EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Thursday 5 January 2017

እውነትም መደገም የለበትም!!


(በኤፊ ሰውነት)
በተቀመጠበት ወንበር ላይ ድርቅ ብሏል፡፡ የጓደኞቹ ጫጫታና ሁካታ ስምጥ ካለበት የሃሳብ ባህር አላባነነውም፡፡ ዝም ብሎ ላስተዋለው በሆነ ጭንቀትና ሃሳብ ውስጥ እየተብሰለሰለ እንደሆነ መገመት አያዳግትም፡፡ እኔም ከጓደኞቹ ተለይቶ እንዲህ መብሰልሰሉ ምን ሃሳብ ቢሸከም ነው በሚል ጠጋ ብዬ ሰላም ወንድሜ ብዬ ትከሻውን ነካ ነካ አደረግኩት፡፡ አንዳች ጅራፍ ያረፈበት ይመስል ለራሴም ድንጋጤ እስኪፈጥርብኝ ድረስ ድንብር ብሎ ተነሳ ግራና ቀኙን እያየ እ እ እ ይቅርታ ሃሳብ ውስጥ ገብቼ ያለሁበትን እንኳን ዘንግቻለሁ አለኝ፡፡ እኔም ሁኔታውን እየተከታተልኩት እንደነበር ነግሬው ከአጠገቡ ካለው ወንበር ላይ ቁጭ ብዬ እንድንጨዋወት ጋበዝኩት፡፡ ለመሆኑ ምንድን ነው በሆድህ የያዝከው ነገር አልኩት፡፡ ምነው ችግር አለ እንዴ? ዓይን ዓይኑን እየተመለከትኩኝ ብታጋራኝ ትንሽ ይቀልህ ይሆናል እናም እስቲ የሆንከውን አጫውተኝ በማለት ተማፀንኩት፡፡


እሱም በፊናው ቀና ብሎ ተመለከተኝና «ይገርመኛል›› ብሎ ጀመረልኝ፡፡ ‹‹ይገርመኛል አንዳንዴ ለምን እንደዛ እንዳደረግኩኝ ለራሴ ሳስበው ይገርመኛል፡፡ ምን ትርፍ አገኘሁ ብዬ ሳስብ የጠፋውን ሳሰላስል በጣም ጭንቀት ውስጥ እገባለሁ፡፡ ራሴን መኮነን ጀምሪያለሁ አለኝ፡፡» ወጣት ሰለሞን ታደሰ (ለዚህ ፅሑፍ ሲባል ስሙ የተቀየረ ነው) ይባላል፡፡ ሰለሞን በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠረው ሁከት ውስጥ ተሳትፈው በማሰልጠኛ ጣቢያዎች የተሃድሶ ስልጠና ሲወስዱ ከነበሩ ዜጎች ውስጥ በጦላይ የተሃድሶ ማዕከል ለአንድ ወር ስልጠና ከወሰዱ 4 ሺህ 35 ሰዎች መካከል አንዱ ነው፡፡

ወጣት ሰለሞን እዚህ ግባ የሚባል የገቢ ምንጭ የለውም፤ ለስራ አጥነቱ ደግሞ መንግስትን ተጠያቂ ያደርጋል፡፡ በበቂ ሁኔታ ስራ አልተፈጠረም የሚል መነሻ አለው፡፡ ይህ አብዛኛው የአገራችን ወጣት የሚያነሳው ተገቢም ትክክለኛም ጥያቄ ነው፡፡ ሰለሞን ይህን ጥያቄ አልያም ቅሬታ መያዙ አይደለም እንዲህ እያብሰለሰለው ያለው ለሁከትና ብጥብጥ እጁን መዘርጋቱ፣ የበርካቶችን ጉሮሮ የሚዘጋ ድርጅትን ለማፈራረስ ማሰቡና እጁን ማንሳቱ ያስጨንቀዋል፡፡  

