EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Tuesday 10 March 2015

ወጥተን ስለመግባታችን ሳይሆን ስለመልማታችን የምናስብባት ሀገር

ኢህአዴግ በተከተለው ትክክለኛ ፖሊሲና ቁርጠኛ አመራር በአገራችን አስተማማኝ ሰላም ሰፍኗል!
የተከበራችሁ የአገራችን ሕዝቦች
አገራችን ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ለረጅም ዓመታት  በጸረ ዴሞክራሲያዊ የጭቆናና የአፈና አገዛዝ ሲማቅቁባት የነበረች መሆኗ የሚታወቅ ጉዳይ ነው። ዜጎች መብታቸውንና ጥቅማቸውን በህጋዊና ሰላማዊ መንገድ ማስጠበቅ የሚችሉበት ዕድል ተነፍጓቸው የነበሩባት ሀገርም ነበረች፡፡ ዜጎች ፍላጎትና ጥቅሞቻቸውን በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚያስከብሩበት እድል ከማጣታቸውም ባሻገርው ለጥያቄወቻቸው ይሰጣቸው የነበረው ምላሽ ግድያና ስቃይ በመሆኑ የትጥቅ ትግልን ብቸኛ አማራጭ ለማድረግ ተገድደዋል።  በዚህም ምክንያት የተለያዩ ብሔረሰቦችን በመወከል የተደራጁ ሃይሎች በትጥቅ ትግል የሚፋለሙበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡
ያለፉት ስርዓቶች ሲከተሉት የነበረው ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር የህዝቦችን የልማትና ዴሞክራሲ ጥያቄ ለመመለስ የማያስችል ይልቁንም በተከተሉት የተሳሳተ አቅጣጫ ከአንዱ ጦርነት ወደ ሌላኛው በመግባት ህዝባችን በማያልቅ ጦርነት ውስጥ ሆኖ ሲማቅቅ የነበረ መሆኑ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ አገሪቱ በሰላም ወጥቶ መግባት ብርቅ የሆነባት፤ ወጣቶች እውቀት በሚገበዩበት አፍላ ዕድሜያቸው ለጦርነት የተዳረጉባት፤ ኢኮኖሚዋ በጦር ሰራዊት ግንባታ የደቀቀባት አገር ነበረች፡፡
ኢህአዴግ በህዝባችን ላይ ተጭኖ የነበረውን የደርግን ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አገዛዝ ከመላው የአገራችን ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር በመሆን ካስወገደ በኋላ የህዝቦችን እኩልነትና ዴሞክራሲያዊ አንድነት የሚያረጋግጥ፤ የሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ማነነትና እሴቶች የሚታወቁበትና የሚከበሩበት፤ በመቻቻልና በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ለመመስረት የሚያስችል ስርዓት እውን በማድረጉ ከጦርነትና ብተና ድነናል፡፡ 


የዘላቂ ሰላማችን መሰረትና ጠበቃ ህዝባችን ነው!
ውድ የአገራችን ሕዝቦች
ለአገራችን ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ዋነኛው ባለቤት ሕዝባችን እንደሆነ ጠንቅቀን እንረዳለን፡፡ ሕዝባችን ልክ በሌሎች የልማት ስራዎች እንደሚያደርገው ሁሉ ተደራጅቶ የአካባቢውን ሰላምና ፀጥታ የሚያስጠብቅበት ሁኔታ በመፍጠራችን ከተራ ወንጀል መከላከል እስከ ፀረ ሽብርተኝነት ትግል አብሮን የሚሰለፍና በባለቤትነት የሚንቀሳቀስ ሆኗል። ዛሬ ገጠሮቻችንና ከተሞቻችን አስተማማኝ የሰላም አየር የምንተነፍስባቸውና በዚህም ፈጣን ልማት የሚቀጣጠልባቸው የለውጥ ስፍራዎች ሆነዋል፡፡
የቀደሙት ስርዓቶች የራሳቸውን ድክመት ከማየትና ይህንኑ ለመፍታት ከመትጋት ይልቅ የሀገራችን የሰላም እጦት ምክንያቶች ጎረቤቶቻችን እንደሆኑ፣ የእነሱ ያለመረጋጋት ለእኛ መልካም እድል፤ ጥንካሬያቸው ደግሞ ለእኛ ውድቀት እንደሆነ አድርገው ሲሰብኩን ኖረዋል፡፡ ኢሕአዴግ ግን የጎረቤቶቻችን ሰላምና እድገት እኛንም እንደሚጠቅመን በማመን ጎረቤቶቻችን የየራሳቸው ብቻም ሳይሆን የእኛም ሰላምና ብልፅግና ደጋፊ የሚሆኑበት የተመቻቸ ሁኔታ እንዲፈጠር በቁርጠኝነት ታግሏል፣ ስኬታማ ውጤቶች በማስመዝገብ ላይም ይገኛል። 
ከጎረቤት ሀገራት ብሎም ከማናቸውም የውጭ ሀገራት ጋር የሚኖረን ግንኙነት የህዝባችንን ጥቅምማስጠበቅና የሀገራችንን ሉአላዊነትማክበር ላይ እንዲመሰረትና በጋራ ተጠቃሚነት መርህም የተቃኘ እንዲሆን በማድረግ ያለፉት ስርዓቶች ይከተሉት የነበረውን የጦርነት አቅጣጫ ሙሉ በሙሉ ቀይረናል፡፡ ከማንኛውም ሀገር ጋር የምናካሂደው ግንኙነት የየሀገራቱን መንግስታት ሉዓላዊነትና እኩልነት በማክበርና በሀገራቱ የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ባለመግባት ላይ የተመሰረተ ሆኗል። ይህም ተገደን ከገባንበት የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነትና በሶማሊያ የአሸባሪና አክራሪ ሃይሎች የጋረጡብንን አደጋ ለመቀልበስ ካደረግነው የመከላከል ውጊያ በስተቀር በታሪካችን ረጅም ሰላማዊ ዓመታትን ማሳለፍ አስችሎናል፡፡


የሠላም እጦት ምንጮችን ለይተን በመንቀሳቀሳችን ብሔራዊ ውርደታችን መንኮታኮት ጀምሯል!
የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች
የብሄራዊ ውርደታችን ምንጭ የሆኑትን ችግሮች መፍታት የሚቻለው በአገራችን ሰላምና መረጋጋት በመፍጠር፤ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን እውን በማድረግ፤ ዘላቂ ልማትና የህዝብ ተጠቃሚነትን በዘላቂነት በማረጋገጥ ብቻ እንደሆነ ኢህአዴግ ያምናል። እነዚህ መሰረታዊ ጉዳዮች ደግሞ በወሳኝ መልኩ ከውስጣችን የሚመነጩ እንጂ የውጭ ሃይሎች በላያችን ላይ የሚጭኗቸው ሰበቦች አይደሉም፡፡
የውጭው ሃይል ሉዓላዊነታችንን ለመድፈር የሚነሳሳው በውስጥ እስከተዳከምንና ለአደጋ ተጋላጭ ሆነን እስከተገኘን ድረስ ብቻ ነው። ባለፉት 23 አመታት ከጎረቤት ሃገሮች ጋር በእኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት መርህ ላይ በገነባነው ግንኙነትና ትብብር የተነሳ ያገኘነው ሰላም ያረጋገጠልን ሃቅ ቢኖርም ይህንኑ ነው። ለዚህ እውነታ ማሳያነት በአባይ ውሃ ተጠቃሚነት ላይ ያንፀባረቅነው አቋም ተጠቃሽ ነው፡፡
ለዘመናት የህዝባችንና የአካባቢያችን የጦርነት ምንጭ እንደሆነ ተደርጎ ሲሳል የነበረውን የአባይ ውሃን ጉዳይ የስጋት ምንጭ መሆኑ ቀርቶ የእድገታችን ምንጭ ለማድረግ እየተረባረብን እንገኛለን፡፡ እስካሁንም ባለው ሂደት በአባይ ውኃ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጉዳይ አንፀባራቂ ስኬቶችን በማስመዝገብ ላይ ነን፡፡ አባይ የተፋሰሱን ሀገራት ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ባረጋገጠ መልኩ ለጋራ ልማትና ብልፅግና መዋል እንዳለበት አዲስ ሃሳብ በማመንጨትም ሆነ ለተግባራዊነቱ ግንባር ቀደም ተዋናይ በመሆን የሀገራችንን ጥቅም ጠብቀን በመጓዝ ላይ እንገኛለን።
የተከበራችሁ የአገራችን ሕዝቦች፤
