EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Thursday 28 July 2016

ዋናው የልማት ሃይል ህዝቡና አምራቹ የግል ባለሃብት ነው።

(በአደም ሐምዛ)
ኢትዮጵያ በቀጣይ በጀት አመት ለምታከናውናቸው ተግባራት ማስፈጸሚያ የሚውለው የፌዴራል መንግስት በጀት 274.3 ቢሊዮን ብር ሆኖ ጸድቋል፡፡ ይህ በጀት በ2008 ዓ.ም ከነበረበት 223.4 ቢሊዮን ብር በ50 ቢሊዮን ብር በላይ ወይም በ12.3 በመቶ እድገት አሳይቷል፡፡ ከ10 ዓመት በፊት ከ32 ቢሊዮን ብር የማይዘል የነበረው የፌዴራል መንግስት ዓመታዊ በጀት ከስምንት እጥፍ በላይ አድጎ ነው እንግዲህ ዘንድሮ 274.3 ቢሊዮን ብር የደረሰው። ሀገራችን በየበጀት ዓመቱ ለምታቅዳቸው የሰላም፣ የዴሞክራሲ፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት ማስፈፀሚያ የምትበጅተው የገንዘብ መጠን ሊያድግ የቻለበት ምክንያትና በጀቱን ማሳደግ ያስፈለገበት ምክንያት ተመጋጋቢ ናቸው።

