EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Saturday 3 September 2016

ኢህአዴግ ችግሮችን በሰከነ አኳሃን የመፍታት የዳበረ ልምድ ያለው ድርጅት!

በክሩቤል መርሃጻዲቅ  

በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ የሀገራችን አከባቢዎች እየታዩ ባሉ አላስፈላጊና ባለቤት አልባ ሰልፎች ምክንያት  ኢትዮጵያ በአስቸጋሪ ቀውስ ውስጥ እንዳለች የሚያስቡ ጥቂት ግለ ሰቦች ይኖሩ ይሆናል፡፡  ይህ  ግን መሪ ድርጅቱ ኢህአዴግንና ፌዴራላዊ ዴሞክራሲዊ ስርዓቱን  በአግባቡ ካለ መረዳት የመነጨ ነው፡፡ በአንድ በጸረ ድህነት ትግል ውስጥ ያለች ድሀ አገር እዚህም እዚያም ችግሮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ ብሎ ካለማሰብ የሚነሳም ይመስላል፡፡ በሌላ መንገድ ደግሞ የኢህአዴግ ታሪክና አመጣጥ በውል ካለመገንዘብ የሚመነጭ ስጋትም ይመስላል፡፡ 


ድርጅታችን ኢህአዴግ በችግሮች እየተፈተነ እዚህ አሁን ለደረስንበት የዕድገት ደረጃ ላይ የደረሰ ህዝባዊ ድርጅት ነው፡፡ ከትጥቅ ትግል ጀምሮ ተፈጥራዊና ሰው ሰራሽ ችግሮችን የማይበግረው አስተማማኝ ህዝባዊ መሰረት ያለውና በችግሮች ውስጥ የተፈጠረ- ችግሮችን በብቃት በመፍታት ረገድም የዳበረ ልምድ ያለው ድርጅትም ነው ኢህአዴግ፡፡ ድርጅቱ አምባገነኑን የደርግ ስርዓት ከማስወገድ ጀምሮ በርካታ ውስጣዊና ውጫዊ  ፈተናዎችን በስኬት አልፏል፡፡ በትጥቅ ትግሉ ወቅት በአንዳንዶቹ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች  (ለምሳሌ በህወሓት) በአንዳንድ ወቅቶች ያጋጡሙ የውስጠ ድርጅት ቀውሶች፣ 1993 ዓ.ም ያጋጠመው የጥገኛ ዝቅጠት አደጋ፣ በ1997 ዓ.ም አጋጥሞት የነበረው ፈተና ወዘተ በከፍተኛ ብስለትና በብቃት እየፈታ በድል ጉዞ እየተራመደ በዚያም ራሱን ከፈተናዎች ይበልጥ እየተማረና ለቀጣይ ጉዞው አስፈላጊ ልምድ እያካበተ የመጣ ድርጅትም ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት እያጋጠሙ ያሉትን ችግሮች የተለያዩ መልክ ያላቸው ቢሆኑም በኢህአዴግ የታሪክ መነፅር መመልከት ለፈለገ ግን የሀገር የህልውና ስጋት መሆን ዕድላቸው እጅግ ጠባብ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ አንድ መልክ  ፈጣን ልማቱ  ህዝቡ በርካታ ተጨማሪ ጥያቄዎች እንዲጠይቅ ያደረገው ሲሆን ለፈጣን ጥያቄዎቹ ፈጣን መልስ አለመሰጠት የፈጠረው ነው፡፡ ቁጥሩ ቀላል ያልሆነ ህዝብ ከድህነት ስር መኖርና የበርካታ ወጣቶች የስራ አጥነት ሁኔታም ሌሎች  ተጨማሪ አባባሽ ሁኔታዎች ናቸው ማለት እንችላለን፡፡ የውጭ  ኃይሎች ጉዳይ አስፈጻሚ የሆኑ የትምክህትና የጠባብነት ፊታውራዎችንም እንዲሁ የህዝቡን ጥያቄ ቀምተው የአገሪቱ ሰላምን የማደፍረስ ዓላማ ሰንቀው በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡

 ይሁንና እነዚህ ችግሮች በኢህአዴግ ስኬታማ አመራርና በህዝባችን ያልተገደብ ተሳትፎ አጭር  በሚባል ጊዜ ውስጥ ተፈትው አከባቢዎቹ ወደ መደበኛ  የልማት ሁኔታቸው እንደሚመለሱ ብዙ ምርምር አሊያም መተንበይ ሳያስፈልግ ድርጅቱ ከዚህ  በፊት አጋጥመው ከነበሩ ችግሮችና በወቅቱ የተፈቱበት አገባብ በማየት መደምደም ይቻላል፡፡   ሁከት ተከስቶባቸው ከነበሩ አከባቢዎችም አብዛኞቹ  ወደ መደበኛና የቀድሞው የተረጋጋ ሁኔታ መመለስ ችሏል፡፡ ይህም ሁኔታው ከኢህአዴግ ቁጥጥር ውጭ እንደማይወጣ በማሳያነት የሚወሰድ ነው፡፡

