EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Wednesday 20 July 2016

የጥፋትና ሽብር ቡድኖች መርህ አልባ የተቃውሞ ስልት


(በክሩቤል መርሃጥበብ)    
በሀገራችንና በህዝቦቿ ስም የሚነግዱ ሽብርተኛ የጥፋት ቡድኖች የኪራይ ሰብሳቢነት አጀንዳቸውን ለመሸፈን ሲሉ ያልሆኑትን ይበሉ እንጂ መቼውንም ለኢትዮጵያ አንድነትም ሆነ ለእድገቷ እንደማይቆሙ በእለት ተእለት ተግባራቸው እያረጋገጡ ይገኛሉ። “እንታገልለታለን” ለሚሉት ህዝብ ሰላምን ሳይሆን ጦርነትን፣ ልማትን ሳይሆን ውድቀትን፣ ዴሞክራሲያዊ አንድነትን ሳይሆን የእርስ በርስ መተላለቅን የሚሹ የጥፋት ቡድኖች መሆናቸው ቀድሞውንም ከሚያራምዷቸው የሚምታቱ አቋሞች የታወቀ ነው። ምንጊዜም የኢትዮጵንና የቀጠናውን ሰላም ለማደፍረስ ከማያንቀላፋው የኤርትራ መንግስት ጋር ከመሰለፋቸው በላይ ደግሞ ይህን እኩይ ሴራቸውን የሚያጋልጥ የለም። አሸባሪውን የግንቦት ሰባት ቡድንና መሰሎቹን ከሻዕቢያ ጋር ያስተሳሰራቸው የተዳከመችና ሰላሟ የራቃት ኢትዮጵያን የማየት ህልማቸው እንጂ የመርህ አንድነት ኖሯቸው አይደለም።