በተከታታይ ከ12 አመታት በላይ የተመዘገው ሀገራዊ እድገት ምጣኔው ቢለያይም በሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ የጎላ አዎንታዊ ተፅዕኖ አሳርፏል። ይህን ተከትሎ በየዓመቱ እያደገ ያለው ዓመታዊ ሀገራዊ የምርት መጠን ከዜጎችና ከአምራችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚሰበሰበው የግብር መጠን እንዲያድግ ቀጥተኛ አስተዋፆ አድርጓል። ይህ ሀገራችን ከውጭ ከምታገኘው ብድርና እርዳታና ከሌሎች የመንግስት ገቢዎች መጨመር ጋር ተደምሮ የፌዴራል መንግስትን ዓመታዊ የበጀት መጠን በቀጣይነት እያሳደገው ይገኛል።
የበጀቱን እድገት ያክል ታዲያ መንግስት በተለያዩ ዘርፎች አቅዶ የሚፈፅማቸው ተግባራትም በመጠንም ይሁን በአይነት በከፍተኛ ደረጃ ማደጋቸው አልቀረም። በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ለተያዙ ግዙፍ ፕሮጀክቶች፣ በህብረተሰቡ ለሚነሱ አዳዲስና አዳጊ የመልማት ፍላጎቶች መንግስት ተገቢውን ምላሽ መስጠት እንዲችል ተጨማሪ በጀት ማስፈለጉ ግድ ነው። የኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀፅ 41 በሚደነግገው መሰረት መንግስት ለጤና፣ ትምህርትና ሌሎች የማህበረሰብ አገልግሎቶች በየአመቱ እያደገ የሚሄድ በጀት መመደብ አለበት። የዘንድሮው በጀት በተለይ ደግሞ በሀገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት ሊተካ የማይችለውን የሰለጠነ የሰው ሃብት በማልማት ትልቅ ድርሻ ያላቸውን መምህራንን የደረጃ እድገት ማስተካከያ ለመተግበር እስከ አምስት ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት መያዝ አስፈልጓል። ባሳለፍነው በጀት ዓመት ኤልኒኖ ያስከተለውን የድርቅ አደጋ ለመከላከል መንግስት 16 ቢሊዮን ብር በመበጀት ለዜጎች በርካታ ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱ የሚታወቅ ነው። የዘንድሮው በጀት በተጨማሪም በኤልኒኖ ክስተት በድርቅ የተጎዱ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋምና ድርቁ በእድገታችን ላይ ያስከተለውን ተፅዕኖ እንዲያካክስ በሚያስችል ምርታማነት ላይ ለመሰማራት የሚያስችል በጀት መያዝን ታሳቢ ያደረገም ነው፡፡
እነዚህን ተግባራት ታሳቢ አድርጎ ከፀደቀው በጀት 214.2 ቢሊዮን ብር ያክሉ ከሀገር ውስጥ የገቢ ምንጮችና ከውጭ እርዳታና ብድር የሚሰበሰብ ሲሆን ቀሪው ግን በሀገር ውስጥ ብድር የሚሸፈን ነው፡፡ ይህ በበጀት ቀመሩ ላይ የሚታየው የበጀት ጉድለት ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ጋር ሲነፃፀር ከሦስት በመቶ ያነሰ በመሆኑ ጤናማ ተደርጎ የሚወሰድ ነው። በ2009 በጀት ዓመት ከአጠቃላይ ሀገራዊ እድገቱ ጋር ተያይዞ የሚኖረው የሀገር ውስጥ የምርት እድገት ከ18 በመቶ በላይ እንደሚሆንና የዋጋ እድገቱ ከ8 በመቶ እንዳይበልጥ ታሳቢ ያደረገ የበጀት እቅድ መሆኑም የበጀት ጉድለቱ በኢኮኖሚ እድገቱ ላይ አሉታዊ አስተዋፆ እንደማያሳርፍ የሚያሳይ ነው።
ይህ እንዳለ ሆኖ ይህንኑም ቢሆን ለመሸፈን በሚደረገው እንቅስቃሴ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት ጥንቃቄ የተደረገበት ነው። መንግስት ጉድለቱን ለመሸፈን ከሀገር ውስጥ ባንኮች በሚበደርበት ወቅት በባለሀብቶች የብድር ፍላጎት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ በመፍጠር በግሉ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚደረግ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ከዚሁ በተጓዳኝነት የሚተገበሩ የበጀትና ፋይናንስ ስርዓቶች ጉድለቱን በማጣጣም ትልቅ ድርሻ ያበረክታሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በጀቱ በዚህ ደረጃ ወቅታዊና የተለመዱ የፌዴራል መንግስት የልማት ስራዎችን ታሳቢ አድርጎ የተዘጋጀና እስካሁን ሲመደብ ከነበረው በጀት ከፍተኛ ጭማሪ ያለው ቢሆንም ሀገሪቱ በየዓመቱ በምታከናውናቸው ዘርፈ ብዙ ተግባራት ዜጎች ሊኖራቸው የሚገባውን ድርሻ ሊተካው የሚችል አይሆንም፡፡ ዋናውና አብዛኛው እቅድ ተፈጻሚ የሚሆነው ህብረተሰቡ ጉልበቱን፣ እውቀቱን፣ ገንዘቡንና ጊዜውን አስተባብሮ በየልማት መስኮቹ በሚያከናውነው የተደራጀ ህዝባዊ ንቅናቄ አማካኝነት ነው፡፡ እያንዳንዷ የተበጀተች ሳንቲም ለታለመላት አላማ መድረሷን ማረጋገጥ በርግጥም አስፈላጊ ቢሆንም የልማት ስራችን በዚህ በጀት ላይ የተንጠለጠለ ከሆነ ግን ውጤቱ አርኪና ጠብ የሚል አይሆንም። ምክንያቱም ዋናው የልማት ሃይል ህዝቡ ነውና።
ዋናው የልማት ስራ ህዝቡን በሰፊውና በዴሞክራሲያዊ አኳኋን ለልማት በማንቀሳቀስ የሚሰራው ነው። ቀጥሎ ትልቅ ሚና የሚጫወተው አምራቹ የግል ባለሃብት ነው። የዚህ በጀትና የመንግስት ሚና ለነዚህ ቁልፍ ሃይሎች የተመቻቸ ሁኔታ መፍጠር ነው። ለአብነት በሁሉም ክልሎች በስፋት ተግባራዊ እየተደረገ ያለውንና በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች የሚሳተፉበትን የተፋሰስ ልማት ስራን ብቻ ብንወስድ እጅግ ከፍተኛ የመንግስት ወጪን የሚተካ ነው፡፡ ሁሉንም ወጪዎች በመንግስት አቅም መሸፈን አሁን ባለንበት የእድገት ደረጃም ሆነ ወደፊት የማይቻል ብቻ ሳይሆን ተፈላጊም አይደለም፡፡ በመሆኑ በየዓመቱ አድጎም ቢሆን የሚበጀተው በጀት ህብረተሰቡ በራሱ ሊያከናውናቸው የማይችሉ ተግባራትን ለማስፈጸም ከማገዝ ያለፈ ሚና የለውም፡፡
ህብረተሰቡ በራሱ ጉልበቱን፣ እውቀቱን፣ ገንዘቡንና ጊዜውን አስተባብሮ በየዓመቱ የሚያከናውናቸውን የልማት ስራዎች አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለ ሆኖ የተበጀተውንም ውስን ገንዘብ ቢሆን ውጤታማ በሆነ መልኩ መጠቀም ልዩ ትኩረትና ጥንቃቄ የሚሻው ነው። በጀቱን ወሳኝ ለሆኑ በተለይም ድህነትን በእጅጉ ለመቀነስ በሚያስችሉና ዘላቂታዊ ጠቀሜታ ባለው ኢኮኖሚያዊ ሽግግርን ለሚያሳኩ መስኮች በቅድሚያና በበቂ ሁኔታ የማዋል ጉዳይ በበጀት ዝርዝሩ ላይ የተመላከተና በአግባቡ የተብራራ ቢሆንም አፈፃፀሙም በዛው ልክ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነው። የበጀት አጠቃቀም ስርዓቱን ወጪ ቆጣቢ ማድረግና ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን ማስወገድም እንዲሁ፡፡
ውጤታማ የበጀት አጠቃቀምን ከመተግበር ጎን ለጎን ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ የመንግስት ገቢን ቀጣይነት ባለው መልኩ ማሳደግ ነው። ሀገራዊ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን የገቢ አቅም አሟጦ መጠቀም ቢቻል ከታክስ ብቻ እስከ 25 በመቶ መሰብሰብ የሚቻል ቢሆንም በእኛ ሀገር ሁኔታ የሚሰበሰበው ከሀገራዊ አመታዊ ምርት ከ13 በመቶ የዘለለ አይደለም፡፡ ይህ በአፍሪካ ካለው አማካኝ 17 በመቶ እንኳን ሲነፃፀር ገና ያልተጠቀምንበት አቅም እንደሆነ መረዳት ይቻላል። በመሆኑም በገቢ አሰባሰብ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታትና ተቋማዊ አቅምን በማጎልበት አስተማማኝ ሀገራዊ አቅም መገንባት ያስፈልጋል።

No comments:

Post a Comment