EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Saturday, 21 January 2017

ፐብሊክ ሰርቪሱ የህዳሴ ጉዟችን መሰረት
                  (በኤፊ ሰውነት)

ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች ውይይቶች በመካሄድ ላይ ናቸው፡፡ እንደአገር በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተነሱ የተሳትፎና የተጠቃሚነት እንዲሁም መሰል የመብት ጥያቄዎችን በተገቢውና አፋጣኝ በሆነ መንገድ ከመመለስ አኳያ ባለፉት ዓመታት ችግሮች መስተዋላቸውን ለይቶ ኢህአዴግ የሚመራው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት ይህንን መፍታት በሚቻልበትና በቀጣይ የህዳሴ ጉዞአችንን ለማሰላጥ የሚያግዘን የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቀሴ ውስጥ ይገኛል፡፡ በዚህም ኢህአዴግና ህዝቡ በጋራ ችግሮችን የመለየትና በቀጣይም መፍትሄ በማስቀመጥ ወደፊት መራመድ የሚችሉበትን ምክክር በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ ባለፉት ዓመታት በነበሩ ስኬቶችና ተግዳሮቶች ውስጥ መላው የአገራችን ህዝብ ጨምሮ የመንግስት አስፈፃሚ አካላት ሚና ከፍተኛ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ውድ አንባብያን ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ የመንግስት ሰራተኛው፣ መላው ህዝብና፣ ወጣቶች ከመንግስት ጋር የሚያደርጉት የጋር ውይይት ተጀምሯል፡፡ እነዚህ አካላት ባለፉት ዓመታት እንደአገር በነበሩ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ኃላፊነት የነበራቸውና የድርሻቸውን የተወጡ በመሆናቸው ያለፉ ስኬቶቻቸውንና የቀጣይ አቅጣጫዎችን በጋራ መምከራቸው ተገቢና ወቅታዊ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡

የዚህ ጽሑፍ ዓላማም በተለይ የመንግስት ሰራተኛው ወይም  ፐብሊክ ሰርቫንቱ ባለፉት ዓመታት እንደአገር በተመዘገቡ ስኬቶችና በገጠሙ ተግዳሮቶች ላይ የነበረውን ሚና ቀንጭቦ ማሳየት ይሆናል፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው ለአንደ አገር ከሁሉም ነገር በላይ የሚቀድመው አገሪቱ የምትመራበትን ህግና የህግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ባለፉት 25 ዓመታት ከህገመንግስቱ ጀምሮ የተለያዩ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች፣ መመሪያዎች፣ አዋጆችና ደንቦች ተቀርጸዋል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት እየተሻሻሉና እየዳበሩ የሚሄዱ ደንብና መመሪያዎች እንደተጠበቀ ሆኖ አገሪቷ ልትመራበት የምትችለውን መስመር ከመንደፍ አኳያ ኢህአዴግ ህዝብ የማስተዳደር ስልጣን ከተረከበ ጊዜ ጀምሮ ይበል የሚያሰኝ ስራ ተሰርቷል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ከሰነድ ባለፈ ይህንን ስልት ሊያስፈፅም የሚችል መዋቅር በመዘርጋትና ያንን መፈፀም የሚችሉ ባለሙያዎችን ከመመደብ አኳያም አበረታች ተግባር ተፈጽሟል፡፡ ከዚህ አኳያ ባለፉት ዓመታት የአገራችንን መጻኢ እድል የሚወስኑ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን መሬት ከማውረድና ለህዝብ ከማድረስ አኳያ ሲቪል ሰርቪሱ የነበረው ሚና የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል፡፡

በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስክ የተቀመጡ ራዕዮችን ለማሳከት መዋቅር ከመዘርጋት ባለፈ ያንን የሚያስፈፅም አካል መኖሩ ግድ ነው፡፡ አንገት ያለ ራስ፤ ራስም ያለ አንገት የማይታሰብ ነውና፡፡ በመሆኑም የህዝብ ኃላፊነት ከተሸከመው ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጀምሮ እሰከታችኛው መዋቅር ድረስ ያለው  ፐብሊክ ሰርቪስ የመንግስትን አገልግሎት ለህዝብ ከማድረስ አኳያ ብቸኛውና አይነተኛ መሳሪያ መሆኑን መገመት አያዳግትም ፡፡