አለ የሚለውን ጥያቄ ማንሳቱ አሁንም ቢሆን ትክክል ነው የሚል ስሜት ቢኖረውም በተሳሳተ   መንገድ ለመግለፅ በመሞከሩ ምክንያት በሀገርና በወገኑ ላይ ጥፋት ማስከተሉ ግን ከልክ በላይ ቆጭቶታል፡፡ በተለይ ይላል ወጣቱ «እኛ ገና ነን፣ ከድህነት መች ተላቀቅንና፣ ጭራሽ ችግራችንን በማሸነፍ ፈንታ ወደ ኋላ የሚመልስ ተግባር ውስጥ ገብቼ መገኘቴ ይከነክነኛል፡፡ ይህ ደግሞ ፈፅሞ መደገም የሌለበት ማንም ወጣት አይደለም ማድረግ ማስብ እንኳን የማይግባው የተሳሳተ ተግባር ነው» ሲል ፍፁም በመፀፀት ስሜት አጫወተኝ፡፡

ከዚህ ስትወጣ እቅድህ ምንድን ነው አልኩት፡፡ ንግግሬን ሳልጨርስ ከአፌ ላይ ተቀብሎ «ያስቀየምኩትን ህዝብ መካስ አለብኝ፡፡ መልካም ሰው ሆኜ ጥያቄንና የአብዛኛውን ወጣትና ህብረተሰብ ጥያቄና ፍላጎት በሰለጠነ አኳኋን ማቅረብ የምችልበትን እድል ለመጠቀምና ቢያንስ መልካም ሰው ሆኜ ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ መለወጤን በተግባር ለማሳየት ቆርጫለሁ፡፡ በፈጣሪ እምልልሻለሁ በእንዲህ ዓይነት የተሳሳተ መንገድ ደግሜ ላለመጓዝ ለራሴ ቃል ገብቻለሁ፣ በፍፁም አልደግመውም›› አለኝ፡፡ እኔም መፀፀቱ በራሱ በቀጣይነት ለመሻሻል አንድ እርምጃ ወደፊት መሆኑን በማስረዳት ዛሬም አልረፈደም አንተ ራስህን ለውጠህ ሌሎችን ለመለወጥ መስራት ይቅርና ማሰቡ በራሱ መልካም ነገር ነው፤ ሁላችንም በየፊናችን አንዲት ግራም አስተዋፅኦ ማድረግ ከቻልን እኮ ትአምር መስራት እንችላለን፣ በተለያዩ ምክንያቶች አስተዋፅኦ ማበርከት ካልቻልን እንኳን አንተም እንዳለከው በተሳሳተ መንገድ ከመሄድ ከተቆጠብን በጋራ ሆነን የተሻለች ሀገር በመገንባት በዓለም አደባባይ አንገታችንን ቀና አድርገን በኩራት የምንራመድበት ጊዜ ሩቅ እንዳልሆነ ከባለፉት 15 ዓመታት ልምዳችን ተነስተን መደምደም እንችላለን አልኩትና ከሰለሞን ጋር በእንደዚህ ሁኔታ ተለያየን፡፡

ውድ አንባብያን አጋጣሚው ከሰለሞን ጋር አገናኘኝ እንጂ አብዛኛው በተሳሳተ መንገድ ለመሄድ ሞክሮ የነበረው ወገን የሰለሞንን ስሜት እንደሚጋራ እገምታለሁ፡፡ በተለያዩ የተሃድሶ የስልጠና ማዕከላት ሲናገሩ የነበሩ ወጣቶችም ስሜት ይህንኑ ነው የሚያረጋግጠው፡፡ በአገራችን ባሳለፍነው ዓመት የተከሰተው ሁከት በረጅም ካስቀመጥነው ሀገራዊ ራዕይ አንፃር ጎታችና ወደ ኋላ የሚመልሰን አደናቃፊ አስተሳሰብና ተግባር መሆኑ ግልፅ ነው፡፡