እነዚህ ኃይሎች በኤርትራ ላያ እየተከተሉት ያለውን አቋምና አካሄድ ከጥቂት ዓመታት በፊት ከነበራቸው አቋም ጋር አነፃፅሮ ለገመገመ ሰው አቋማቸው ምን ያህል እርስ በርሱ የሚጋጭና መርህ አልባ እንደሆነ ለማረጋገጥ ቀላል ነው፡፡ አሁን የሻዕብያ ተላላኪ በመሆን እያገለገሉ ያሉ የትምክህት ኃይሎች ከተወሰኑ ዓመታት በፊት “የኢትዮጵያ መንግስት ኤርትራን በኃይል በመውረር የዓሰብ ወደብን ማስመለስ አለበት“ በሚል መፈክራቸው የምናውቃቸው ነበሩ፡፡ ኢህአዴግን ለማብጠልጠል ሲሉም ይህንን አጀንዳ ለዓመታት አራግበውታል፡፡ አንዳንዶቹ ከዚህ በፊት በተካሄዱ ጠቅላላ ምርጫዎች የሚሳተፉ ነበሩና ምርጫ በመጣ ቁጥር በዚሁ አጀንዳ ድምጽ ለማግኘት ብዙ ደክመዋል፡፡ “ኢህአዴግ ደርግን ለመጣል ባደረገው ትግል ከሀገር ገንጣዩ ሻዕብያ ጋር አብሯል” ብሎ በመክሰስም እነዚህን ኃይሎች የሚስተካከል አልነበረም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝቦች ግን የእነርሱን መሰሪ አመለካከትና ተግባር እያከሸፉና ድምፃቸውን እየነፈጉ ህዳሴያቸውን በማፋጠን ላይ ናቸው፡፡
ኪራይ ሰብሳቢ ሃይሎች ወጥ አቋም ኖሯቸው አያውቅምና ከትናንት አቋማቸው 360 ዲግሪ ዞረው በተቃራኒው ቢሰለፉ የሚገርም ባይሆንም መነሻቸውን መረዳት ግን ይገባል። ለእነዚህ ጽንፈኛ ኃይሎች አገርና ህዝብ ማለት የግል ጥቅማቸው ብቻ ነው፡፡ ከዚህ የአጭር ጊዜ ጥቅምና በዘላቂነትም ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሰፍን የሚመኙትን የኪራይ ሰብሳቢነት ስርዓት እንዳይዘረጉ “እንቅፋት” የሆነባቸውን ስርዓት ለማስወገድ ያስችለናል ብለው ስላሰቡ ከአቋማቸው በአንዴ ተገልብጠው ‘የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው’ በሚል አመክንዮ ብቻ ሻዕቢያን ጨምሮ የኢትዮጵያን በጎ ከማይመኙ ሃይሎች ጋር አብረዋል፡፡
ከዚህ በመነሳት አዲስ አበባንና ሌሎች አካባቢዎችን እንደ ባግዳድ ለማድረግ ተልዕኮን ከመቀበል ጀምረው በተለያዩ የዓለም አደባባዮች ሻዕቢያን የመሰለ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት የለም ብለው እስከመስበክ ደርሰዋል፡፡  ከአንድ ዓመት በፊት አስመራ ድረስ ሂደው ከአምባገነኑ ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ቃለ መጠይቅ ያደረጉ የኢሳት ጋዜጠኞች ኢሳያስ አፈወርቂ ከማንም በላይ ለኢትዮጵያ አንድነት የሚጨነቅ ሰው እንደሆነ፣ እንደውም ለኢትዮጵያ አንድነት ሲል እንቅልፍ አጥቶ እንደሚያድር ምንም ሳያፍሩ ነግረውናል፡፡ ኢትዮጵያን ለማተራመስ በዓለም የሚገኝ ማንኛውንም ሃይል ለማገዝ ቆርጦ የተነሳው የኤርትራ መንግስትም የጽንፈኞቹ ጥሩ የገንዝብ ምንጭ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ እነርሱም የኤርትራ መንግስት በሚሰጠው አቅጣጫ መሰረት “አቤት”፣ “ወዴት” በማለት ታማኝ ሎሌነታቸውን አሳይተዋል፡፡
በኤርትራ ስልጣን ላይ ያለው ገዢ መደብ በጎረቤት ሃገራት ላይ ካደረገው ግልፅ ወረራ ጀምሮ በስውር የቀጠናውን ሰላም ለማደፍረስ ለአሸባሪ ሃይሎች በሚያደርገው ድጋፍ የተነሳ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ተደጋጋሚ ውግዘትና ማዕቀብ ሰለባ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይባስ ብሎ ደግሞ አስተዳድረዋለሁ በሚለው ህዝብ ላይ በሚያደርሰው እስራት፣ ግርፋትና ሞት ይወነጀላል፡፡ የተባበሩት መግስታት ድርጅት (ተመድ) የሰብአዊ መብት መርማሪ ኮሚሽን ይህንኑ ከመረመረ በኋላ የሻዕቢያ መንግስት በኤርትራ ህዝብ ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየፈፀመ መሆኑን የሚገልፅ ሪፖርቱን ባሳለፍነው ወር ይፋ አድርጓል፡፡ ይህን ተከትሎ አለም አቀፍ ጫናና ውግዘት የበዛበት ሻዕቢያ የአለም ህብረተሰብን የትኩረት አቅጣጫ ለማስቀየር ሲል በሃገራችን ላይ ግልፅ ወረራ ፈፅሟል፡፡ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትም አፀፋዊ እርምጃ በመውሰድ ወረራውን ቀልብሷል፡፡
