EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Monday 2 January 2017

የመንግስት ሰራተኞች ውይይት ስኬቶቻንን የምናጎለብትበትና ድክመቶቻችንን የምናርምበት ሊሆን ይገባል፡፡

በሀገራችን ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡት ለውጦች የመላ ህዝቡ ተሳትፎ፣ የፈጻሚው አካል ንቁ እንቅስቃሴና የኢሕአዴግ አመራር ድምር ውጤቶች ናቸው፡፡ የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ በቀረፃቸው ፖሊሲና ስትራቴጂዎች እየተመራ ኢህአዴግ የሚጠበቅበትን አበርክቷል፡፡ የህዝቡ ያልተቆጠበ ድጋፍና ተሳትፎ ደግሞ የወጡት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች አተገባበር ውጤታማ እንዲሆን አድርጓል፡፡ በየደረጃው በሚገኙት የመንግስት መዋቅሮች የሚሰራው ፈጻሚው ሃይል ወይም ሲቪል ሰርቫንቱም ከፖሊሲዎቹና ስትራቴጂዎቹ የተቀዱ እቅዶችን መሬት በማስነካት ፍሬ እንዲያፈሩ ተግቷል፡፡ የዚህ ድምር ከትላልቅ ከተሞች ጀምሮ እስከ ገጠር ቀበሌዎች የዘለቀ ለውጥ እንዲመዘገብ አስችሏል፡፡
ባሳለፍናቸው 15 የተሃድሶ ዓመታት በጤና፣ በትምህርት፣ በመሰረተ ልማት፣ በግብርና፣ በተፈጥሮ ኃብት ልማትና በመሳሰሉት ዘርፎች ለውጦች እንዲመዘገቡ ፈጻሚው ወይም ሲቪል ሰርቫንቱ የማይተካ ሚና ተጫውቷል፡፡ በመካላከል ላይ ያተኮረውን የጤና ፖሊሲ አተገባበር ውስጥ በገጠርና በከተማ የእናቶችና የህጻናት ሞትና የተላላፊ በሽታዎች ስርጭት በእጅጉ እንዲቀንስ የጤና ኤከስቴንሽን ሰራተኞችና ሌሎች የመስኩ ባለሙያዎች ተረባርበዋል፡፡ በመልካም ተሞክሮነት የሚጠቀስ ተግባርም ተከናውኗል፡፡ ጤናማ ትውልድን ለማፍራት የተጀመረውን ጥረት ከግብ ለማድረስ ወደፊትም የእነዚህ ባለሙያዎች ድርሻ ከፍተኛ እንደሆነ ኢህአዴግና የኢፌዴሪ መንግስት ይገነዘባሉ፡፡
እንደ ጤና ሁሉ ለዓመታት በከተሞችና በመሃል ሀገር ታጥሮ የቆየው የትምህርት ዕደል ለሁሉም እንዲዳረስ መምህራንና የመስኩ ባለሙያዎች ጥረዋል፡፡ የሀገራችን አስቸጋሪው የመልከዓ ምድር አቀማመጥና የአየር ሁኔታ ሳይገድባቸው ከአርብቶ አደሩና አርሶ አደሩ መንደር ዘልቀው የእውቀት ሻማ ለኩሰዋል፡፡ በነሱ ጥረት ዛሬ ከብዙ የአፍሪካ ሀገራት ድምር የህዝብ ቁጥር የሚበልጥ ቁጥር በላይ ዜጎቻችን በትምህርት ገበታ ላይ ይገኛሉ፡፡
በተመሳሳይ የኢኮኖሚያችን ዋልታ በሆነው የግብርና መስክ ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ ከአርሶ አደሩና ከአርብቶ አደሩ ጋር በየኔነት መንፈስ የግብርና ባለሙያዎች ተረባርበዋል፡፡ የግብርና ግብዓቶችን አርሶ አደሩ እንዲጠቀምና የግብርናውን ስራ እዲያዘምን ግንዛቤ በመፍጠርና በማገዝ በዘርፉ በተከናወነው ስራ ረዥም ርቀት እንድንራመድ አስችለውናል፡፡ ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ ወጥተው ትርፍ ማምረት የቻሉና ወደ ኢንቨስትመንት የገቡ አርሶ አደሮችን መፍጠር የተቻለውም በእነሱ ጥረት መሆኑ የሚዘነጋ አይደለም፡፡  እንደ አጠቃላይ በሀገራችን በሚመረተው ምርት በምግብ እህል ራሳችንን እንድንችል ያደረገው ውጤትም የተመዘገበው የመስኩ ባለሙያዎች ባደረጉት ያላሰለሰ ጥረት ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በመሰረተ ልማት ዝርጋታ፣ በሃይል አቅርቦት፣ በማህበራዊ አገልግሎትና ሌሎች መስኮች ሁሉ በተመዘገቡት ሰፋፊ ድሎች ውስጥ የፈጻሚው አካል ደማቅ አሻራ ይታያል፡፡ በአጠቃላይ በዚህ ሀገር ውስጥ ባለፉት 15 የተሃድሶ ዓመታት የተመዘገቡት ድሎች መሪው ድርጅት ኢህአዴግን ጨምሮ የመላ ህዝቡ፣ የሲቪል ሰርቫንቱና ሌሎች ባለድርሻ አካላት  የጋራ ጥረት ውጤት እንደሆኑ ከላይ የተጠቀሱት እውነታዎች አስረጂ ናቸው፡፡
