EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Wednesday 19 November 2014

የፀና የትግል ታሪክ ለዛሬው ትውልድ


በአሜሳይ ከነዓን

ህዝባዊ ትግል ግልፅ ዓላማና ግብ አለው፡፡ አገራችንም ህዝባዊ ትግል መራራ ቢሆንም በድል እንደሚጠናቀቅ ማሳያ ሊሆኑ የሚችሉ የበርካታ እውነተኛ ትግል ታሪክ ባለቤት ነች፡፡ ትክክለኛውን የህዝብ ጥያቄ አዳምጦ ጠመዝማዛውንና የማይቻል የሚመስለውን የትግል ውጣ ውረድ በፈታኝ ሁኔታ በማካሄድ ትግል ከህዝብ ጋር ድል እንደሆነ በተግባር ማሳየት የቻለ የሰመረ የተጋድሎ ታሪክ ባለቤት ኢህዴን አንዱ ምልክት ነው፡፡ ህዳርን በርካቶቻችን ከራሳችን ህይወት ጋር እያቆራኘን በተለያየ መንገድ እናስባት ይሆናል፡፡ ለመላው የኢትዮጵያ ጭቁን ህዝቦችና ለኢህዴን ታጋዮች ደግሞ ህዳር 11 ቀን 1973ዓ.ም ልዩ የመታሰቢያ ቀን ናት፡፡

የፋሽስታዊ ደርግ በንፁሃን ወገኖቻችን ዘንድ ሽብርና የጅምላ ጭፍጨፋ ማካሄዱ ያንገፈገፋቸው ጥቂት ቆራጦች እንቢ ለጭቆና በማለት ህዝባዊ ወኔ በመሰነቅ የነፃነት ጎህ ምልክት የሆነውን የያኔው ኢህዴን የአሁኑ ብአዴን የመሰረቱበት ቀን ነው ህዳር 11፡፡ የፅሁፌ ዓላማ የኢህዴንን የረጅም ዓመታት የትግል ታሪክ ለመዘከር ባይሆንም ላስቃኛችሁ ካሰብኩት ጭብጥ ጋር ቁርኝት አለውና እንደው በግርድፉ ላስታውሳችሁ ከሚል ነው፡፡ ህዳር 5 እና 6 በአዲስ አበባ የፌደራል ዞን አደረጃጀት የብአዴን አባላት ኮንፈረንስ ተካሂዶ ነበር፡፡ የብአዴን/ኢህአዴግ 34ኛ ዓመት የምስረታ በዓልም በዕለቱ ተከብሯል፡፡

ኮንፈረንሱን በወፍ በረር እንዲህ ቃኝቼዋለሁና አብረን እንራመድ ብያለሁ፡፡ በፌደራል ትራንስፖርት አዳራሽ የተካሄደው የፌደራል ዞን የብአዴን አባላት ኮንፈረንስ ገና ከማለዳው ነበር የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች ወደ አዳራሹ መግባት የጀመሩት፡፡  በኮንፈረንሱ ለመሳተፍ ከቦታው የተገኙት አባላቱ በአዳራሹ ጢም ብለው ሞልተዋል፡፡ እኔም ውይይቱ ከመጀመሩ በፊት ማስተዋሻዬንና ብዕሬን አዘጋጅቼ ውይይቱን መከታተል ጀመርኩኝ፡፡ አቶ ከበደ ጫኔ የንግድ ምኒስትር እና የብአዴን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እና አቶ ጌታቸው አምባዬ የፍትህ ምኒስትር እና የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል በጋራ በመሆን ኮንፈረንሱን ለመምራት ከመድረክ ተሰይመዋል፡፡

“አንፀባራቂ ድሎቻችንን የሚፈታተኑ ድክመቶቻችንን በማረም ለመድረኩ ተልዕኳችን እንብቃ” በሚል መሪ ቃል የታጀበው የመወያያ ሰነድ በአቶ ጌታቸው አምባዬ አማካኝነት ለኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች መቅረብ ጀመረ፡፡ ባለፉት 23 ዓመታት የአገራችንን እድገት ከአማራ ክልል እድገት ጋር በማቆራኘት የተመዘገቡ አንፀባራቂ ድሎች ፍንትው ብለው ለተሳታፊዎቹ ቀረቡ፡፡

በተለይ ኢህአዴግ ከተሃድሶ በኋላ በመስመራችን ልማታዊና ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ኢኮኖሚ የበላይነት በማረጋገጥ ኪራይ ሰብሳቢነትን በሂደት ለመድፈቅ የሚያስችለውን ርብርብ ማድረግ እንደሚገባው ግልፅ ያለ አቅጣጫ በማስቀመጥ የመጣበትን የ13 ዓመታት የተሃድሶ ጉዞ በኮንፈረንሱ ተብራርቷል፡፡ በእርግጥም የተሃድሶ ዘመን በአገራችንም ይሁን በክልሉ የተመዘገቡ ድሎች ብቻ ሃገራችን እየመጣችበት ላለው የተሳካ ጉዞና የአንፀባራቂ ድሎቿ ምስጢር የተሃድሶ መስመሩ እና አመራሩ እንደሆነ ይበልጥ ግልፅ ሆነ፡፡

አቶ ጌታቸው አምባዬ ኢህአዴግ ድህነትና ኋላ ቀርነትን ለማስወገድ እልህ አስጨራሽ የትግል ሂደቶችን በማለፍ ዛሬ ላይ አገራችን ባለፉት 11 ተከታታይ ዓመታት ባለሁለት አሃዝ እድገት ማስመዝገብ የቻለች ሃገር መፍጠር ችሏል ብለዋል፡፡ አያይዘውም ብአዴን/ኢህአዴግም ከድህነትና ከኋላ ቀርነት ጋር በሚያደርገው ትንቅንቅ ዛሬ ላይ በአርሶ አደሩና በከተማው ህዝብ ላይ ተጨባጭ ስኬቶችን ማስመዝገብ ችሏል በማለት አብራርተዋል፡፡


አቶ ጌታቸው በገለፃቸው ላይ እንዳስታወሱት የተሃድሶ መስመራችንን በነደፍን በዓመቱ ባጋጠመ ድርቅ በአገራችንም ይሁን በክልሉ የርሃብ አደጋ አንዣቦ የነበረ ሲሆን አገራዊ ምርታችን ከማሽቆልቆሉ ባሻገር ከ14 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ እህል እስከመመፅወት ተደርሶ ነበር፡፡ ላለፉት 11ዓመታት በተካሄደው ርብርብ ይህ ክስተት ታሪክ መሆን ችሏል፡፡ በ2005/2006 የምርት ዘመን በሰብል ምርት ብቻ 254 ሚሊዮን ኩንታል እህል ማምረት ተችሏል፡፡ ከዚህ ውስጥ የአማራ ክልል ድርሻ ደግም 81 ሚሊዮን ኩንታል መሆን ችሏል ብለዋል፡፡

በአርሶ አደራችን ከመጣው ለውጥ ባልተናነሰ መልኩ በከተሞችም በርካታ አበረታች ተግባራት ተፈፅመዋል፡፡ በከተሞች ፈተና የነበረው የስራ አጥነት ችግር ዛሬ ላይ ወጣቶቹ የመንግስትን ድጋፍ እንደ እርሾ በመጠቀም በራሳቸው መንገድ ስራ ፈጥረውና በተፈጠረው የስራ እድል ተሰማርተው ጥሪት ማፍራት ጀምረዋል፡፡ ዛሬ በክልሉ ከተሞች በወሳኝነት ያለው ጥያቄ ከስራ እድል ጥያቄ ባሻገር ምርታማነትን በቀጣይነት ስለማሻሻል እየሆነ መጥቷል፡፡ በማህበራዊ ዘርፍም በክልሉ አመርቂ ውጤቶች በመመዝገብ ላይ ናቸው፡፡ እንደአገር የትምህርት መስክ ያለፉት አፈፃፀሞችን ብንመለከት በ1983ዓ.ም ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን የማይበልጡ ተማሪዎችን የተረከበው ኢህአዴግ ዛሬ ከ23 ዓመታት በኋላ   ከ22 ሚሊዮን የማያንሱ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡ በአማራ ክልልም በትምህርት መስክ የተገኘው ውጤት አንፀባራቂ ነው ፡፡ በ1983ዓ.ም ከ300 ሺህ የማይበልጡ ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ የነበሩ ሲሆን ዛሬ ከ23 ዓመታት በኋላ 4 ነጥብ 2ሚሊዮን ህፃናትና ታዳጊዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ እናገኛቸዋለን፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በአገርም ሆነ በክልሉ የሁለተኛ ደረጃም ይሁን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማስፋፋት ላይ የመጡ ስኬቶች የሚታዩና የሚጨበጡ ናቸው፡፡

እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ስኬቶች ታዲያ በድርጅታችን የመሪነት ድርሻ በህዝብ የነቃ ተሳትፎና ትግል የተመዘገቡ ውጤቶች ናቸው ሲሉ አቶ ጌታቸው በንግግራቸው ጠቁመዋል፡፡ በእርግጥም በተወሳሰበና ትግል በሚጠይቅ መድረክ ላይ የተመዘገቡ ድሎች አልኩኝ እኔም ለራሴ፡፡