ይህ ክስተት ፀሃይ ከሞቀው የሻዕቢያ መንግስት ጠብ አጫሪነት ባህሪ ይበልጥ በሀገራችን ስም የሚነግዱ አሸባሪ ቡድኖችን ባህሪ ገሃድ እንዲወጣ አድርጎ አልፏል፡፡ መከላከያ ሰራዊታችን የወሰደውን እርምጃ ተከትሎ ግንቦት 7 እና ተከታዮቹ ጽንፈኛ ኃይሎች የኢትዮጵያን ራስን የመከላከል መርህን የተከተለ ተመጣጣኝ እርምጃ ከመቃወም ጀምረው ሁለቱም አገሮች ወደ ጦርነት ቢገቡ ከኤርትራ መንግስት ጋር እንደሚሰለፉ ያሳዩት አቋም የጥፋት ኃይሎቹ መርህ አልባ ጸረ ህዝብና ጸረ ሀገር አቋም ያሳየ ነው፡፡
እነዚህ የሽብር ሃይሎች በተጨማሪም የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርትን በመቃወም ከሻዕቢያ ጋር በአንድነት “ተራ ውንጀላ” ብለውታል፡፡ ቀድሞውንም ፍጹም ከህዝባዊነት የራቁ እንደሆኑ የታወቁ ቢሆኑም በዚህ ደረጃ የኤርትራን ህዝብንና ዓለም አቀፍ ማህበረሰብን ተቃውመው ይቆማሉ ተብሎ የሚታሰብ ስላልሆነ አቋማቸውን አስገራሚ አድርጎታል፡፡ በመላው ዓለም የሚገኙ ኤርትራውያን የኮሚሽኑን ሪፖርት ደግፈው የኤርትራ ባለስልጣናት ለፍርድ እንዲቀርቡ በሰላማዊ ሰልፍ ሲጠይቁ የእኛዎቹ አሸባሪዎች ደግሞ አይናቸውን በጨው አጥበው የኤርትራ ህዝብ በጥሩ ሁኔታ እንዳለ መስበክን ተያያዙት፡፡ ከኤርትራ መንግስት የሚወረውሩላቸው ጥቂት ብሮች ለመለቃቀም ሲሉ ኤርትራውያን በየቀኑ አገራቸው ጥለው እንዲሰደዱ፣ በዚህም ኤርትራ ከአፍሪካ በስደተኞች ብዛት አንደኛ በዓለምም ከሶርያና አፍጋኒስታን ቀጥላ እንድትጠራ ያደረገውን መንግስት ደግፈው ከዓለም ማህበረሰብና ከእውነት በተቃራኒው ተሰልፈዋል፡፡ አንድ የግንቦት ሰባት አመራር የኤርትራ መንግስት ህዝቡን የሚወድና ከጥፋት ነጻ እንደሆነ ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸው ‹‹በኤርትራ ምርጫ ቢደረግ ህዝቡ ሻዕብያን ይመርጣል›› በማለት ወረታውን ለመቀበል ሲሉ የኤርትራ መንግስትን አስደስተዋል፡፡
ኢህአዴግና በኢህአዴግ የሚመራው የኢፌዴሪ መንግስት ግን በኤርትራና ስልጣን ላይ ባለው ቡድን ላይ የሚከተሉት ፖሊሲ ግልጽና የማያወላውል ነው፡፡ ኢህአዴግ በኤርትራ በስልጣን ላይ ያለው ቡድን ጸረ ዴሞክራሲያዊ እንደሆነ ገና ከትጥቅ ትግል ጀምሮ የተገነዘበውና በተለያዩ ሰነዶቹም በግልጽ ያስቀመጠው ጉዳይ ነው፡፡ በኤርትራ ህዝብ ፍላጎት መሰረት ኤርትራ ነጻ አገር ከሆነች ወዲህ በመልካም ጉርብትና ላይ የተመሰረተ የሁለትዮሽ ግንኙነት ለመመስረት ጥረት አድርጓል፡፡ አከባቢውን ለማተራመስ ቆርጦ የተነሳው የኤርትራው መንግስት ግን ገና አገር ማስተዳደር ከጀመረ ማግስት ጀምሮ መጀመሪያ የመንን፣ በመቀጠል ጂቡቱንና ሱዳንን በኃላም ኢትዮጵያን በመውረር ከሁሉም አጎራባች አገሮች ጋር ወደ ግጭት ገብቷል፡፡
በጠብ አጫሪው የሻዕብያ መንግስት ምክንያት በሃገራቱ መካከል ሰላም ማስፈን ባይቻልም በኢህአዴግ የሚመራው መንግስት ካለው የህዝባዊነት መንፈስ በመነሳት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ እንዲጠናከር እየሰራ ይገኛል፡፡ በየቀኑ ከስርዓቱ ለማምለጥ እግሬ አውጪኝ ብለው ለሚሸሹ ኤርትራውያን መጠለያ ከመስጠት ጀምሮ ወጣት ኤርትራውያን በኢትዮጵያ በሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመማር ዕድል እንዲያገኙ እየተደረገ ነው፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ በኤርትራ ያለው መንግስት ለሚያደርገው ትንኮሳ ተመጣጣኝ ምላሽ መስጠትም ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ የፈፀመችውና አሁንም የምትከተለው አቋም እንደሆነ ገልፃለች፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ከድህነት ለመውጣት በሩጫ ላይ ያሉ በመሆናቸው እያንዳንዱ የሰላም ደቂቃ ዋጋ አላት፡፡ እናም ጦርነት የሚመረጥ አይደለም፡፡ ሆኖም የኤርትራ መንግስት ትንኮሳ ማድረጉን መርጦ በዚህ ድርጊት የሚቀጥል ከሆነ በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት በኤርትራ መንግስት ላይ አስፋላጊውን እርምጃ መውሰድ ተገቢ ይሆናል፡፡ 

No comments:

Post a Comment