በእርግጥ እነዚህን ለውጦች ለማስመዝገብ ጉዞው ለመሪው ድርጅትም ሆነ ለፈፃሚዎቹ አልጋ በአልጋ አልነበረም፤ ውጤቱም ቢሆን ልንደርስበት ከሚገባን ጫፍ ያደረሰን አይደለም፡፡ የመጡት ለውጦች የህዝቡን የልማት ፍላጎት እጅጉን የጨመሩና ተስፋ ሰጪ ቢሆኑም በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የህዝቡን እርካታ በሚገባ ያረጋገጡ አይደሉም፡፡ ለዘመናት ከኖርንበት ድህነትና ኋላ ቀርነት እንዲሁም ከህዝቡ የመልማት ፍላጎት ጋር ሲታዩም የሚመጥኑ አይደሉም፡፡
ለዚህ ደግሞ የግብዓት ያለመሟላት፣ የቴክኖሎጂ አቅም ማነስ፣ የአመራር ጉድለትና ሌሎች የሚነሱ ተግዳሮቶችና ምክንያቶች ቢኖሩም በራሱ በፈጻሚው አካል የተፈጠሩ ግድፈቶችም አቢይ ምክንያቶች ናቸው፡፡ ባለው የሰው ኃይልና ባሉት የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ለህዝቡ ተገቢውን አገልግሎት መስጠት አዳጋች ሲሆንብን ታይቷል፡፡ በቁርጠኝነት፣ ታታሪነትና የአገልጋይነት መንፈስ የሚሰሩ የመኖራቸውን ያህል የግል ጥቅማቸውን የሚያሳድዱ፣ በመንግስት አገልገሎት አሰጣጥና ግልጸኝነት ላይ ችግር የሚፈጥሩ ሰራተኞችም አሉ፡፡ መልካም አስተዳደርን በማጓደል፣ በሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ውስጥ የተዘፈቁና የህዝቡን ምሬት ያባበሱ ፈጻሚዎች በመንግስት መዋቅር ውስጥ እንዳሉ ይታወቃል፡፡
ከላይ የተቀመጡት አጓጊ የልማትና የለውጥ ትሩፋቶችን ከዳር ማድረስ የምንችለው መሪው ድርጅትን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የህዝብ ውግንናን በተላበሰ መልኩ ተግባሮቻቸውን መከወን ሲችሉ ብቻ ነው፡፡ በዚህ ቁመና ላይ ለመገኘት ልክ ኢሕአዴግ በውስጡ እንዳደረገው ተሃድሶ ሁሉ ፈጻሚውም አካል በተሃድሶ ሂደት ማለፍና ጉድፎቹን ማራገፍ ይጠበቅበታል፡፡  በድርጅትና በመንግስት ስልጣን ላይ ያለ የተዛባ አተያይን ለማረምና የበደልነውን ህዝብ በልማት ለመካስ በድርጅታችን ውስጥ በጥልቅ ተሃድሶ ዳግሞ የማጥራት ስራ እየተካሄደ እንደሚገኝ ሁሉ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያለው ሰራተኛም የተመደበበትን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጣና ስህተቶችን እንዲያርም ይሄው ሂደት ሊተገበር ግድ ይላል፡፡
በመሆኑም የፈጻሚው አካል የጥልቅ ተሃድሶ ሂደት ከዚህ ሳምንት ጀምሮ ይካሄዳል፡፡ የኢሕአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባደረገው መደበኛ ስብሰባው እነዚህ የመንግስት ሰራተኞችና ሌሎች አካሎች ውይይቶች በጥራት እንዲከናወኑም አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
ውይይቶቹ ስኬታማ የሚሆኑትና የታለመላቸውን ግብ መምታት የሚችሉት ሁሉም ተሳታፊዎች በንቃትና በነፃነት ሲሳተፊ ነውና መድረኮች በዚህ አግባብ እንዲፈፀሙ ባለድርሻ አካላት ሃላፊነታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡

1 comment: