EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Wednesday 30 November 2016

የገባውን ቃል የማያጥፍ ህዝባዊ ድርጅት!


(በኤፊ ሰውነት)
በመኖሪያ ቤታችን፣ በስራ ቦታችን አልያም ደግሞ በትራንስፖርት ላይ፤ ብቻ በያገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ሁላችንም እናወራበታለን፣ እንመካከርበታለንም፡፡ በአቅማችን ይሄ ቢሆን ቢሆን ስንልም ሃሳበችንን እንሰነዝራለን፡፡ ካሳለፍነው ዓመት መጨረሻ የተጀመረው የኢህአዴግና ኢህአዴግ የሚመራው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት በጥልቅ የመታደስ ንቅናቄን ጉዳይ፡፡ በአገራችን ከተከሰተው አለመረጋጋት በኋላ ሁላችንም ሰከን ብለን አገራችንን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ሊያሸጋግር በሚችል ጉዳይ ላይ መምከር እንዳለብን በማመን ኢህአዴግና በእሱ የሚመራው መንግስት በጥልቅ የመታደስ እንቅስቃሴ ከጀመሩ ወራት ተቆጥረዋል፡፡ ይህ በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴ ሂደት በመሆኑ አሁንም የራሱን መልካም ነገሮችን ይዞ መምጣቱ የማይቀር ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ኢህአዴግ ህዝባዊነቱን ጠብቆ ለህዝብ የሚኖር፣ ለህዝብ የገባውንም ቃል ሳያወላዳ የሚፈፅም በመሆኑና እስካሁን ያለው በጥልቅ የመታደስ ንቅናቄ ውጤትም የሚያመላክተው ይሄንኑ በመሆኑ ነው፡፡
ኢህአዴግና መንግስት በሀገር አቀፍ ደረጃ ያጋጠሙንን እንቅፋቶች በማስወገድ አገራችንን ወደ ፊት ለማራማድ የሚያስችለውን በጥልቅ የመታደስ ንቅናቄ መጀመራቸው በህብረተሰቡ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለማስተናገድ የሚያስችል ስብዕና፣ አመለካከትና ብቃት ከመገንባት ባሻገር ለዘመናት የገነባናቸው የጋራ እሴቶቻችንን አደጋ ላይ እንዳይወድቁ በማድረግም የላቀ ፋይዳ ያለው ነው፡፡
ሁላችንም እንደምንገነዘበው ኢህአዴግ ከትጥቅ ትግሉም ጀምሮ ከፊቱ የሚጋረጡ ችግሮችን በብስለት ከህዝብ ጋር እየፈታ ለድል የበቃ ድርጅት ነው፡፡ ጥቂት ሆኖ የጀመረው ጉዞ ዛሬ እልፎችን አፍርቷል፡፡ አለቀላት የተባለችውን አገር ፈፅሞ በማይታመን የለውጥ ምህዋር ውስጥ ማስገባት ችሏል፡፡ ነገ ደግሞ ወደ ቀደመው ስልጣኔዋ የሚመለሳትንና በዓለም አደባባይ ስሟ ከፍ ብሎ የሚጠራበትን የህዳሴ ጉዞ ጀምሯል፡፡ ይህ ለመላው የአገራችን ህዝቦች ብሩህ ተስፋን የሚያስጨብጥና ነገም ህዝባዊ ከሆነውና ሁሌም ቢሆን በቃሉ ከሚኖረው ኢህአዴግ ጋር አገራችንን መለወጥ እንደሚቻል የሚያረጋግጥ ማስተማመኛ ነው፡፡
የመጣንበትም ሆነ ወደ ፊት የምንጓዝበት የለውጥ ጉዞ ከውጭም ይሁን ከውስጥ እንቅፋት የሚያጋጥመው በመሆኑ መውጣት የሚገባን አቀበታማና ኮረብታማ ጉዞ መኖሩ አይቀሬ ነው፡፡ አገራችንን ወደ ፊት ለማራመድ ደግሞ ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘን የማይቻል የሚመስለውንና ጠመዝማዛውን ጉዞ በድል እንደተወጣነው ሁሉ ማናቸውንም እንቅፋቶች መርህ ላይ በመቆምና ከመስመራችን ሳንዛነፍ በብስለት መሻገር ግድ የሚል ይሆናል፡፡ 
ከዚህ አኳያ በአገራችን የተከሰተው ወቅታዊ ችግርም አገራችንን በሩቅ ለማድረስ ካስቀመጥነው ራዕይ አንፃር ሲመዘን የአገራችንን የህዳሴ ጉዞ ወደ ኋላ ሊጎትት የሚችል በመሆኑ ሁለንተናዊ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል የመታደስ ንቅናቄ ውስጥ መገባቱ ተገቢና ነገን አሻግሮ የማየት ውጤት ተደርጎ ነው የሚወሰደው፡፡ ህዝቡ ለሚያነሳቸው ማናቸውም ጥያቄዎች ተገቢውንና ወቅቱን የጠበቀ በሳል መልስ ባለመመለሳችን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ከጊዜ ወደ ጊዜ ስር እየሰደደና እየተከማቸ ሊመጣ ችሏል፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ ደግሞ የሚወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎችም የችግሩን ስፋትና ጥልቀት የማይመጥኑና ለበለጠ መነሳሳት የሚጋብዙ ሲሆን ይታያል፡፡ ስልጣንን ለራስ ጥቅም ማበልፀጊያነት መጠቀም ኢህአዴጋዊ ስብዕና ሊሆን አይችልም፡፡ በመሆኑም ኢህአዴግና መንግስት በየደረጃው አዲስ ካቢኔዎችን በማደራጀት የተሃድሶ እንቅስቃሴውን በስፋት ቀጥለዋል፡፡