በሀገራችን ሰላምን ማስፈን መቻላችን በርካታ ጠቀሜታዎችን እንድንጎናፀፍ አስችሎናል፡፡ ከማያባራ ጦርነትና እልቂት ተላቀን መላ ርብርባችንን ዋነኛ ጠላታችን ወደ ሆነው ድህነት እንድናዞር አስችሎናል። ውስጣዊ አንድነታችን ተጠብቆ ውጫዊ አደጋ ተጋላጭነታችን እንዲቀንስ አድርጓል፡፡ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ የነበረንን የረጅም ጊዜ አሉታዊ ገጽታ በበጎ መልኩ እንዲቀየር ጉልህ ሚናም አበርክቷል፡፡ አገራችን ከራሷ ተርፋ በዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ ባላት ገንቢ ሚና አራተኛ ደረጃን ይዛለች፡፡ ይህም በኢህአዴግ መሪነትና መላ አገራችን ህዝቦች ባደረጉት ርብርብ የተገኘ አኩሪ ስኬት ነው፡፡
የአገር መከላከያ ሰራዊታችን የአፍሪካን ሰላም ለማስከበር አስፈላጊ ሆኖ በተገኘበት ቦታ ሁሉ በመሰማራት ከፍተኛ ውጤት አስመዝግቧል፡፡ ከሩዋንዳ ጀምረን እስከ ላይቤሪያና ብሩንዲ ከዚያም እስከ ሁለቱ ሱዳኖች የመከላከያ ሰራዊታችን በተጓዘበት ሁሉ ብቁ የሰላም አስከባሪ ሃይል መሆኑንና ህዝባዊነቱም በተግባር እያስመሰከረ ይገኛል፡፡ በዓለም የዲፕሎማሲ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ አገራችን በጦርነት ለሚፋለሙ ጎረቤት ሃገሮች የጋራ አሸማጋይና የፀጥታ አስከባሪ ሆና እንድታገለግል የተመረጠችው ለዓለም ህዝቦች ፍትሃዊ ዳኝነት የመስጠት ታማኝነቷ በመጎልበቱ ነው፡፡ 
አገራችን በጎረቤት አገሮች በሱዳንና በደቡብ ሱዳን መንግስታት የተፈረመው ሁሉን አቀፍ የሰላም ስምምነት ማእቀፍ በተሳካ ሁኔታ እንዲፈፀም በሁለቱ ሀገራት አዋሳኞች ላይም የሰላም አስከባሪ ሰራዊቷን በማስፈር ለአካባቢው ሰላምና መረጋጋት ያላትን ቁርጠኝነት በተግባር አረጋግጣለች፡፡  
ከሁለት አስርት  ዓመታት በላይ መንግስት አልባ በመሆን ዜጎቿ የሰላምና መረጋጋት ወጋገኑ ጠፍቶባቸው በእርስ በርስ ጦርነት ሲታመሱ የነበሩት ሶማሊያውያን የተረጋጋች ሀገር መገንባት የሚያስችላቸውን የተመቻቸ ሁኔታ በመፍጠር ረገድ የሀገራችን ድጋፍ ከፍ ያለ ነበር፣ ነውም። በተለይም ለሀገራችን እና ለአካባቢው ሀገሮች ጭምር ስጋት ሆኖ የነበረውን ራሱን የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ህብረት ብሎ የሚጠራውንና በኋላም በአገራችን ላይ ጅሃድ በማወጁ ምክንያት በመከላከያ ሰራዊታችን በደረሰበት ጠንካራ ምት ተበታትኖ የቆየውን የአልሸባብ ሽብርተኛ ቡድን በመታገል በምትኩ የተረጋጋ ማዕከላዊ መንግስት እንዲመሰረት በመደገፍ ሀገራችን በትጋት ሰርታለች። በሀገር መከላከልና ደህንነት ጉዳዮች ያለን ትስስር ከጎረቤት ሀገሮች ጋር ብቻ ሳይወሰን በዓለም አቀፍ ደረጃም ሽብርተኝነትን እና ሌሎች አለም አቀፍ ወንጀሎችን በመከላከል ረገድ በጋራ የምንሰራበትን ሁኔታ ፈጥረናል፡፡
በአጠቃላይ ሀገራችን ሁከትና ብጥብጥ በማይለየው የአፍሪካ ቀንድ ውስጥ የራሷን አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት በማረጋገጥ የቀጠናው የሰላም ተምሳሌት ለመሆን ችላለች። በዚህም ሀገራችን ቀድሞ ትታወቅበት የነበረው ጦርነትና ያለመረጋጋት አሁን ሙሉ በሙሉ መቀየር ብቻ ሳይሆን ለዓለም ሰላም ዘብ በመቆም ዕውቅና አትርፋለች፡፡
በፀረ-ሽብርተኝነት ላይ እያካሄድን ያለው ትግል ለዘላቂ ሠላማችንና ልማታችን ዋስትና ነው!
የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች
ኢህአዴግ በፀረ ሽብር ትግሉ በቁርጠኝነት የሚንቀሳቀሰው ለዜጎቻችን በሰላም ውሎ በሰላም መግባት ካለን ፅኑ ፍላጎትና ሃላፊነትም ነው፡፡ በዚህም ሀገራችን ጠላቶቿ እንደሚመኙላት የሽብር ምድር ሳትሆን የሰላም አየር የምንተነፍስባት፤ ወጥተን ስለመግባታችን ሳይሆን በየቀኑ ስለመለወጣችን የምንጨነቅባት ሀገር ሆናለች፡፡ በአንፃሩ እንደ ኢትዮጵያ ተገቢውን የመከላከል ስራ ያልሰሩ ያደጉ ሀገራት ጭምር አሁን የአደጋው ግንባር ቀደም ሰለባ ሲሆኑ ቀድመው ያልሰሩትን የቤት ስራ ተመልሰው ወደ መከወን ገብተዋል።
ኢሕአዴግ የአገራችንን ዘላቂ ሠላምና መረጋጋት ለማስፈን የፈጠረው ሠላማዊና በመርህ ላይ የተመሰረተ አካባቢያዊ ሁኔታና ግንኙነት ለተቃዋሚዎች በተለይ ደግሞ ለፅንፈኛ ሃይሎች አይዋጥላቸውም፡፡ ተቃዋሚዎች ያለፉትን ስርዓት ያረጁ አስተሳሰቦች ተሸክመው አሁንም ከጎረቤቶቻችን ጋር ያለን ግንኙነት የሻከረና በጥርጣሬ ላይ የተሞላ እንዲሆን ስለሚፈልጉ የተለያዩ የበሬ ወለደ አሉባልታዎችን በማንሳት ስኬታማውን የሰላም ማስከበር እንቅስቃሴያችንን ለማጠልሸት ይራወጣሉ፡፡ በአንድ በኩል ኢህአዴግ የራሱን የውስጥ ችግር ሳይፈታ ጎረቤት አገራት ለሰላም ማስከበር ተልዕኮ መውሰዱ ለፖለቲካ ፍጆታ ነው ሲሉን ይከርሙና በሌላ በኩል ደግሞ በሃገር ውስጥ የህዝባችንን ደህንነት ለማስጠበቅ የምንወስዳቸውን የመከላከል እርምጃዎች ኢትዮጵያ ከሽብር ተግባር ነፃ የሆነች ሰላማዊ ሀገር ነች፤ ስለሆነም የፀረ ሽብር ህግ አያስፈልጋትም በማለት ያደናግራሉ፡፡
ሀገራችን የሽብር ስጋት ብቻ ሳይሆን በተግባርም የተፈፀመባትና የለበለቧት፤ ብዙ ዜጎችን ለማጥፋት የተቃጡ የሽብር ተግባሮች የከሸፉባት መሆኗንና እነዚህም የሽብር ተግባሮች መነሻቸው በጎረቤት ሀገራትና በውስጣችን ባደፈጡ ሽብርተኞችና የሽብር ተላላኪዎች መሆኑ ሃቅ ነው፡፡ እናም ኢሕአዴግ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሽብርተኞች ላይ የተከፈተው ዘመቻ አንድ አካል ሆኖ የራሱን ሚና በከፍተኛ ቁርጠኝነትና የኃላፊነት መንፈስ በአግባቡ ሲወጣ ዋናው አላማ የህዝባችንን ሰላምና ደህንነት በመጠበቅ ለልማትና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታችን ምቹ ሁኔታ መፍጠር መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ዳግም ልናስገነዝባቸው እንሻለን፡፡
ውድ የአገራችን ሕዝቦች፤
የልማትም ሆነ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታችን ተጠናክሮ የሚቀጥለው በሀገራችን የሰፈነው ሰላም መቀጠል ሲችል ብቻ ነው፡፡ ኢሕአዴግን መምረጥ ደግሞ የተጀመረውን ልማት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ አጠናክሮ ማስቀጠል ብቻ ሳይሆን አዳዲስ የልማት፤ የሰላም፣ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ፕሮጀክቶችን ቀይሶ የሀገራችን የህዳሴ ጉዞ አጠናክሮ ማስቀጠል ማለት ነው። ኢሕአዴግን መምረጥ የራስዎን፤ የቤተሰብዎንና የሀገርዎን ሰላምና ደህንነት ሳይዘናጋ የሚያስከብርልዎን ድርጅት መምረጥ ማለት ነው፡፡
ኢሕአዴግ የአደጋ ተጋላጭነታችን ምንጮችን በመለየትና ምንጮቹን በማድረቅ ውጤታማ የውጭ አደጋ ተጋላጭነት የመከላከል አቅም ለመፍጠር እየተጋ ያለ ድርጅት ነው፡፡ ኢሕአዴግ በአምስተኛው ዙር ሀገራዊ ምርጫ ድምፃችሁን እንድትሰጡት የሚጠይቃችሁ ዛሬም እንደ ትናንቱ ከእናንተ ጋር በመሆን የሀገራችንን ዘላቂ ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ያለውን ቁርጠኝነት በከፍተኛ ሁኔታ በማረጋገጥ ነው፡፡
ለፈጣን ልማት፣ ዘላቂ ሰላም እና ዴሞክራሲ-ኢህአዴግን ይምረጡ!!

No comments:

Post a Comment