በአገራችን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተደነገገበት ዋና መነሻም ይህን ሁከትና ግርግር በአስተማማኝ መንገድ መግታት የሚያስችለንን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ነው፡፡ በተፈጠረው ሁከት ቀላል የማይባል ንብረት ወድሟል በርካታ ቁጥር ያላቸው በተለያዩ ድርጅቶች ተቀጥረው የሚሰሩ ዜጎች ገቢ ቆሟል፡፡ የግል ባለሃብቶችና የመንግስት ንብረት መውደሙ እንደ አገር ከድህነት ለመውጣት የምናደርገውን ጉዞ ከመጎተቱ ባሻገር በአገራችን ለዓመታት የተገነባው ሰላማችን ላይ ጥላ ማጥላቱና ነጋችንን ማበላሸቱ አይቀሬ ነው፡፡ በዚህ የተሳሳተ ተግባር ውስጥ የተሳተፈው የእኛው ዜጋ መሆኑ ደግሞ የጥያቄው ይዘት ምንም ይሁን ምን በእንደህ ዓይነት መንገድ መፈፀም የማይገባው በመሆኑ ነገሩን በማስተዋል እንድንመለከትና ነገም ቢሆን ብዙ ስራ መስራት እንደሚገባን የሚያመላክት ይመስለኛል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከወጣ ጊዜ ጀምሮ በእዚህ ተግባር ውስጥ የተሳተፉ ዜጎችን ሰብስቦ በተለያዩ የተሃድሶ ስልጠና ማዕከላት ውስጥ በማስገባት መንግስት በርካታ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን እያከናወነ ቆይቷል፡፡ መንግስት የራሱን ድክመቶች በዝርዘር ለይቶ የመፍትሄ አቅጣጫ በማስቀመጥ ወደ ተግባር ገብቷል፡፡ ሁከትና ብጥብጥ ወስጥ የተሳተፉ ወጣቶችን በተመለከተ ያሰቀመጠው አቅጣጫም ምንም እንኳን ወጣቶቹ ጥያቄያቸውን ያቀረቡበት መንገድ እና ይህንን ለመተግበር የወሰዱት ኃይል የተቀላቀለበት የተግባር እርምጃ ስህተት ቢሆንም  ሁኔታውን በሆደ ሰፊነት በመከታተል ብስለት የተሞላበት የእርምት እርምጃ እየወሰደ ይገኛል፡፡

ወጣቶቹ በስልጠና ማዕከላት ውስጥ "አይደገምም፣ የወጣቱ ሚና፣ ህገመንግስት፣ የቀለም አብዮት፣ የኢትዮጵያ ሕዳሴና የኢትዮጵያ ታሪክ" በሚሉ ሰነዶች ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን በመስጠት ወጣቶቹ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ግንባታ ላይ አሻራቸውን ማሳረፍ የሚችሉበትን በጎ ራዕይ ለማስጨበጥ የሚያስችል ስንቅ ማስያዝ ችሏል፡፡ ሰልጣኞቹ ከመንግስት ጋር በመሆን ችግሮችን በሰለጠን መንገድ የሚፈቱበትን እድል ብቻ መጠቀም እንዲችሉና ሕጋዊና ሰላማዊ ከሆኑ መንገዶች ውጭ ያሉ አማራጮች ግን የተሳሳቱ ናቸው ብቻም ሳይሆን ዋጋም እንዲሚያስከፍሉ የማስገንዘቡ ጉዳይ በትኩረት ተሰርቶበታል፡፡

በዚህም በኮማንድ ፖስቱ በቁጥጥር ስር የነበሩና በጦላይ ለአንድ ወር የተሃድሶ ስልጠና የወሰዱ 4 ሺህ 35፣ በብርሸለቆ ማሰልጠኛ ተቋም 744 ሰልጣኞች፣ በአዋሽ አርባ ማሰልጠኛ ማዕከል 1 ሺህ 180፣ በአላጌ 1 ሺ 930 ሰልጣኞች፣ በይርጋለም ተሃድሶ ማዕከል የሰለጠኑ 1 ሺህ 813 ወገኖቻችን የተሃድሶ ስልጠናቸውን በማጠናቀቅ ወደ ህብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ተድርገዋል፡፡  በዚህ ጉዳይ የኢፌዴሪ መንግስት ያሳየው ሆደ ሰፊነትና ታጋሽነት ምን ያህል በብስለትና በብቃት እንደተወጣው ለመገንዘብ ተመራማሪ መሆን አያስፈልግም ለሁ፡፡

በጦላይ የተሃድሶ ማዕከል ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ወጣቱ ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መሰረት ጥያቄውን የማቅረብና መልስ የማግኘት ያልተሸራረፈ መብት እንዳለው በመግለፅ የአመጽና ግርግር ተግባራት ውስጥ መሳተፍ ዋጋ እንደሚያስከፍል አስገንዝበዋል፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ በአገራችን የተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ እንዳይደገም መንግሥትም የራሱን ስህተት ለማረም ጥልቅ ተሃድሶ እያደረገ መሆኑን በመግለፅ ወጣቱም እንዲሁ የራሱን ስህተት በማረም ሠላሙን መጠበቅ እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡

ስራ አጥ የሆኑ ወጣቶችም በራሳቸው መንገድ ስራ እንዲፈጥሩ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ያስረዱት ጠቅላይ ሚንስትሩ ወጣቱ ሠላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ የማይነጣጠሉ የአገራችን የህልውና መሰረት መሆናቸውን ተገንዝቦ እነዚህን እሴቶች የመጠበቅም ሆነ የማስጠበቅ ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ጠይቀዋል።

በተመሳሳይ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ለማ መገርሳ ከወራት በፊት በተፈጠረው ሁከትና ግርግር ምክንያት በህይወትና ንብረት ላይ ጥፋት መድረሱን በማስታወስ ይህም በማንኛውም መስፈርት ተቀባይነት የሌለው መሆኑንና ክልሉ ሊለወጥና ሊለማ የሚችለው የክልሉ ወጣቶች ለሠላም በጋራ ዘብ ሲቆሙ እንደሆነ አስገንዝበዋል።

ወጣቶቹ «በሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ግንባር ቀደም ተሳታፊ ሆነው የበደሉትን ሕዝብ በቀጣይ መካስ አለባቸው» ያሉት ደግሞ በብርሸለቆ የተሃድሶ ማሰልጠኛ ተቋም የተገኙት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ናቸው። ቀደም ሲል ተፈጥሮ በነበረው ሁከትና ግርግር በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ እንደነበሩ ያስታወሱት አቶ ገዱ ሰልጣኞቹ በስልጠና ያገኙትን እውቀትና ግንዛቤ በውስጣቸው ከማስገባት ባለፈ በሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ግንባር ቀደም ተሳታፊ መሆን እንደሚገባቸው ገልፀዋል፡፡ አያይዘውም ተመራቂዎች በቀጣይ በመሰል የብጥብጥ ተግባራት መሳተፍ እንደሌለባቸው ገልጸው፣ ሌሎችን በመምከርና ጉዳቱን በማሳየት የአገሪቱ የልማት እንቅስቃሴ እንዳይደናቀፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉም አሳስበዋል።

አዋሽ አርባና አላጌ የተሃድሶ ስልጠና ማዕከላት የተሳተፉ ወጣቶችም አይደገምም ሲሉ በጋራ ድምፃቸውን ሲያሰሙ ተደምጠዋል፡፡ በአዋሽ አርባ የተገኙት የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ በከር ሻሌ በሀገሪቱ የተረጋገጠውን ሰላም፣ ልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ለማስቀጠል የወጣቶች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን በመግለፅ ወጣቶች ከመንግስት ጎን ተሰልፈው ድጋፋቸውን በማጠናከር ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ያለመታከት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ወጣቶች  የአፍራሽ ሃይሎች  መሳሪያ መሆን እንደሌለባቸው ያስታወቁት አቶ በከር በክልሉ ተከስቶ በነበረው ሁከት ውስጥ  በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የተሳተፉ ወጣቶች ከስህተታቸው በመማር  በማዕከሉ ቆይታቸው ያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት ተጠቅመው ለልማትና እድገት ጠንክረው መስራት ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡ በተመሳሳይ በአላጌ ተሃደሶ ስልጠና ማዕከል የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳደር አቶ ኡመር ሀሰን መንግስት ያሉበትን ችግሮች ለመፍታት ያለውን ዝግጁነት በመግለፅ ስራ አጥ ለሆኑ ወጣቶች የስራ እድል የማመቻቸት ስራ በተጠናከረ ሁኔታ እንደሚከናወን አስረድተዋል፡፡ 