ለዚህም ነው የህዝቡ ጥያቄ የህልውናችን ስጋት ሳይሆን የኢህዴግ ስኬት ተደርጎ መወሰድ ያለበት፡፡ ህዝቡ መጠየቅ ካቆመማ የኢህአዴግ ውድቀት እንጂ ስኬት ሊሆን አይችልም፡፡ ኢህአዴግ በድል ጉዞ እንዲጓዝ የቻለው በሚከተለው ትክክለኛ አቅጣጫ ቢሆንም ያለ ህዝቡ ትብብርና ድጋፍ ግን ውጤት ማምጣት የሚታሰብ አይሆንም፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታም ሲታይ የኢትዮጵያ ህዝብ ሰላምና ልማት ይፈልጋል፡፡ አንዳንዶቹ  ለሁከት መንስኤ እየሆኑ ያሉ ጥያቄዎች  ፈጣን ልማቱን የፈጠራቸውና የልማት ይፋጠንልን ጥያቄዎች  ናቸው፡፡ ከዚህ መረዳት የምንችለው ህዝቡ የበለጠ ልማትና አስተማማኝ ሰላም ይሻል፡፡ ልማቱ በፈለገው ልክ ካልተረጋገጠለትም አፅንኦት ሰጥቶ ይጠይቃል፡፡ መንግስትንም ወጥሮ እስከ መያዝ ደርሷል፡፡

የኢትዮጵያ ህዝቦች የሰላምን ክብርና ዋጋ ምን ያህል እንደሆነ ከታሪካቸው አሳማረው የሚያውቁት እውነታ ነው፡፡ በሰላም መደፍረስ ምክንያት ብዙ በደል፣ ስቃይና እንግልት የደረሰባቸው ህዝቦች ናቸውና፡፡ የሰላም እጦት ያስከተለው ጦርነት የበርካታ ህዝብ ህይወት ሲበላ መኖሩን ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት የነበረ አስከፊው የታሪካቸው ገፅታም ነው ለኢትዮጵያውያን፡፡  ሌሎች በርካቶች ደግሞ ለአካል ጉዳትና ለስደት የተደረጉበት የድቅድቅ ጨለማ ዘመናትንም ተሻግረዋል፡፡  ከዓለም ታላላቅ ስልጣኔዎች ተርታ ይሰለፍ  የነበረው የቀድሞ የስልጣኔ ዘመን ቁልቁል እንዲጓዝ ምክንያት የሆነው የሰላም ማጣት  እንደሆነም ከማንም በላይ ይገነዘቡታል፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያም ከዘመነ መሳፍንት ጀምሮ በተካሄዱ ደም አፋሰሽ እርስበርስ ጦርነቶች የኋሊት ጉዞ ስትጓዝ ኖራለች፡፡ ያለፈው መቶ ዓመታት ጉዞ እንኳን ብንመለከት ሀገራችን በከፍተኛ የሰላም ጥማት ስትሰቃይ እንደነበር በውል እናውቀዋለን፡፡  ለዚህም ነው ለበርካታ ዘመናት አንቀላፍተን ዓለም ወደፊት በሚራመድባቸው አያሌ ዘመናት እኛ ደግሞ ወደኋላ እያዘቀዘቅን መጥተን በስተመጨረሻም የርሃብና የሰቆቃ ተምሳሌት ለመሆን የበቃነው፡፡  በተለይም በቅድመ 1983 ዓ.ም በነበረው ሁኔታ በሀገራችን የተረጋጋ ሰላም ከሰማይ በላይ ርቆን እኛም በድህነትና በኋላቀርነት ስንማቅቅ ኖረናል፡፡

ኢህአዴግ ደርግን አስወግዶ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መከተል ከጀመርን ወዲህ ግን በጸብ አጫሪው የሻዕብያ ስርዓት የተከፈተብንን ወረራ ለመቀልበስ ካካሄድነው ጦርነት ውጭ 20 ዓመታት በላይ የሰላም አየር ስንተነፍስ ኖረናል፡፡ በዚህም መሰረታዊ የህዝብ የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች ጥያቄዎች በማያሻማ መልኩ ሕገ-መንግስታዊ ዋስትና እንዲያገኙ ተደርጓዋል፡፡ አስተማማኝ ሰላም ሰፍኖ ህዝቡ ፊቱን ወደ ልማት በማዞሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ በ ምሳሌነት የሚጠቀስሽ ፈጣን ልማት ማስመዝገብ ጀምረናል፡፡  ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ በርካታ ትላልቅ የመሰረት ልማት ግንባታዎች በሁሉም መስኮችና አከባቢዎች እየተፋጠኑ ነው፡፡  30 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎቻችንም  በትምህርት ገበታ እተሳተፉ ዘመናዊ ዕውቀት እየገበዩ ይገኛሉ፡፡ እናም ሁሉም የሀገራችን ህዝቦች በአሁኑ ስዓት በሥራ ላይ ናቸው፣ ሰለማቸው እንዲደፈርስም በፍፁም አይፈቅዱም፡፡

