EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Sunday 24 July 2016

ትምክህትና ጠባብነት የሚታረሙት ቀጣይነት ባለው የአመለካከት ለውጥ ነው

(በሓዱሽ ካሡ)
እያገባደድነው ባለነው አመት በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ደም አፋሳሽ ግጭቶች ተከስተዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል የተወሰኑ አካባቢዎች እንዲሁም በሰሜን ጐንደር ዞን አንዳንድ ወረዳዎችና በቅርቡም በጎንደር ከተማ በፀረ ሰላም ሀይሎች የጥፋት ሴራ የበርካታ ሲቪልና የፀጥታ አስከባሪ አባላት ህይወት ጠፍቷል፡፡ ህዝቡ ሰላም አጥቷል፣ በሚልዮኖች ብር የሚገመት ንብረትም ወድሟል፡፡ በየአካባቢው የተነሳውን እሳት ህዝብና መንግስት ተቀናጅተው በኃላፊነትና አስተዋይነት መንፈስ ባያጠፉት ኖሮ ማቆሚያ የሌለው ጥፋት ይከሰት እንደነበረ አያጠያይቅም፡፡ በተለይ የየአካባቢዎቹ ነዋሪዎች መንግሥት ህገ ወጥነትን ለመከላከል የወሰዳቸውን ሕጋዊ እርምጃዎች ደግፈው በመቆም ለሰላማቸው ዘብ ሆነዋል፡፡ መላ ህዝቡ ያደረገው አመፅንና ረብሻን የመከላከል ሂደት እዚህም እዛም በአፍራሽ ኃይሎች መሪነት የተቀሰቀሱት ግጭቶችና ጥፋቶች ጥቂቶች ስውር አላማቸውን ለማሳካት ሲሉ ያራመዱዋቸው እንጂ የህዝቡ አጀንዳዎች እንዳልሆኑ በገሃድ አሳይቷል፡፡