በፌዴራል ደረጃ አዲስ የመንግስት ካቢኔዎች ተዋቅረዋል፡፡ ክልሎች ደግሞ ራሳቸውን እያዩና መፍትሄ ያሉትን ርምጃ እየወሰዱ ይገኛሉ፡፡ በኦሮሚያና አማራ ክልል ክልሉን የሚያስተዳድሩ አመራሮችን በአዲስ መልክ አዋቅረዋል፡፡ በትግራይና በደቡብ ክልልም በተመሳሳይ በጥልቅ የመታደስ ንቅንቄው እንደቀጠለ ነው፡፡ ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል የክልሉን ካቢኔ ከማዋቀር ባሻገር የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባና ሌሎች አመራሮችን ሹመትም አፅድቋል፡፡ ይህ ሂደት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ከተሞችን ወደ ተሻለ ልማት፣ ዕድገትና ብልጽግና የሚያደርስ አመራር እንደሚያስፈልግ በመግለፅ የተሾሙት አመራሮችም ይህ ስብዕና ያላቸው መሆኑን የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ ምክር ቤት 12 አዳዲስ የካቢኔ አባላትን ሹመት ከሰሞኑን አፅድቋል፡፡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አዳዲስ ተሿሚዎች የአመራር ብቃትና ህዝባዊ ወገንተኝነት፣ የስራ ልምድና የትምህርት ዝግጅታቸው ህዝብን ለማገልገል የሚያስችላቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የህወሓት/ኢህአዴግ ከፍተኛና የመካከለኛ አመራርም በክልሉ ለሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደርና የልማት ችግሮች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችለውን የተሃድሶ ግምገማ በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ሰሞኑን አዲስ አበባ የፌዴራል ተቋማት አመራሮች ባደረጉት በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ ላይ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችና የሙስና ተግባራትን በማረም፤ ህዝቡ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል፡፡  
ደኢህዴን በበኩሉ ሁሉን አቀፍ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ውይይት በማካሄድ ድምዳሜ ላይ መድረሱን አስታውቋል፡፡ አርሶ አደሩን በተመሳሳይ የእድገት ደረጃ ላይ ለማድረስ የሞዴል አርሶ አደሮችን ተሞክሮ የማስፋትና የሁሉንም አርሶ አደር ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያስችል እንቅስቃሴ እንደሚደረግም ተመላክቷል፡፡ በመግለጫውም በተሃድሶ እንቅስቃሴ በትኩረት ከተወያዩበት ጉዳይ አንዱ የወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት መሆኑ ተገልጿል፡፡ ወጣቶችን ወደ ስራ በማሰማራት ከራሳቸው አልፈው ቤተሰባቸውንና አገራቸውን መጥቀም የሚችሉበት ሁኔታ እንደሚፈጠርም ተገልጿል፡፡
በአጠቃላይ አሁን ባለው ተጨባጭ እውነታ ኢህአዴግና መንግስት ለህዝብ በገቡትና እናሳካለን ባሉት መጠን እየተጓዙ ይገኛሉ፡፡ ይህ የተሃድሶ እንቅስቃሴ አሁን ያልተቋጨና የሚቀጥል መሆኑ በተደጋጋሚ ተጠቅሷል፡፡ አሁን በተጀመረው ልክ እንደሚቀጥልም ሂደቱ ያረጋግጣል፡፡ በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ ዋና ዓላማ ህብረተሰባዊ ለውጥን በማረጋገጥ እንደቀድሞው ሁሉ መንግስትና ህዝብ በጋራ መቀራረብ ፈጥረውና ተባብረው አገራችንን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የሚተጉበትን እድል የሚያሰፋ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እንደ አገር የተጀመረው ንቅናቄ ይህን ለውጥ ለማረጋገጥ በሚያስችል ሂደት ላይ መሆኑን መደምደም ይቻላል፡፡

እስካሁን ያለው ሂደት ጤናማና ነገም በተሻለ መንፈስ የሚቀጥል መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ እኛ አገራችን አንድ ኢትዮጵያ ናት። አገራችንን ለማተራመስ ደፋ ቀና የሚሉ አካላትን ማግለልና እስካሁን የገነባነው ሰላምና እያረጋገጥን ያለነው ልማት እንዳይስተጓጎል መትጋት ይጠይቃል፡፡ ኢህአዴግ ይህ እንዳይደናቀፍ የተፈጠሩ ችግሮችንም በማያዳግም መልኩ እልባት በመስጠትና ነገን መሸከም የሚችል ቁመና በመፍጠር ረገድ ሌት ተቀን እየታገለ ይገኛል፡፡ ትናንት የማይቻለውን ችሎ ከህዝብ ጋር ድል የነሳ፣ ለህዝብ የኖር ድርጅት በመሆኑ ነገም ቃሉን በተግባር ለሚያውለው ኢህአዴግ አቅም ልንሆነው ይገባል ባይ ነኝ።

No comments:

Post a Comment