EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Tuesday 14 March 2017

ብዝሃነት በህብረ-ብሄራዊ የፌዴራል ስርዓት

(በእውነቱ ብላታ - ሚኒስትር ዲኤታ)
የህብረ-ብሄራዊነት ዋነኛ መገለጫዎች ከሆኑ አበይት ጉዳዮች የብሄር፤ የቋንቋ፤ የሀይማኖት እና የባህል ብዝሃነት ግንባር ቀደም ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ብዝሃነት በህብረ-ብሄራዊ የፌዴራል ስርዓት ውስጥ በሂደት የግድ መፈጠር የሚገባው ነው፡፡ ብዝሃነት ልዩነቶችን በሚያስተናገድ ሥርዓት ውስጥ ከህብረ-ብሄራዊ ውበትነት አልፎ የስርዓቱ ዋልታና ማገር እንዲሁም ምሰሶ ሆኖ በልዩነት ውስጥ ያለውን አንድነት ያጠናክራል፡፡

ብዝሃነት በተሻለ ደረጃ ግልጽነትን ስለሚፈጥር የኪራይ ሰብሳቢነት፤ የጠባብነትናትምክህት እንዲሁም የፀረ ሰላም ኃይሎችን መደበቂያ ዋሻ ለመናድ ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠር እድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ የዘርፋ ጠቢባን ብዝሃነት ከባድና አድካሚ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ሂደት ውስጥ ታልፎ የሚገኝ ወይም የሚደረስ መሆኑን ለማስረዳት ሲሉ ኅብረ ብሄራዊነትን እንደ ድፍድፍ ነዳጅ ሲገልጹት ብዝሃነትን ደግሞ እንደ ተጣራ ነዳጅ እና እንደነጠረ ወርቅ ወይም ውድ ማዕድን ይመስሉታል፡፡ ብዝሃነትን የሚያስተናግድ የአመለካከት የበላይነት ባልሰፈነበት ወቅትም ህብረ-ብሄራዊነትን በህግና በመመሪያ ደረጃ መተግበር የሚቻል ሲሆን ብዝሃነት ግን የህብረ-ብሄራዊነትን የአመለካከት ልዕልና ማረጋገጥን ይጠይቃል፡፡
ሀገራችን ብዙሃነትን ማስፈንና ማክበር ይቅርና በተፈጥሮ ብቻ በውስጧ ያለውን ልዩነት እንኳን ማስተናገድ ተስኗት ነበር፡፡ ህብረ-ብሄራዊት የሆነችው ሀገራችን በውስጧ ያሉትን ልዩነቶች አምና መቀበል ተስኗት ለበርካታ አስርት ዓመታት በእርስ በእርስ ጦርነት ስትናጥና የኋልዮሽ ጉዞ ሽምጥ ስትጋልብ ኖራ ለመናድ ጥቂት እርምጃ ሲቀራት ብረ-ብሄራዊነትን ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀበለችው በሽግግሩ ዘመን ቻርተር፤ ኋላም 1987 በኢፌዴሪ ህገ መንግስት ነው፡፡
ሀገራችን ልዩነቶችን አምና ለመቀበል ረጅም ዘመናትና መራራ ትግል ቢጠይቃትም አሁን ግን ከዚያ ሁሉ አስከፊ የጨለማ ዘመን አልፋ ብዙህነትን በተግባር ለማረጋገጥ ረጅሙን ጉዞ በቁርጠኝነት ጀምራለች፡፡ብዙህነት መረጋገጥ እንደ እኛ ላለ ህብረ ብሄራዊ ሀገር የሰላም፤ የልማትና የዴሞክራሲ ማስፈኛ ወሳኝ መሰረት ስለሆነ በሚገባ አውቀን የበኩላችንን ድርሻ የመወጣት ሀላፊነት አለብን፡፡
በሀገራችን ብዙህነትን እውን ለማድረግ ከሚሰሩ ስራዎች በህብረ ብሄራዊ የፈዴራል ስርዓቱ ላይ በቂ ግንዛቤ፤ መግባባት እና የአመለካከት የበላይነት በሁሉም ደረጃ ማረጋገጥ ይገኝበታል፡፡ በህብረ-ብሄራዊ የፌዴራል ስርዓታችን ውስጥ በተፈጥሮ ያለው ልዩነት በሥራና በሂደት ወደ ብዙህነት ሲያድግ፤ ህብረ ብሄራዊነታችን በተግባር፤ በሥራ ሲረጋገጥ ሀገራዊ ውበታችንና ኩራታችን ይሆናል፡፡ ለብዙህነት መሰረት በሆነው የፌዴራል ሥርዓቱ ላይ በቂ ግንዛቤ ሳይኖር የሚሰራ ስራ ለአንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ግንባታ፤ ለሰላም፤ ለዴሞክራሲና ልማት የሚኖረው በጎ አስተዋፅዎ ባይኖርም አላስፈላጊ የገንዘብ፤ የጊዜ፣ የዕውቀትና የጉልበት ብክነት ማስከተሉ አይቀርም፡፡ ስለ ብዝሃነት መስረታዊ መነሻና መድረሻ በአግባቡ መረዳትና ማስረዳት ሚና ወሳኝ ነው::
