ይገኛሉ፡፡ ዋነኛው የልማት መሳርያ የሆነው መሬት በአርሶ አደሩ እጅ ያለ ሀብት በመሆኑ መሬትና ማንኛውንም ሀብት አካባቢያቸውን ለማልማት እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡ 

ከላይኛው እስከ ታችኛው ባሉ የአስተዳደር እርከኖች ራሳቸው በሚመርጧቸው ሰዎች በመተዳደር ላይ ናቸው፡፡ ከቀበሌ እስከ ክልል ራሳቸው በመርጧቸው ሰዎች የሚተዳደሩ ከመሆናቸው በተጨማሪ በጋራ ጉዳዮችም ማለትም በፌዴራል ደረጃ በእኩል ተሳታፊነት መርህን መሰረት በማድረግ ተወክለዋል፡፡ በፌዴራል መንግስት ደረጃ የህዝብ ተወካዮችና የፌደሬሽን ምክር ቤቶች ተጠቃሽ ሲሆኑ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለአንድ ሰው አንድ ድምጽ በሚለው መርህ መሰረት ብሔር ብሔረሰቦች ራሳቸው መርጠው በሚልኩት ተወካዮች እንደ ህዝብ ብዛታቸው በእኩልነት መወከል ችለዋል፡፡ በቁጥር አናሳ የሆኑትም ቢያንስ አንድ የፓርላማ መቀመጫ እንዲኖራቸው ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም በዓይነቱ ልዩ የሆነ ሁሉም ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የተወከሉበት የፌደሬሽን ምክር ቤት ተመስርቷል፡፡ 

የፌዴራል አስፈጻሚ አካላት ለህገ መንግስቱ ታማኝ መሆን፣ ሁሉንም የሀገራችን ህዝቦች በእኩልነት ማገልገልና ብቃት የሚሉ መስፈርቶችን በሚያሟሉ ግለሰቦች ይዋቀራል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በአስፈጻሚው መዋቅርም በተመሳሳይ የብሄር ተዋጽኦ እንዲጠበቅ እየተደረገ ነው፡፡ 

ከላይ ከተጠቀሱ ሁኔታዎች አንጻር ስናየው አዲሱ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለሁሉም ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እኩል የመልማት ዕድልና የስልጣን ባለቤትነት የሰጠ ሲሆን ለአድልዎ በር የዘጋም ነው፡፡ በዚህም መሰረት ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው በማስተዳደር ላይ ናቸው፡፡  በክልሎቹ መልካም ውጤቶች ከተገኙ በዋናነት በየክልሉ ባለ ህዝብና አስዳደር ጥረት የተገኙ ተደርገው የሚወሰዱ ሲሆን ውደቀትም ካለ በተመሳሳይ የእነዚሁ አካላት ኃላፊነት ይሆናል፡፡ 

ሀቁ ይህ መሆኑ እያታወቀ ግን በፌዴራላዊ ስርዓቱ ላይ ያነጣጠረ ዘመቻ ሲደረግ ይስተዋላል፡፡ በተለይም የኪራይ ሰብሳቢነት ወኪል የሆኑት የጠባብነትና ትምክህት ኃይሎች የፌዴራል ስርዓቱ ስራ ላይ ከዋለበት ወቅት ጀምረው ጥላሸት መቀባታቸውን አላቆሙም፡፡  ከ1983 ዓም ዓም በፊት የነበሩት ጨቋኝ ስርዓቶች አምላኪ የሆኑ የትምክህት ኃይሎች ‹‹የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እስር ቤት›› ተብላ እንድትጠራ ምክንያት ሆነው የነበሩ ጨቋኝ ስርዓቶችን በማወደስና ስርዓቶቹ ጥሩ እንደነበሩ አስመስለው በማቅረብ አዲሱን ፌደራላዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለማጥቃት የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ እነዚህ የትምክህት ኃይሎች በህዝቦች የተባበረ ትግል እና ውድ መስዋዕትነት የተወገዱ ስርዓቶች አቀንቃኝ በመሆን የፌደራሊዝም ስርዓቱ ‹‹በታኝ ነው›› በሚል በውሸት ከማጥላላት ጀምሮ በርካታ የፈጠራና የአሉባልታ መረጃዎች ማሰራጨት ከጀመሩ ውለው አድረዋል፡፡ በህዝቦች መካከል መበላለጥ እንዳለ አስመስለው በማቅረብም አዲሱን ስርዓት ለማጥቃት ላይ ታች ሲሉ ይስተዋላል፡፡ 