"ሃገሪቱ  ወደ ህዳሴ የምታደርገውን ጉዞ ማረጋገጥ የሚቻለው በወጣቱ ተሳትፎ ነው፤ ወጣቱ የጥፋት ሳይሆን የልማት ሃይል መሆኑን መንግስት ይገነዘባል" ያሉት ደግሞ በይርጋለም ተሃድሶ ማዕከል የተገኙት የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደሴ ዳልኬ ናቸው፡፡ የተሃድሶ ስልጠናው የወጣቶችን የልማት አቅም በዘላቂነት ለመጠቀም የሚያስችል ክህሎት ያስጨበጠ መሆኑን የገለፁት አቶ ደሴ በእነዚህ ወገኖች የተፈፀመው ወንጀል በህግ የሚያስጠይቅ ቢሆንም በሁከቱ ተሳታፊ የነበሩ አብዛኞቹ ወጣቶች ባለማወቅና ተገፋፍተው የገቡበት በመሆኑ መንግስት ሁኔታውን ከህዝባዊ ባህሪው በመነሳት መዝኖ ወጣቱ በመልካም ስነምግባር ታንጾና ታድሶ ለውጤታማ ተግባር እንዲነሳሳ በቁርጠኝነት በመስራት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በእነዚህ ማዕከላት የተሃድሶ ስልጠና የወሰዱ ወገኖች መንግስት በህብረተሰቡ ዘንድ የሚነሱ ጥያቄዎችን ታች ድረስ በመውረድ መፍታት እንደሚገባው የገለፁ ሲሆን መንግስት በቀጣይ ለሚያደርገው ማናቸውም የለውጥ እንቅስቃሴ ድጋፋቸውን እንደሚያሳዩና የሚነሱ ጥያቄዎችን ከጥፋት በፀዳ መልኩ ሰለማዊና ሕጋዊ በሆነ መንገድ ብቻ ለማንሳት የተቻላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል፡፡

በተደጋጋሚ ለመጥቀስ እንደተሞከረው በአገራችን በየጊዜው መመለስ የሚገባቸው ጥያቄዎች መኖራቸው በራሱ ችግር አይደለም፡፡ አዳጊ ሀገር ነውና አሁንም በርካታ ጥያቄዎች እንደሚኖሩ ታሳቢ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ጥያቄው በህዝብ ዘንድ መነሳቱም ምንም ክፋት ባይኖረውም ጥያቄው የቀረበበት መንገድ ግን ከኢትዮጵያዊ ጨዋነት ውጭ የሆነና በተለይ ከድህነት ጋር እየታገለች ላለች ብሩህ ተስፋ ያላት አገር ፈፅሞ የማይመጥን መንገድ መሆኑ ላይ መግባባት ያስፈልጋል፡፡

መንግስትም የህዝብ ጥያቄዎችን በተሻለ ሁኔታ ለመመለስ የሚያስችለውን ቁመና ለመገንባት ያላሰለስ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ ይህ መሬት ላይ ወርዶ ለውጥ እንዲያመጣ በሰከነ ሁኔታ ነገሮችን የሚመዝን ወጣትና የህብረተሰብ ክፍል ሊኖረን ይገባል፡፡ በመሆኑም በቀጣይ እንደአገር ለሚከናወኑ የለውጥ ተግባራት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሁኔታዎችን በሰከነ መነፅር መመልከትና የጋራ ቤታችንን በጋራ ለመገንባት ለመረባረብ ቁርጠኛ መሆን ይኖርበታል፡፡ በእርግጥም የትናንቱ ዛሬ አይደገምም፡፡ መደገምም የለበትም፡፡ ከዚህ የተሻለና ለሁሉም ሰላም ወዳድ ኢትዮጵያዊ ልክ የሚሆን የሰለጠነ መንገድ አለና ጥያቄዎቻችንን በሰለጠነ መንገድ ማቅረብን ማስቀደም ይገባናል፡፡


በእኔ እይታ ኢህአዴግ የሚመራው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት ህዝባዊነትና ሆደ ሰፊነት አንዱ መገለጫ ይሄ ነው እላለሁ፡፡ ያጠፋን ከመቆንጠጥና ከማሳደድ በፊት በተገቢው ሁኔታ በመምከር የተከተለው የተሳሳተ መንገዱ ትክክል አለመሆኑን አሳይቶ ማረምና መግራት የብሎሆችና የሩቅ አሳቢዎች ድርጊት ነው፡፡ የኢፌዴሪ መንግሰት ያደረገውም ይህንኑ ነው፡፡ እናም ይህ የመንግስት ሆደ ሰፊነት ሁሌም ቢሆን መርህ ሆኖ መቀጠል ይገባዋል ባይ ነኝ፡፡ ለአኛ የሚጠቅመን ነጋችንን ማበላሸት ሳይሆን ነጋችንን ለማሳመር በሙሉ ልብ መትጋት ነውና ሁላችንም በዚሁ መንፈስ ለህዳሴአችን በጋራ እንረባረብ፡፡ ሰላም!! 

No comments:

Post a Comment