በመጀመሪያ ደረጃ ብዙህነት ማለት በተፈጥሮ የሚገኝ በዓይነት ወይም በልዩነት ላይ የተመሰረተ የቁጥር ብዙነት ብቻ ሳይሆን ሙሉ አቅማችንን ተጠቅመን በልዩነቶቻችን ውስጥ ያለውን አንድነት የውበትና የጥንካሬ ምንጭ ለማድረግና ለማጎልበት በቁርጠኝነት በመስራት የሚረጋገጥ የጥምረት እና የጥረት ውጤት የሆነ ህብር ነው፡፡ ብዙህነት የሚሠራበትና በአብሮነት ሂደት ልናሳካውና ልናጎለብተው የምንችል የመስተጋብር ውጤት ነው፡፡ ብዙህነት ማለት በሀይማኖቶችና ተቋሞቻቸው እንዲሁም በብሄርብሄረሰሰቦች ወይም ህዝቦች መካከል ሊኖር የሚገባውን ግንኙነት በመቻቻል፤ በመከባበርና በመረዳዳት ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ህብረት እንዲሆን ለማድረግ በሚፈጠረው መልካም ግንኙነት የሚረጋገጥ የአብሮነት ውጤት ነው፡፡ ብዙህነት እንደ ልዩነት በተፈጥሮ ብቻ የሚገኝ ሳይሆን በተጨባጭ እንዲኖርና አንዲረጋገጥ ለማድረግ ስራን እና ጥረትን የሚፈልግ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህም አኳኋን ሲገነባ በህብረ ብሄራዊ ስርዓት ውስጥ ያለው ልዩነት የውበትና የአብሮነት ማሳያ/መገለጫ ይሆናል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ስንመለከት ብዙህነት ማለት መቻቻል ማለት ብቻ ሳይሆን ልዩነቶቻችንን በፈጠሩት እሴቶች እና ለልዩነታችን መኖር ምክንያት በሆኑ ማንነቶቻችን ላይ መግባባት እና የጋራ ግንዛቤ (መረዳዳትን) መፍጠር ነው፡፡ መቻቻል ለአብሮነት የሚያስፈልግ የጋራ እሴት ቢሆንም ተቻችሎ ለመኖር ግን አንዱ የሌላውን እምነት ምንነት እና ማንነት በጥልቀት ማወቅ አስገዳጅ አይደለም፡፡ የማንነት እና የሀይማኖት ጥንቅሯ ብዙ በሆነባት አለማችን ውስጥ መቻቻል ብቻውን ቁንፅል የሆነ እና ጨለምተኝነትንና ቅድመ-ቅኝት (Stereotypes) ለማስወገድም በራሱ ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ በተለያዩ ማንነቶች እንዲሁም ሀይማኖቶች መሀል ሊወገድ የሚገባው ጨለምተኝነት እስካለ እና እስካልተወገደ ድረስ ጊዜያትን ቆጥሮም ቢሆን በአሉታዊነቱ ዋጋ የሚያስከፍል እዳ ሊሆን ይችላል፡፡ ጨለምተኝነት ደግሞ መወገድ የሚችለውና የሚገባው ባማሩ ቃላት ብቻ ሳይሆን በተግባር በተረጋገጠ ቁርጠኝነት እና የስራ ውጤት ወይም መስዋዕት ነው፡፡
በሦስተኛ ደረጃ ብዙህነት ማለት በተለያዩ ሁኔታዎች በአጋጣሚ የሚፈጠር አንፃራዊነት (relativism) እና እንደየሁኔታው የሚለያይ/የሚቀያየር ሳይሆን በማንኛውም ሁኔታ እንዲኖር ለማድረግ የግድ ዋጋ ወይም መስዋዕት የሚከፈልለት/የሚከፈልበት ነው፡፡ ብዙህነት ዋጋ የሚከፈልለት እንደመሆኑ መጠን በአሁኑ ወቅት ብዙህነትን አስመልክቶ ያለ የአቅጣጫ ምልከታና እርምጃ የማንነት መገለጫዎቻችንን እንድንተው የሚጠይቅ አይደለም፡፡ ይህ ማለት ለአብሮነታችን ሲባል በሀይማኖቶች፣ በብሄር፣ ብሄረሰሰቦች፣ ህዝቦች ወይም ማንነቶች መሀል ያሉ ልዩነቶቻችንን መተው ወይም መካድ ሳያስፈልግ የጋራ በሆኑ ጉዳዮቻችን ላይ ግንኙነቶችን በመፍጠርና በማጠናከር አንድነትንም ጭምር ማረጋገጥ ማለት ነው፡፡
በመጨረሻም ብዙህነትን የውይይት፤ የድርድር እንዲሁም የሰጥቶ መቀበል ባህል መጎልበት ውጤት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ብዙህነት ሰጥቶ መቀበልን መሠረት ያደረገ ድርድርን፤ የጋራ መረዳዳትን እና ግንዛቤ የሚፈልግ ሂደት (ሥርዓት) ነው፡፡ ውይይት የተሳታፊዎች ሁሉ መስማማት ማለት ሳይሆን ለውይይቱና ድርድሩ መሳካት ከመነሻው አንስቶ የሚደረግን ቅን እና ፅኑ ፍላጐትን ጨምሮ መልካም የሆኑ የመወያያ ሃሳቦችን እንዲሁም ጥሩ ንግግርን የሚያስተናግድ ነው፡፡

ይህንንም ለማሳካት ሁለት ነገሮችን መረዳት ይፈልጋል፡፡ በአንደኛ ደረጃ ልዩነታችንን አክብረን በአንድነት ለመኖር የሚጠቅሙን አስተሳሰቦችንና ግንኙነቶችን ማዳበር አለብን፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በዕለት ተዕለት ህይወታችን ውስጥ አንዱ ከሌላው ጋር የሚጋራቸው መደበኛ ያልሆኑ መግባቢያዎች ጭምር ህብረ ብሄራዊነትን የሚያከብሩና የሚያንፀባርቁ መሆን ይገባቸዋል፡፡

No comments:

Post a Comment