EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Wednesday 29 March 2017

ኢህአዴግ የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን ለማጠናከር ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ ነው፤ ተደራዳሪ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የጀመሩትን ገንቢ ሚና አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡




በኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) እና በ21ዱ ሀገር አቀፍ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የተጀመረው ድርድርና ክርክር በፓርቲዎቹ መካከል በመደማመጥና በመግባባት መንፈስ ለ7 ዙሮች በተሳካ ሁኔታ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ በእነዚህ የውይይትና የድርድር ጊዜዎች ፓርቲዎቹ የድርድርና የክርክር ረቂቅ ደንቡን በጋራ በማዘጋጀት፣ በውይይት በማዳበርና ገንቢ አስተያየቶችን በመስጠት ሃላፊነታቸውን በመወጣት ላይ ናቸው፡፡ የእስካሁኑ ሂደት የሚያሳየው ፓርቲዎቹ ለዚህ ሀገራዊና ወቅታዊ አጀንዳ ልዩ ትኩረት መስጠታቸውን ነው፡፡

መጋቢት 20/2009 ዓ.ም በተደረገው ውይይት ድርድርና ክርክሩን ማን ይምራው? በሚለው ጭብጥ ዙሪያ ተጨማሪ ጊዜ በመውሰድ ሰፊ ውይይት አድርገዋል፡፡ ፓርቲዎቹ ለሰባት ዙሮች ያደረጓቸው ውይይቶች በፓርቲዎች መካከል ያለው መደማመጥና  ሃሳብን በሰከነ ሁኔታ  በነፃነት የመግለፅ ልምድ እየደበረ መምጣቱን የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡ ዛሬ ለሰባተኛ ጊዜ በተደረገው ውይይት ፓርቲዎች በአገራችን የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲን ለማጎልበትና ወደ አንድ ደረጃ ከፍ ለማድረግ የሚያስችል ቁርጠኝነት እንዳላቸው የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ዛሬ በተደረገው ውይይት ፓርቲዎቹ ውይይትና ድርድሩን ማን ይምራው በሚለው ጭብጥ ላይ ሰፊና ጥልቀት ያለው ውይይት አድርገዋል፡፡ ፓርቲዎቹ መነሻ ምክንያቶቻቸውን በዝርዝር በማቅረብ አቋሞቻቸውን አንፀባርቀዋል፡፡ ኢህአዴግን ጨምሮ አብዛኞቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ‹‹ውይይትና ድርድሩ መመራት ያለበት በራሳችን ነው›› ሲሉ ሌሎች ስድስት ፓርቲዎች ደግሞ ድርድሩን  “ነፃና ገለልተኛ አካል” ይምራው የሚል ሃሳብ አራምደዋል፡፡ ዛሬ በፓርቲዎቹ መካከል በተደረገው የሰከነ ውይይት ድርድሩ በማን ይመራ በሚለው ጭብጥ ላይ አብዛኞቹ ፓርቲዎች የጋራ አቋም ያራመዱ ሲሆን ስድስት ፓርቲዎች የፓርቲ አባሎቻቸውና አመራሮቻቸው ጋር ተጨማሪ ውይይት ማድረግ እንደሚገባቸው በመግለፅ ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ለሚያዚያ ሁለት ተይዟል፡፡

ኢህአዴግን ጨምሮ የድርድሩ አካል የነበሩ አብዛኞቹ ፓርቲዎች ድርድሩን ማን ይመራው? የሚለው ሃሳብ ላይ ጊዜ ከመውሰድ ወደ ዋናዎቹ አገራዊ አጀንዳዎች በመግባት ድርድሩን ማካሄድ እንደሚገባ ሲገልፁ ተደምጠዋል፡፡ ፓርቲዎቹ የሚደረገው ውይይትና ድርድር በራሳቸው በ22ቱ ፓርቲዎች መካከል በየጊዜው በሚዘዋወርና ለሁሉም እኩል እድል በሚሰጥ የአወያይነት ሚና (chairmanship) መፈፀም እንዳለበት ጠንካራ እምነት በመያዝ መነሻ ምክንያቶቻቸውን አስገንዝበዋል፡፡ በዚህም ድርድሩን በራሳቸው በፓርቲዎቹ መካከል ሊሆን ይገባል ያሉበትን ሁለት አበይት ምክንያቶች አስጨብጠዋል፡፡

የመጀመሪያውና ዋነኛው ምክንያት ድርድሩን በራሳቸው በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል እንዲሆን ማድረግ ሂደቱ ላይ የበለጠ መተማመንን ከመፍጠሩም በላይ የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ ስርዓቱን የሚያጠናክረው ነው፡፡ አንዳንድ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች “ነፃና ገለልተኛ አካል” በሚል ሽፋን ድርድርና ክርክሩን የመምራት ሚና በሌሎች ኃይሎች እጅ እንዲወድቅ መፍቀዳቸውም የድርድር ሂደቱን ከማስተጓጎልና በራሳችን የፖለቲካ ጉዳይ ሌላ አካል እንዲፈተፍት ከመፍቀድ የዘለለ ፋይዳ ይኖረዋል ብለው እንደማያምኑና ሂደቱን ለመምራት ፓርቲዎቹ በራሳቸው በቂ መሆናቸውን ብሎም ሉዓላዊነትን አሳልፎ መስጠት እንደማይገባም ኢህአዴግን ጨምሮ አብዛኞቹ ፓርቲዎች አስረግጠው ገልፀዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር የውስጥ ሃይልም ቢሆን ከፖለቲካ ውግንና ነፃ የሚሆን ባለመሆኑ በራሱ የድርድሩ ሂደት ላይ እንቅፋት መሆኑ አይቀሬነቱ አያጠራጥርም፡፡ ከዚህ ነጥብ በመነሳት ኢህአዴግና አብዛኞቹ ፓርቲዎች ራሳቸው የድርድር መድረኩን መምራት አለባቸው ሲባል በቀጣይ በሚከራከሩባቸውና በሚደራደሩባቸው ሀገራዊ የፖለቲካ አጀንዳዎች ላይ “ነፃና ገለልተኛ” የሆነ አካል ሊኖር እንደማይችል ከመገንዘብም ጭምር ነው፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ማንኛውም የውጭም ሆነ የሀገር ውስጥ ሃይል በድርድር ሂደቱ የመሳተፍ ፍላጎት ካለው በታዛቢነት መሳተፍ እንደሚችል፤ ነገር ግን የመድረክ መሪ ሊሆን እንደማይገባ አቋማቸውን ግልፅ አድርገዋል፡፡

በሁለተኛ ደረጃ ኢህአዴግና አብዛኞቹ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚከተሉት የፖለቲካና የርዕዮተ ዓለም ልዩነት እንደተጠበቀ ሆኖ ቁልፍ በሆኑ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ አቋም እያራመዱ በሰጥቶ መቀበል ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ድርድርና ክርክር ይደረጋል ብለው ያምናሉ፡፡ እነዚህ የፖለቲካ አስተሳሰቦችና እነርሱ ላይ ተመስርቶ የሚካሄዱ ክርክሮች ታዲያ የትኛውንም ወገን ወደ አንድ ጎን ስበው አቋም ከማስያዝ የሚቀሩ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ በያዘው አቋም ላይ ተመስርቶ የማደራደር ሚናን የተረከበ ሶስተኛ ወገን ደግሞ ፓርቲዎቹ ላይ ፍላጎቱን ለመጫን የቻለውን ያክል ትግል ማድረጉ አይቀርም፡፡ ይህ በኢህአዴግና በፓርቲዎች መካከል በሚደረጉ ድርድርና ክርክሮች ሊያልፍ የሚገባው ውድ ጊዜ በፍሬ አልባ የሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነትና ይህንኑ ተቃውመው በሚሰነዘሩ አስተያየቶች እንዲባክን እድል የሚከፍት ነው የሚሆነው፡፡ የዚህን ሶስተኛ ወገን ሚና በማሳነስ በተራ የተናጋሪዎች ወረፋ ሰጪነት እንገድበዋለን ሊባል ይችላል፡፡ ይህም ቢሆን ግን እጅ ለሚያወጡ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች በየተራ እድል ለመስጠት ከሆነ ለምን ሌላ ሶስተኛ ወገን አስፈለገ? የሚል ጥያቄን ማስነሳቱ አይቀርም፡፡

ኢህአዴግ እና ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር ሲያደርጉ የአሁኑ የመጀመሪያቸው አይደለም፡፡ ለአብነት በ1997 ዓ.ም የተካሄደውን 3ኛ ዙር ሀገር አቀፍ ምርጫን ተከትሎ ፓርቲዎቹ ተደራድረዋል፡፡ ከ4ኛው ዙር ምርጫ ዋዜማ ጀምሮም ከበርካታ ፓርቲዎች ጋር ኢህአዴግ ተደራድሯል፤ ተከራክሯል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የስነ ምግባር አዋጁን ፈርመው የጋራ ምክር ቤቱን ከመሰረቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋርም በዘላቂነት ውይይቶች በመካሄድ ላይ ናቸው፡፡ እነዚህ መድረኮች ሁሉ የተመሩት በራሳቸው በፓርቲዎቹ ነው፡፡ ይህ መሆኑ ያስከተለው የፍትሃዊነት መጓደል ወይም አላስፈላጊ ጫና አልነበረም፡፡

እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ዋናው የድርድር አጀንዳ ሳይገባ የማቅማማት አዝማሚያ በማሳየት የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲውን የሚያቀጭጭ አቋም ሲያራምዱ ተስተውሏል፡፡ አሁን ላይ ያለበቂና አሳማኝ ምክንያት መድረኮቹ በ“ነፃና ገለልተኛ አካል” ካልተመሩ ሂደቱ ፍትሃዊ አይሆንም በሚል አስቀድሞ የድርድሩን ውጤት ለመፈረጅ የሚደረገው ጥረትና አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ይህን የልዩነት ነጥብ መያዛቸው ድርድሩን ማን ይምራው ከሚል አጀንዳ ባሻገር ያለውን አገራዊ ተልዕኮ ላይ እንቅፋት የሚሆንና ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የትግል መድረኮችን ከማጥበብ የሚዘል ፋይዳ ይኖረዋል የሚል ግምት የለም፡፡ ይህን አቋም የሚያራምዱ ፓርቲዎች በተከታታይ ዙሮች እንደተገለፀው ከኢህአዴግ ጋር የሁለትዮሽ ድርድር፣ በቡድንና ከአጠቃላይ ፓርቲዎች ጋርም ውይይት ለማድረግ ካስፈለገ ክፍት መሆኑ የተገለፀ በመሆኑ የድርድሩ ሂደት ላይ ብቻ በመታጠር ጊዜ መውሰዱ ተገቢ ነው ማለት አይቻልም፡፡ በመሆኑም በዚህ ጉዳይ ተጨማሪ የውይይት ጊዜ የጠየቁ ፓርቲዎች አገራዊ ከሆነው ሰፊ ተልዕኮ በመነሳት ሃሳባቸውን ወደ አብዛኞቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደሚያስጠጉ ይታመናል፡፡

ኢህአዴግ አሁን ለምንገኝበት የዴሞክራሲ ስርዓት እውን መሆን የኢትዮጵያ ሕዝቦች ያደረጉትን መራር ትግል በመምራት ለስኬት ያበቃ ድርጅት ነው፡፡ በዚህ ሂደት ውድ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች የማይተካ ህይወታቸውን ሰውተዋል፤ አካላቸውን አጉድለዋል፡፡ ይህ ዜጎች መስዋዕት የከፈሉለት የዴሞክራሲ ስርዓት በየወቅቱ የሚያጋጥሙትን ተግዳሮቶች እየተሻገረ አስተማማኝ መሰረት ወዳለው የመድብለ ፓርቲ ስርዓት እንዲሸጋገር ኢህአዴግ ዛሬም ተነሳሽነቱን ወስዶ እየሰራ ያለ ፓርቲ ነው፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች እንደገለፀውም አንድም የፓርላማ መቀመጫ ከሌላቸው ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመደራደር ፍቃደኝነቱን ያሳየው ከዚሁ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታው ካለው ፅኑ እምነት በሚመነጭ እና በዳግም ጥልቅ ተሃድሶው ከለያቸው ችግሮች በመነሳት ለሕዝቡ የገባውን ቃል በተግባር ለመፈፀም ነው፡፡

በኢህአዴግ በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል በርዕዮተ አለም ደረጃ ያለው መሰረታዊ ልዩነት እንደተጠበቀ ሆኖ የሀገራችንን የፖለቲካ ስርዓት በማጎልበት ሂደት ውስጥ ሁሉም ተደራዳሪ ፓርቲዎች የድርሻቸውን ሚናና ሃላፊነት እንደሚወጡ ይጠበቃል፡፡ በመሆኑም ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች እስካሁን ባለው ሂደት ያሳዩትን ሙሉ ፍቃደኝነት እያደነቀ በቀጣይም የኢትዮጵያ ሕዝቦችንና የሀገራችንን የፖለቲካ ሉዓላዊነት ያከበረ፣ በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሰረተ የድርድርና ክርክር አቅጣጫን በመከተል ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታው መጠናከር የበኩላቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ ያቀርባል፡፡

መንግስትን እንደሚመራ ገዥ ፓርቲም ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚያቀርቧቸውን ሃሳቦች ለሕዝብ፣ ለሀገርና ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታችን ካላቸው ጥቅም አንፃር በመመዘን የሕግም ሆነ የአፈፃፀም ማስተካከያዎችን ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም ዳግም ያረጋግጣል፡፡ ዛሬ ለሰባተኛ ዙር በተደረገው ውይይት ኢህአዴግና አብዛኞቹ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደገለፁት ድርድሩን ማን ይምራው የሚለው ነጥብ ጊዜ ወስዶ የሚያከራክር ባለመሆኑ ወደ ዋናው አጀንዳ በመግባት ፓርቲዎችም ውክልና ለሰጣቸው አካል በሃላፊነት መንፈስ በመንቀሳቀስ ትልቅና የአገራችንን የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ ስርዓት ሩቅ ሊያደርስ በሚችለው አጀንዳ ላይ መረባረብ የሚገባ ይሆናል፡፡ ዛሬ እንደተስተዋለው ፓርቲዎች በብስለትና በሰከነ መንፈስ ሆነው ጉዳዩን በማጤን ሚያዚያ ሁለት ድርድሩን ማን ይምራው የሚለው አጀንዳ መቋጫ ተበጅቶለት በሙሉ መስማማት ውስጥ ኢህአዴግና ሃያ አንዱ ፓርቲዎች ወደ ቀጣይ የድርድር አጀንዳ እንደሚሸጋገሩ ይጠበቃል፡፡   

No comments:

Post a Comment