በተደጋጋሚ ለማመላከት እንደተሞከረው በአገራችን ባለፉት 25 ዓመታት በተከናወኑ አበረታች ተግባራት አገራችን ተከታታይና ፈጣን የሆነ ልማት ማስመዝገብ ከመቻሏ ባሻገር ተስፋ የሚጣልባት ባለራዕይ አገር ለመሆን በቅታለች፡፡ ዴሞክራሲ እንዲያብብ፣ የዜጎች እኩል ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲጎለብት፣ ዜጎች በአገራቸው ሰርተውና ሃብት አፍርተው የሚለወጡባት አገር እንድትሆን ከማድረግ አኳያ እንዲሁም በተለይ መንግስት በአገራችን የመሰረት ልማት ለማስፋፋት፣ የማህበራዊ ልማትን ለማፋጠን በሚነድፈው ስትራቴጂና እሱን ለማስፈፀም በሚያደርገው እንቅስቃሴ ውስጥ የመንግስትን ፕሮግራም በማስፈፀም በኩል  የመንግስት ሰራተኛው ሚና ከፍተኛ ነበር፡፡ መላው የአገራችን ህዝብ ደግሞ ከመንግስት አስፈፃሚዎች ጋር እጅና ጓንት ሆኖ በመደገፍና በጋራ ለመንቀሳቀስ በተጨባጭ ያሳየው ቁርጠኝነት በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡

የመንግስትን አገልግሎት ለህዝቡ ተደራሽ ለማድረግ በሚከናወን ተግባር ሁሉ የመንግስት ሰራተኛው ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ህዝቡን ሲያገለግል መቆየቱ አይዘነጋም፡፡ በከተማም ሆነ በገጠር ቤት ለቤት ከማስተማር ጀምሮ በተለያዩ መድረኮች በመወያየትና ግንዛቤ በማስጨበጥ ህዝቡ በሚከናወኑ የልማት ስራዎችና መሰል ተግባራት ቀጥተኛ ተሳታፊ እንዲሆን ከማስቻል አኳያ የመንግስት ሰራተኛው በቁርጠኝነት ሰርቷል፡፡ በገጠር አኗኗሩም ከከተማ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ፈፅሞ የተለየ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አሁን አገራችን ለደረሰችበት የለውጥ ደረጃ መሰረት የሚሆን ተግባር በመንግስት ሰራተኛው ተፈፅሟል፡፡ ስለግብርና ምርትና ምርታማነት፣ ስለተፈጥሮ ሃብትና መስኖ ልማት ስራችንና የተመዘገበውን ስኬት ስናወራ በገጠር አርሶ አደሩን በቀጥታ ስለሚደግፈውና ቀን ከሌሊት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ተራራ ገደሉ ሳይበግረው ከአርሶ አደሩ ጋር አብሮ የሚታትረውን የግብርና ባለሙያ አብረን እናነሳለን፡፡ ስለጤና ስናወራም እንዲሁ፡፡ የጤና ፖሊሲያችን መከላከልን መሰረት ያደረገ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኑ ከዚህ ባሻገር ያሉ አገልግሎቶችም ቀላል የሚባሉ አይደሉም፡፡ የጤና ኤክስንቴንሽን ባለሙያን ለአብነት አንስተን ብንነጋገር እናቶችን በቀጥታ ከመደገፍና በተለይ ሁሉም በገጠሪቱ የአገራችን ክፍል የሚኖር ዜጋ ከዘልማዳዊና ኋላ ቀር የአኗኗር ዘይቤ እንዲወጣ፣ በመንግስት የቀረቡ የጤና አገልግሎቶችን እንዲጠቀም በመስተማርና መተግበራቸውንም በቀጥታ በመከታታል ጭምር ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ይከውናሉ፡፡ እናቶች ልጆቻቸውን ከጤና ተቋም ውጭ እንዳይወልዱ በጤና ተቋማ ያለመውለድ ጉዳትን በማስተማር፣ ያለእድሜ ጋብቻን አምርሮ በመታገልና የስነ ተዋልዶ ጤናንም በማስተማር የመንግስት ሰራተኛው የሚፈፅመው በገንዘብ የማይተመን ተግባር ለአገልግሎት ከሚከፈል ደመወዝ የዘለለ የዜግነት ኃላፊነትን መወጣት ጭምር እንደሆነ መገንዘብ እንችላለን፡፡ በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ትግበራ የጤናና የትምህርት ልማት ስኬትን ስናወሳ የመንግስት ሰራተኛው ይሄን ለማሳካት የተጓዘበትን ውጣ ውርድ አብረን እናወሳለን፡፡ እንደአገር አንድም ህፃን ከትምህርት ገበታው እንዳይቀር በሚደረገው ሁሉን አቀፍ እንቅስቀሴ የመንግስትን ረጅም ዓላማን የሚያሳኩትና በተጨባጭም ባለፉት ዓመታት የተገኙትን ስኬቶች ስናነሳም የስኬቱ ባለቤቶች እነዚሁ በመስኩ የተሰማሩ  ፐብሊክ ሰረቫንቶች እንደሆኑ መገንዘብ ያስፈልጋል፡