አቶ ጌታቸው ሌላው በማብራሪያቸው ትኩረት የሰጡት አጀንዳ ኪራይ ሰብሳቢነት በተመለከተ ነበር፡፡ እንደእሳቸው አገላለፅ የተጠቀሱት የፖለቲካ ኢኮኖሚ ለውጦችና ለዚህም ያበቃን የድርጅታችን አመራር መሰረታዊ መገለጫዎች እንደተጠበቁ ሆነው ዛሬም ለኪራይ ሰብሳቢነት የተመቸው ፖለቲካ ኢኮኖሚ ከፍተኛ ፈተና መሆኑ ነው፡፡

በዚህ ሂደት ውስጥ የሚታዩ ፀረ ልማትና ፀረ ዲሞክራሲ አስተሳሰቦችና ተግባራት በፖለቲካ ኢኮኖሚ ውስጥ አሉታዊ ተፅእኖ ማሳደራቸው አልቀረም፡፡ የምርታማነት ደረጃን በበቂ ሁኔታ ማሳደግ፣ የመሰረተ ልማት አውታሮችን በሚፈለገውን መንገድ በማቅረብ፣ ለኢንዱስትሪ ሽግግሩ መሳለጥ አይነተኛ ሚና ያለው የማኑፋክቸሪግ ዘርፍን በተሳካ ሁኔታ ማስፋፋት አሁንም ትኩረት የሚሹ አበይት  አቅጣጫዎች ናቸው፡፡ በገጠርም ሆነ በከተማ ለልማትና ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እንቅፋት የሆኑ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን አርኪ በሆነና ከኪራይ ሰብሳቢነት በፀዳ አስተሳሰብ መፍታት ላይ ያሉ ክፍተቶች ለሚፈለገው የህዳሴ ጉዞ እንቅፋት መሆናቸው አልቀረም፡፡ ዕንቅፋት ባለበት ደግሞ ፍጥነት ብሎ ነገር እጅግ አስቸጋሪ ይሆናል።

የውስጠ ድርጅት ጥንካሬን በተመለከተም አቶ ጌታቸው ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡ አባላት በተለይ የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካዊ መገለጫዎቹን በብቃት እና በንቃት ከመታገል አንፃር ሰፊ ክፍተት እንዳለ ገልፀዋል። ድርጅታችን ኢህአዴግ የስርዓቱ ዋነኛ ፈተና ኪራይ ሰብሳቢነት እነደሆነ በግልፅ አስቀምጦ አስተሳሰቡንም ተግባሩም በፅናት እየታገለ ይገኛልም ብለዋል፡፡  ኪራይ ሰብሳቢነት መገለጫዎቹ በርካታ እንደመሆናቸው መጠን አባላት ትግላቸውን ያዝ ለቀቅ እያደረጉ ሳይሆን ጥራት ባለው መንገድ መታገል እንደሚገባቸውም አስታውሰዋል፡፡ በተለይ ትምክህት፣ ጠባብነትና አክራሪነት የስርዓቱ ዋነኛ አደጋዎች በመሆናቸው አባላት በቁርጠኝነት አምርረው መታገል  ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

አቶ ጌታቸው ብአዴን በተለይ ለአዲሱ ትውልድ የጥንካሬ ተምሳሌት የሚሆን የወርቃማው የትግል ታሪክ ባለቤት ድርጅት በመሆኑ አባላቱ የድርጅቱን የተግል ታሪክ በመላበስ እና ከአድርባይነት፣ ከትምክህትና ከጠባብነት በፀዳ መልኩ ፀረ ድህነት ትግሉን በተሟላ የትግል ቁመና ሊመሩት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ብአዴን ዛሬም እንደትናንቱ ለክልሉም ሆነ ለአገራችንና ለህዝባችን ዕድገትና ብልፅግና አስፈላጊውን ሁሉ መስዋዕትነት ለመክፈል እንደትናንቱ ዝግጁ በመሆኑ መላው አባላቱ  በዚህ የትግል ስሜት ከድህነት ጋር መታገል እንዳለበት አስመርውበታል፡፡

በኮንፈረንሱ ተሳታፊ የነበሩት አባላት በርካታ ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡ በተለይ ኪራይ ሰብሳቢነትን በመታገል ሂደት ውስጥ አባላቱ እየገጠማቸው ስለለ ችግር ሲያነሱ ተስተውለዋል፡፡ የመሰረተ ልማት አውታሮችንና የመልካም አስተዳደር ችግርን በተመለከተም በውይይቱ በስፋት የተነሱ ሲሆን የውስጠ ድርጅት ጥንካሬን በማጎልበት በኩል ከእያንዳንዱ አባል ስለሚጠበቀው ድርሻም ከኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች አስተያየቶችና ጥያቄዎች ቀርበዋል፡፡

በጥያቄዎቹና አስተያየቶቹ ላይ አቶ ከበደ እና አቶ ጌታቸው ምላሽ እና ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን በተለይ የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚን በመናድና በምትኩም ልማታዊ ፖለቲካል ኢኮኖሚን የበላይነት በማረጋገጥ በኩል ስለሚኖረው ቀጣይ ትግል በተመለከተ አመራሮቹ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

አቶ ከበደ በተለይ አባላቱ ከመተጋገል ጋር በተያያዘ ላነሱት ጥያቄ ሲያብራሩ ከብአዴን/ኢህአዴግ የትግል ታሪክ የምንረዳው መሰረታዊ ቁምነገር ትግል ጠመዝማዛና ፈተና የበዛበት ግን ደግሞ በፅናት ከታገሉ አይቀሬ ድሉ  የህዝብ መሆኑን በማስረዳት ለመታገል ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጥ አያስፈልግም፣ ይህ የድርጅታችን መለያም መገለጫም አይደለም በማለት አስረድተዋል፡፡ አባለቱ በመስመራቸው ፀንተው ያለአንዳች መወለጋገድ መታገል ከቻሉ በእርግጥም የወርቃማው ድርጅት የብአዴን አባላት መሆናቸውን በተግባር አረጋግጠዋል ማለት ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡ እንደእሳቸው ገለፃ የውስጠ ድርጅት ጥንካሬ የሚመነጨው ከራሳቸው ከአባላቱ በመሆኑ አባላት አዳዲስ አባላትን የሚመለምሉበት ግንባታ የሚሰጡበትን በተግባርም ተልዕኮ እየሰጡ የሚያበቁበት በተሟላ ተቋማዊ አሰራር ውስጥ መግባት አለባቸው ካሉ በኋላ በተግባር ተፈትኖ ውጤታማ አባል ደግሞ ኪራይ ሰብሳቢነትንም ይሁን ሌሎች ፀረ ልማት አስተሳሰቦችና ተግባራት መመከት የሚችል የተሟላ ፖለቲካዊ ቁመና ይኖረዋል ሲሉ በዝርዝር አስረድተዋል፡፡

አቶ ጌታቸው በበኩላቸው አሁንም ለኪራይ ሰብሳቢነት የተመቸውን የፖለቲካል ኢኮኖሚ በድርጅታችን የጠራ መስመር ተደራጅተን እስካላስወገድነው ድረስ ችግሮች መኖራቸው አይቀርም፣ የርብርብ ማዕከሉ በተለይ በከተሞች የልማታዊ ዲሞክራሲያዊ ፖለቲካል ኢኮኖሚ የበላይነትን ማረጋገጥ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ እያንዳንዱ አባል በቁርጠኝነት መታገል ይኖርበታል ብለዋል፡፡

በኮንፈረንስ ተሳታፊዎች በኩልም አሁንም እንደ ብአዴን እየተገናኙ ተግባራትን በመገምገምና አባላትን በማብቃት ለመድረኩ ተልእኮ የሚመጥን ተተኪ ትውልድ የማፍራት ትግሉ በአመራሩም በአባላቱም በኩል የየድርሻቸውን በመውሰድ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉ የጋራ አቋም ወስደዋል፡፡

በመጨረሻም የብአዴን 34 ዓመት የምስርታ በዓል በትግል የተሰው ሰማዕታትን በማሰብና የሻማ ማብራት ፕሮግራም በማከናወን የተካሄደ ሲሆን የኮንፈረንሱ አባላትም ባለ10 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ኮንፈረንሱ ተጠናቋል፡፡ አባላቱ በአቋም መግለጫቸው በብአዴን/ኢህአዴግ እየተመዘገቡ ያሉ አንፀባራቂ ድሎችን በማስቀጠልና የአገራችን ዋነኛ ጠላት የሆኑትን ድህነትና ኋላቀርነትን ድል በመንሳት የአገራችንን ህዳሴ እናረጋግጣለን በማለት ብአዴን/ኢህአዴግ ያስተማራቸውን በመተጋገል ውስጥ ያለ አንድነት ጠብቆ በማቆየት ለድርጅታቸው መስመር የሚከፈለውን ዋጋ ለመክፍል ያላቸውን ዝግጁነት አረጋግጠዋል፡፡

No comments:

Post a Comment