ከላይ እንደተጠቀሰው በአሁኑ ስዓት መንግስት ለህዝብ ጥያቄዎች አፋጣኝ  ምላሽ መሰጠት ባልቻለባቸው የስራ መስኮችና አካባቢዎች ህዝቡ የተለያዩ ጥያቄዎች በግልፅ እያቀረበ ይገኛል፡፡ በእርግጥ በኢትዮጵያ ውስጥ የጥፋት ማዕበል እንዲቀጣጠል የሚፈልጉ አፍራሽ ኃይሎች ጥያቄዎቹን ቀምተው ሁከትና ትርምስ ለመፍጠር የተለያዩ ሙከራዎች እያደረጉ እንዳሉ ሁላችን በግልፅ የምንገነዘበው ተጨባጭ እውነታ እየሆነ መጥቷል፡፡ ይህ እኩይ ዕቅዳቸው ሊሳካለቸው አልቻለም እንጂ:: ይህ ድብቅ ሴራቸው በመሰረታዊነት ማክሸፍ የተቻለውም ግን በዋናነት ህዝቡ ለሰላሙና ለልማቱ ባለው ከፍተኛ ቁርጠኝነት እንደሆነ ወዳጅም ሆነ ጠላት የተገነዘበው የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡

ሁኔታውን አስመልክተው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ የሰጡት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ሰሞኑን እንዳሉት በአንዳንድ የሀገራችን አከባቢዎች የሚስተዋሉ ችግሮች ምክንያት ኢትዮጵያ ትፈራርሳለች ብሎ ማሰብ የተሳሳተ ግምገማ ነው ወይም ኢትዮጵያን በቅጡ ካላማወቅ የሚመነጭ ነው ብለዋል፡፡“ እዚህም እዚያም ብጥብቶች ሲታዩ ስጋት ቢኖር የሚገርም አይደለም፣ አገራችን አሁን ይቅርና ከዚህ በፊት  እንኳን አልተበተነችም፡፡ በአንድ አላፊ ክስተት የምትበተን አድርጎ የሚያስብ ሰው አገሪቱን  በደንብ የማያወቅ ነው፤ ሀገራችን በአሸዋ ላይ የተገነባች አይደለችም፡፡ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችን በጽኑ መሰረት ላይ የተገነባ ነው፡፡”  ሲሉም አክለዋል፡፡

በየወቅቱ የሚከሰቱ ችግሮች በአግባቡ ካልተፈቱ ከባድ አደጋ የማስከተል አቅም የላቸውም ባይባልም አሁን ካለው ሀገራዊ ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ሲታይ ግን ችግሮቹ  ሀገርን እስከማፍራረሰስ የሚደርስ አደጋ የሚያስከትሉ አይደለም ብሎ መደምደም ይቻላል፡፡ በህዝባዊው ድርጅታችንና በልማታዊ ዴሞክራሲዊ መንግስታችን የሰከነና የዳበረ የችግሮች አፈታት ልምድና ተሞኩሮ በአጭር ጊዜ የሚፈቱ የህዳሴአችን መለስተኛ ተግዳሮቶችም ናቸው፡፡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች  በፍጥነት መመለስና የስርዓቱ አደጋዎች ተብለው የተለዩ ችግሮች ደግሞ በጽናት በመተጋል ህዳሴአችንን እውን የማድረጉ ተልዕኮአችን ለነገ የማይባሉ የህልውናችን ስራዎች እንደሆኑም በሚገባ እንገነዘባለን፡፡

ኢህአዴግ ውስጡን የሚመለከት ድርጅት በመሆኑ በውስጡ የሚታዩ ችግሮች ለማስወገድ የሚያስችል ጥልቅ ተሃድሶ ማድረግ ጀምሯል፡፡ በአንድ እጅ ማጨብጨብ አይቻልምና የሰላሙና የልማቱ ባለቤት የሆነ ህዝብ ሰላሙን ነቅቶ ከመጠበቅ ጎን ለጎን ተሃድሷችን በስኬት እንዲካሄድ የሚያደርገውን ተሳትፎ አጠናክሮ መጠበቅ አለበት፡፡ እጅ ለእጅ ተያይዞን ህዳሴያችንን እውን እናደርጋለን፡፡

1 comment:

  1. EPRDF SHOULDNOT FORGET his grass roots, the people of Tigray needs especial attention due to several man made and natural factors, dear EPRDFs?
    it would have been possible if done properly and with justifiable arguments... i don't think others regions will have a complain. it was a battle field for 100 years, and it is still the Biggest military base due to the No peace and No war status with Eritrea. so many people from inside and Out side have objections to the rule of law in Tigray and discomfort for Eprdf fails to understand the Hearts of many innocent Tigreans who have lost every thing during the war and lost hope and confidence due to the present Mismanagements and lack of Good Governance which should not be in Normal terms in Tigray, if Tigray should have to be a model to others due its experience of its grass root mobilized population and obedience! i call it discipline !!!but why is that not possible???

    ReplyDelete