በከተማም ያለው ሁኔታ ተመሳሳይ ነው፡፡ ስለጥቃቅንና አነስተኛ፣ ስለጤና አገልግሎት፣ ስለ መሰረተ ልማትና በመንግስት የሚቀርቡ የተለያዩ አገልግሎቶችን ስናነስ የመንግስት ሰራተኛው አብሮ ይነሳል፡፡ እንደአገር በሚከናወኑ ማናቸውም እንቅስቀሴዎች ውስጥ የመንግስት ሰራተኛው ሚና ተነጥሎ የሚታይ አይደለም፡፡ ይህ የሚያመላክተው የመንግስት ሰራተኛው ጥንካሬና ቁርጠኝነት እንደ አገር ለሚከናወኑ ማናቸውም ተግባራት መጻኢ እድል ወሳኝ መሆኑን ነው፡፡ በአጠቃላይ የመንግስት ሰራተኛው በአገራችን ለተመዘገበው ተከታታይ እድገት ያበረከተው አስተዋፅኦ የላቀ መሆኑን ማየት ይቻላል፡፡ ይህ እውነታ እንደተጠበቀ ሆኖ ባሳለፍነው ዓመት እንደ አገር በገጠሙ ፈተናዎች  ፐብሊክ ሰርቪሱ የመልካም አስተዳደር መርሆዎች ላይ ቆሞ ከመስራት አኳያ የገጠመው መሸራረፍ በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ቁጠን መቀስቀሱ ይታወሳል፡፡

ህዝባችን ከሚያነሳቸው አብይ ጥያቄዎችና ኢህአዴግ በጥልቅ ተሃድሶ ከለየው አንገብጋቢ ጉዳይ አንዱ የአድሎአዊ አሰራር መኖርና ኃላፊነትን ለራስ ጥቅም የማዋል ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር በፐብሊክ ሰርቪሱ የአገልጋይነት ስሜት መጥፋትና ኪራይ ሰብሳቢነት መንገስም ይጠቀሳል፡፡  ይህ ደግሞ ዞሮ ዞሮ መጠኑ ይለያይ እንጂ የመንግስት ሰራተኛው መውሰድ ያለበት ኃላፊነት ጭምር ነው፡፡ በታማኝነት በቅንነትና በህዝብ አገልጋይነት ስሜት የመንግስት አገልግሎትን ለህዝብ የሚያቀርቡ የመንግስት ሰራተኞች የመኖራቸውን ያህል በቅድመ ሁኔታ፣ ማባበያ በመጠየቅና ለህዝብ የተሰጠን ጊዜ በመሸራረፍ ፈፅሞ ህዝባዊነትን ባልተላበስ ስሜት ውስጥ ሆኖ ስራውን ባልተገባ ሁኔታ የሚጠቀም ሰራተኛም ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ በእጅ መንሻ ካልሆነ አንድ ገፅ ፋይል ገልፆ የማያይ ሙስና መቀበልን እንደግዴታ ቆጥሮ በድፍረት በመንግስት አገልግሎት ኪራይ የሚሰበስብ ፈፃሚ ለጉድ መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ በአጠቃላይ ፐብሊክ ሰርቪሱ በባለፉት ዓመታት እንደ አገር በተመዘገቡ በርካታ ስኬቶች ውስጥ የጎላ ድርሻ ያለውን ያህል የተመሰቃቀሉ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩና የህዝብ ቁጣም እንዲገነፍል ያበረከቱት አሉታዊ አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም፡፡ በመሆኑም ስለ አለፈው ችግራችን ስናነሳ ፐብሊክ ሰርቪሱ የነበረውን ስኬትና ተግዳሮት በልኩ መውሰዱ የግድ ይላል፡፡ ስለቀጣይ ረጅሙ የህዳሴ ጉዟችንም ስናነስ እንዲሁ  ፐብሊክ ሰርቪሱ ራሱን ለዛ ማዘጋጀትና ራሱን ከአገራዊ ተልዕኮና ዓላማ አንፃር መመዘን እንደሚገባው ማስቀመጥ ግድ ይሆናል፡፡

ውድ አንባብያን ሁላችንም እንደምናስታውሰው የኢሕአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባደረገው መደበኛ ስብሰባው የመንግስት ሰራተኞች፣ የህዝብና የወጣት ባለድርሻ አካላት ውይይቶች እንዲከናወኑ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ እንደ አገር የተጀመረውን ጥልቅ ተሃድሶ መሬት ማስነካትና በውጤት ማጀብ የሚቻለውም ሁሉም የራሱን መልካም ጎኖች በማጎልበትና መሻሻል የሚገባቸውን ችግሮች ደግሞ ያለርህራሄ መመልከትና የመፍትሄ አካል መሆን ሲችል በመሆኑ ይህን ማስጨበጥ የሚችል ውይይት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ ተጀምሯል፡፡ የመንግስት ሰራተኛው የጥልቅ ተሃድሶ ሂደት አንዱ ሲሆን ውይይቱ መልካም በሚባል ደረጃ የተለያዩ ገንቢ ሃሳቦች እየተንሸራሸሩበት የተጀመረ ሲሆን ሂደቱ በተለያዩ ተቋማትም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡


በእኔ እይታ ውይይቱ ተገቢና ወቅቱን የጠበቀ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ኢህአዴግና ኢህአዴግ የሚመራው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስታችን እንደአገር ባለፉት ዓመታት የታዩ ችግሮችን በመለየት የተሃድስ እንቅስቃሴ ውስጥ ገብቷል፡፡ ይህ አገራችንን ከሩቅ ለማድረስ ካለው ፍላጎትና ቁርጠኝነት መሆኑን መገመት አያዳግትም፡፡ የመንግስት ሰራተኛውም በዚህ የህዝባዊነት መንፈስ ነገሮችን መመልከት የሚገባው ይሆናል፡፡ የመንግስት ሰራተኛው ከራስ ጥቅም በላይ የህዝብ አጀንዳ ይበልጣል የሚል እምነት መያዝ አለበት፡፡ መንግስት በተለያየ አጋጣሚ ሲገልፅ እንደተሰማው የመንግስት ሰራተኛው ያልተሳተፈበት ልማት ሰላምና ዴሞክራሲ በውሃ ጠብታ ግዙፍ ድንጋይን እንደመስበር በመሆኑ የመንግስት ሰራተኛው እያንዳንዱ መልካም ተግባሩ አገርን የሚያለማ፤ አንድ ቅንጣት የጥፋት አካሄዱ ደግሞ በህዝብ ሁለንተናዊ ለውጥ ላይ እንደመቆም መሆኑን ከልብ መቀበል ይኖርበታል፡፡ የፐብሊክ ሰረቫንቱ ህዝባዊ ወገንተኝነት መላበስ ዞሮ ዞሮ ለራስ ጥቅም እንደመስራት አድርጎ መውሰድ ይገባል፡፡  ፐብሊክ ሰረቫንቱ ከህዝብ በተሰበሰበ ገቢ የሚከፈለው ከመሆኑ ባሻገር የራሱን ወገን የሚያገለግል መሆኑ ደግሞ በራሱ የሞራል ግዴታም ጭምር ያለበት መሆኑን ተገንዝቦ በዛ መንፈስ መስራት ይገባዋል፡፡ ፐብሊክ ሰርቪሱ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል አይነት አስተሳሰብ ውስጥ ከገባ አገራችንን ወደ ቁልቁለት የሚወስድ በመሆኑ  ፐብሊክ ሰርቪሱ ችግሮችን ወደራሱ አስጠግቶ በማየትና አሉ የሚባሉ ችግሮችንም ጭምር ለቅሞ በማሳየት የህዳሴ ጉዟችንን ለማሳለጥ በሚከናወኑ ተግባራት ውስጥ የራሱን ማዕተም ማሳረፍ ይኖርበታል ባይ ነኝ፡፡ ፐብሊክ ሰርቪሱ የአገልጋይነት መንፈስን በማጎልበት ለህዳሴያችን መሰረት መሆን ይገባዋል፡፡ ሰላም፡፡   