በተመሳሳይ መልኩ ያለፉት ስርዓቶች በህዝቦች ላይ ያደረሱትን በደል አሁንም እንዳልቀረና እየቀጠለ እንዳለ አስመስለው የሚሰብኩ የጠባብነት ወኪል ኃይሎች በእኩልነትና በመደጋገፍ ላይ በተመሰረተው የፌዴራል ስርዓቱ ላይ የሚያደርጉት አሉታዊ ዘመቻ ቀጥሏል፡፡ 

በህዝቦች ላይ ይደርስ የነበረውን አስከፊውን ጭቆና ለማስወገድ መራራ ትግል አድርጎ ውድ መስዋዕትነት የከፈለው ኢህአዴግ በእኩልነት ላይ የተመሰረተው አዲሱ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲገነባም ጠንካራ ትግል አድርጓል፡፡ የብተና አደጋ ተጋርጦባት የነበረችውን ሀገር አንድነቷ ተጠብቆ እንዲቀጥል የሆነው በኢህአዴግ ግንባር ቀደም ትግል ብሄር ብሄረሰቦች ያጸደቁትን ህገ መንግስትና እሱን ተከትሎ በመፈቃቀድ ላይ ተመስርቶ የተገነባው አዲሱ ፌዴራላዊ ዴሞከራሲያዊ ስርዓት እውን በመሆኑ ነው፡፡

ኢህአዴግ የትምክህትና የጠባብነት አመለካከትና ተግባራት የፈዴራል ስርዓቱ ፈተና ወደማይሆኑበት ደረጃ ለማድረስ በመታገል ላይ ይገኛል፡፡ ሰሞኑን መደበኛ ስብሳበውን ያካሄደው የኢህአዴግ ምክር ቤት የፌደራል ስርዓቱ አድሏዊ እንደሆነ በማስመሰል በትምክህትና በጠባብ ኃይሎች ዘንድ አንዱን የበላይ ሌላኛውን የበታች በማስመሰል የሚቀርበው ፕሮፓጋንዳ መሰረተ ቢስ ከመሆኑም በላይ በህዝቦች ትግል የተመሰረተውን ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን ለማጥቃት ያለመ መሆኑን በመገንዝብ በኋላ ቀር አመለካከቶቹና ተግባራቱ ምህረት የለሽ ትግል መደረግ እንደሚገባም ገምግሟል፡፡  

ኢትዮጵያ የጀመረችውን የህዳሴ ጉዞ ከዳር ማድረስ እና ያለማድረስ ጉዳይ በምናደርገው ትግል ላይ ይወሰናል፡፡ ኢህአዴግ የኪራይ ሰብሳቢነት ወኪል የሆኑት የትምክህትና ጠባብነት አመለካከትና ተግባራት በህዳሴ ጉዞው ላይ የተደቀኑ አደጋዎች መሆናቸውን አውቆ ሲታገላቸው ቆይቷል፡፡ ይሁንና የሚደረገው ትግል ውስንነቶች የነበሩበት በመሆኑ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እነዚህ የትምክህትና የጠባብት አመለካከቶችና ተግባራት ስልታቸውን በመቀያየር ፌዴራላዊ ዴሞከራሲያዊ ስርዓቱን ለማጥቃት እየተረባረቡ ይገኛሉ፡፡

የህዳሴው ጸር የሆኑት እነዚህ አመለካከቶችና እነሱን ተከትለው የሚመጡ አፍራሽ ተግባራትን ለመመከት የሚደረገውን ትግል ማጠናከር ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግናና ስልጣኔ ለማድረስ ወሳኝ ነው፡፡ እናም ትግሉ ከሌሎች የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጋር ተቃኝቶ መሄድ ያለበት ነው፡፡ ኢህአዴግ የህዳሴ አመኬላ የሆኑት የጠባብነትና የትምክህት አመለካከቶችና ተግባራትን የማስወገድ ጉዳይ ለኢህአዴግ ብቻ የተተወ ጉዳይ እንዳልሆነ ይገነዘባል፡፡ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በመፈቃቀድ ላይ የመሰረቱትን ስርዓት ለማጥቃት የሚያሴር ማንኛውንም ኃይል ለመፋለም የሚያደርጉትን ጥረት ከምን ጊዜውም በላይ ማጠናከር አለባቸው ብሎ ያምናል፡፡ 

No comments:

Post a Comment