በዚህ ጽሑፍ አቅራቢ አተያይ ችግሩ ከኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት የሚመነጭ ነው፡፡ መንስዔው ትምክህት፣ ጠባብነትና አሸባሪነትን የመሰሉት የኪራይ ሰብሳቢነት መገለጫዎች የጋራ ግንባር ፈጥረው ለጋውን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብና ተግባር ግራና ቀኝ ለማላጋት ቀንና ሌሊት በመራወጥ የደቀኑት አደጋ ነው፡፡ የእነዚህ አመለካከቶች ተሸካሚዎች መርዘኛና አጥፊ የሀሰት ፕሮፓጋንዳቸውን በመርጨት፣ የተወሰኑ ወገኖችንም በማደናገር ጥፋቶች ፈፅመዋል፡፡ እነዚህ የጥፋት ተግባሮች ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት ወዳድ የሆኑትን የኢትዮጵያ ህዝቦች እንዲሁም ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ኃይሎችን በማሳሰብ ላይ ናቸው፡፡ ይህ አይነት አስተሳሰብና ተግባር በእንጭጩ ካልተቀጨ ሊያስከትለው የሚችለውን መዘዝና አደጋ ለመገመት ይከብዳል፡፡
በርግጥ ግጭቶቹ በተከሰቱባቸው አካባቢዎች አሁን መረጋጋት ሰፍኗል። ይሁንና ችግሩ ዘላቂ እልባት አግኝቷል የሚያሰኝ አይደለም፡፡ ያም ሆኖ ችግሩ በቀጣይ ትግል መክሰሙ አይቀሬ ነው፡፡ ለምን ቢባል ውሸት ፍጥነት ያላት፣ እውነት ግን ፅናት በመሆኗ ነው፡፡ ነገር ግን አሁንም ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ ችግሩን በአጭር ጊዜ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ የሚቻል አለመሆኑን ነው። እንደ አባባሉም መሬት ላይ የበቀለ አረም ሊታረም ይችላል፣ አእምሮ ላይ የበቀለ አረም ግን ዘመናትን ይጨርሳል ነውና ዘላቂ መፍትሄ የሚገኝለት ቀጣይነት ያለው የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት በመስራት ነው፡፡
ሃናን አርዳንት የተባሉት አሜሪካዊት የፖለቲካ ተመራማሪና ሃያሲ ትምክህት የሌሎችን ብሄሮች ማንነት በመካድ፣ የተጋነነ ዘረኝነትን መሠረት አድርጐ የአንድን ብሄር የበላይነት የሚሰብክ አደገኛና የዘቀጠ እምነት ነው ይላሉ፡፡ ጠባብነት ደግሞ የተዛቡ ታሪካዊ ግንኙነቶችን ብቻ ነቅሶ በማውጣት በዴሞክራሲያዊ አንድነት ውስጥ እንኳን ራስን ተጎጂ አድርጎ የማቅረብ አዝማሚያ ነው። የአንድ ሀገር ወይም ስርዓት ጠባቂ እራሱን ብቻ አድርጎ መውሰድና ሌሎችን በጥርጣሬ ማየትም ሌላው የጠባብነት መገለጫ ነው። የትምክህትና የጠባብነት አስተሳሰብ የመጨረሻ መዳረሻ የሚሆነው የድህነት አዙሪት ውስጥ መግባትና የእርስ በርስ መናቆር ሲሆን በጊዜያዊነትም ቢሆን በጣም ጥቂቶችን የሚጠቅም ብዙሃንን ግን የሚጎዳ አካሄድ ነው፡፡
የድህነት ዘበኛ የነበረው ፋሽስታዊው የደርግ መንግሥት ኋላቀር የትምክህት አስተሳሰብ አስፈፃሚ ነበር፡፡ የትምክህት አስተሳሰብ ጎልቶ በወጣበት ሁሉ ጠባብነት አለና ይሄው ስርዓት ለጠባብ ሃይሎች መፋፋት ምክንያት ሆኗል። ሁለቱ ሃይሎች በየፊናቸው በመጓተት ሃገራችንን የመበታተን ጫፍ አድርሰዋት እንደነበር ይታወቃል። ደርግ በልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች መሪነት እና በመላው የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መራር ትግልና ከባድ መስዋዕትነት ተገርስሷል፡፡ ነገር ግን ለዘመናት የዘለቀውና ደርግ ሲያራምደው የነበረው አስተሳሰቡ በአሁኑ ጊዜም የተለያዩ ህብረ ቀለሞች እየተቀባ፣ በኢህአዴግ የሚመራውን የህዳሴው ጉዞ ለማደናቀፍ ከመሞከር አልቦዘነም፡፡
እዚህ ላይ የኢትዮጵያ ህዝቦች ልብ ሊሉት የሚገባ አንድ መሠረታዊ ጉዳይ አለ፡፡ ይኸውም የኢትዮጵያ የህዳሴ ጉዞ የማይዋጥላቸው በሃገር ውስጥና በውጭ ያሉት አፍራሽ ኃይሎች አገራችን ባደገችና በተረጋጋች ቁጥር የእነሱ አስተሳሰብና ተግባር ከነሰንኮፉ ግብአተ መሬቱ የሚገባበት ሁኔታ እንደሚፋጠን ማወቃቸውን ነው፡፡ በመሆኑም ብሄርን ከብሄር ከማጋጨት ጀምሮ ከሰማይ በታች ያለውን ማንኛውንም ለእነሱ የሚጠቅም ያረጀ የማደናገሪያ አጀንዳ ከተቀበረበት ጉድጓድ አውጥተውና አቧራውን አራግፈው መርጨታቸው አይቀርም፡፡ እናም ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብና ተግባር የበላይነት እስከሚይዝ ድረስም የትምክህትና ጠባብነት አስተሳሰብና ተግባር እየተንፏቀቁም ቢሆን መቀጠላቸው አይቀርም፡፡ ስለሆነም ዘላቂ መፍትሄው የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚን በልማታዊ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ለመቀየር የተጀመረውን ዘርፈ ብዙ ስራ አጠናክሮ በማስቀጠል የህዳሴ ጉዟችንን ማፋጠን ብቻ ነው። ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የጋራ ክንዳቸውን አጣምረው የዜሮ ድምር ፖለቲካ አራማጅ ሃይሎችን ዛሬም እንደወትሮው ሊመክቷቸው ይገባል።
እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ 75 በላይ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ተቻችለውና ተፈቃቅረው የሚኖሩባት አገር ናት፡፡ ይህ ለዘመናት የኖረው የመቻቻል ባህልና እሴት ለሌሎች አገሮች ተምሳሌት እንደሆነ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ደግሞ ደጋግሞ አውስቶታል፡፡ አሁንም ሆነ ወደፊት ኢትዮጵያውያን አብሮ ለመኖር ያላቸው ዕድል አንድና አንድ ብቻ ነው፡፡ ይኸውም ባለፉት 25 ዓመታት ብዝሃነታቸው የአንድነታቸው መገለጫ መሆኑን በእምነት ጨብጠው የህልውናቸውና የአንድነታቸው ዋስትና የሆነውን ዴሞክራሲያዊ ፌዴራላዊ ሥርዓት እንደ ዓይናቸው ብሌን እየጠበቁ ወደፊት መራመድ ነው። ከአሁን በኋላም ወደፊት እንጂ ወደኋላ ይመለሳሉ የሚል ጥርጣሬ ባይኖረኝም አሁንም ብዙ የቤት ሥራ እንዳለባቸው በየጊዜው እዚህም እዛም እየተፈጠሩ ያሉ ግጭቶች ህያው ምስክር ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች 17 መራራ የትጥቅ ትግል ዓመታት በገጠርና በከተማ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ታጋዮች ውድ ህይወታቸውን የከፈሉት ትምክህትና ጠባብነት ዳግም እንዲያንሰራሩ ወይም ሌላ መልክ ይዘው ብቅ እንዲሉ አይደለም፡፡ ይልቁንም ዴሞክራሰያዊ ብሄርተኝነት አብቦ፣ በመፈቃቀድና በመቻቻል ላይ የተመሠረተ ዴሞክራሲያዊ አንድነት በፅኑ መሠረት ላይ አኑረው፣ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመገንባት እንጂ፡፡ እናም ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ የማይነጣጠሉ ቀዳሚ አጀንዳዎቻቸው ከሆኑ በርካታ አመታት ተቆጥረዋል፡፡ በኢህአዴግ የሚመራው የኢፌዴሪ መንግሥትም ይህንን ዓላማ ከግብ ለማድረስ በመረባረብ ላይ ይገኛል፡፡ በአንፃሩ የአፍራሽ ኃይሎች ዋነኛ አጀንዳ ብጥብጥ፣ ሁከት፣ በንፁሃን ህይወትና ንብረት ላይ እሳት መጫር መሆኑ በተግባራቸው እየተመሰከረ ነው።
በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ዜጎች የመሰላቸውን ሃሳብ በነፃነት ያስተላልፋሉ። የፖለቲካ ድርጅቶችም ዜጎችን በየአመለካከታቸውና መደባቸው ከፍለው ያደራጃሉ፣ ለማህበራዊ መሰረታቸው በጎ ለውጥ የሚያስገኙ ፖሊሲና ፕሮግራሞችን በመቅረፅና ጠቃሚ ያልሆነውን ደግሞ ለማስቀየር ይታገላሉ በሰላማዊና ህግ በሚፈቅድላቸው አግባብ ከህዝብ ድምፅ በሚገኝ ድምፅ ስልጣን ሲይዙም የቆሙለትን አላማ ለመተግበር ይንቀሳቀሳሉ በአገራችን ኢትዮጵያ የፈለቁ አንዳንድ የፖለቲካ ኃይሎችና የውጭ ተላላኪዎች ግን ከዚህ በተለየ መርህ አልባ የተቃውሞ ስልት በመከተልና ዘመን ያለፈበት የትምክህትና የጠባብነት አስተሳሰብ አጀንዳ በማውለብለብ ዜጎችን የድህነት አዙሪት ውስጥ ለመክተትና እርስ በርስ በርስ ለማናቆር ይተጋሉ፡፡

የኢፌዴሪ መንግሥት እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ዋነኛ ትኩረት አሁንም ቢሆን ድህነትን ተፋልመው 2017. መካከለኛ ገቢ ያላት አገር መፍጠር ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት 22 ከመቶ የሚሆን ህዝባችን ከድህነት ወለል በታች እንዲሁም ከህዝባችን 17 በመቶ የሚሆን ሥራ ያጣ ዜጋ ባለበት ሁኔታ ተኝቶ ማደር አይቻልም፡፡ ድህነት ከመዋጋት በላይም በፍፁም ሌላ ቀዳሚ አጀንዳ ሊኖርይችልም፡፡ ድህነትን በመዋጋት ሂደት እንቅፋት የሆኑትን እነዚህን የአመለካከት ሰንኮፎች መንቀልም ታዲያ የዚሁ ትግል አካል አንድ አካል ነው። በዚህ መስክ የሚገኘው ድልም የድህነት ዘበኛ የነበረውን የደርግ ስርዓት ከማስወገድ ያልተናነሰ ስኬት ነው የሚሆነው።

1 comment:

  1. የትምክት እና የጠባብነት አመለካከቶችን በየጊዜው ከህዝብ ጋር በመሆን መዋጋቱ እና ቀንደኛ የህዝባችንን ጠላት ድህነትን መታገል ዋናው አቅጣጫችን ቢኖንም ከዚሁ ጋር ባልተናነስ ግን የሰላም አስጠባቂ ሃይላችንን አመጽን የመመክት አቅም ማሳደግ ግን እኩል ትኩረት መስጠት ያለብን ስራ ይመስለኛል፤ እንደ ደርግ ህዝብ ላይ እንተኩስም፤ እየሞትንም የሀገራችንን ትንሳኤ እናረጋግርጣለን፤ ትክክለኛ አቅጣጫ ነው ግን ደግሞ መስዋእትነቱን የምንቀንስበት መንገድ ካለ ብንፈትሽ መልካም ይመስለኛል፤ የጸጥታ ሃይሉን የአካል ብቃት፤ ጥይትና ሌሎች ጥቃቶችን የሚከላከልበት የውስጥ አልባሳትና የሰውነት መከላክያዎች፤ ወዘተ...ሊታሰበበት የሚገባ ጉዳይ ይመስለኛል። ግባችን የጸጥታ ሃይሉ ላይ ጥቃት የሞከር እና የፈጸመ ሁሉ ሳይቀጣ እንዳይቀር ማድረግ እና ለህዝባችንም መሳርያ የሚያነሳ ሁሉ ለፍርድ እንደሚቀርብ ወይም እዚህ ባደጉ አገሮችን እንደምናየው በመሳርይ እንደሚጠፋ ማሳምንና ማሳየት ይስፈልጋል። በኦሮምያን በጎንደር የተፈጸመው የጸጥታ አስከባሪዎች ሞት ከልቤ አሳዝኖኛል፤ ዘለአለማዊ ክብር ለሰማእታቱ ይሁን።

    ReplyDelete