Friday, 20 January 2017

በጋራ ጥረት የሚሳካ አበረታች እንቅስቃሴ


(በኤፊ ሰውነት)
በአገራችን የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ እውን መሆን የጀመረው አህአዴግ ከመላው የአገራችን ህዝብ ጋር በመሆን አምባገነን የሆነውን የደርግ ስርዓት በገረሰሰ ማግስት መሆኑ ይታወቃል፡፡ በደረግ ዘመነ መንግስትም ሆነ ከዛ በፊት ባሉ የስልጣን ዘመናት በአገራችን የሃሳብ ልዩነትን የሚያስተናግድ አስቻይ ሁኔታ ፈፅሞ እንዳልነበረ ይታወሳል፡፡ ነገስታቱም ሆነ ደርግ ስልጣንን ለህዝብ ማገልገያ መሳሪያነት ሳይሆን የማይነካ የተጠበቀ ቦታ አድርገው በመውሰዳቸው የሃስብ ልዩነት ያላቸውን ስብስቦች ለመቀበል እንኳንስ የህግ ይቅርና የሞራል ዝግጅትም አልነበራቸውም፡፡

አሁን በአገራችን እያጣጣምነው ስላለው ዴሞክራሲና የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ሁኔታ ስናወራ እያወራን ያለነው የ25 ዓመታት እድሜ ልምድን መሆኑን መገንዘቡ አይከፋም፡፡ በእኔ እምነት ዴሞክራሲ በህብረሰተብ ውስጥ እየተገነባ የሚሄድ የአስተሳሰብ ስልጥንና ነው፡፡ የመናገር የመጻፍና የመቃወም መብቱ ለዘመናት ተነፍጎ ለቆየ የህብረተሰብ ክፍል ስለ ዴሞክራሲ አጠቃላይ ሁኔታ ያለውን ግንዛቤ ይዞት ከመጣው አስተሳሰብ ጋር ለማዛመድ ጊዜ የሚወስድበት ከመሆኑ ባሻገር ምናልባትም ዴሞክራሲ የሚለው ሃሰብ በራሱ የተገለለና አላስፈላጊ አድረጎ መቁጠሩም ሆነ በአግባቡ መጠቀም ላይ በሁሉም የህብረተሰባችን ክፍል መኖሩ የማይቀር ነው፡፡ በአገራችን የ25 ዓመታት ጉዞ ውስጥ ዴሞክራሲያችን ከተነሳበት አንፃር እየጎለበተ ይምጣ እንጂ አሁንም በብዙ ተግዳሮቶች የተሞላ መሆኑን ማስመር ያስፈልጋል፡፡

ስለዴሞክራሲ ስናወራ ምርጫ ቦርድን ጨምሮ ሌሎች ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን ማንሳታችን አይቀርም፣ ስለዴሞክራሲ ስናወራ የህዝብ ተሳትፎን እናወራለን፣ ስለዴሞክራሲ ስናወራ ስለ መንግስት ስልጣንና የስልጣን ክፍፍል እናነሳለን፣ ስለዴሞክራሲ ስናነሳ ተያይዘው የሚነሱ በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ ይህ የሚያመላክተው ዴሞክራሲንና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የመጠቀም ጉዳይ ሰፊና የራሱን ጊዜ የሚፈልግ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ በአገራችን የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ እውን ከሆነበትና ስልጣን በዜጎች መልካም ፍቃድ ላይ በተመሰረተ ነፃ ምርጫ መወሰን ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን የመጠቀም ልምዳቸው ከመጎልበቱ ባሻገር የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታችንም እየዳበረ መምጣት ችሏል፡፡

የመድብለ ፓርቲ ስርዓት በአገራችን እውን መሆኑ በአገራችን የህዝብን ስልጣን መምራት የሚችለው በህዝብ የተመረጠ ፓርቲ መሆኑን ከመስረገጡ ባሻገር ዜጎች መብቶቻችንን ያስከብሩልናል ብለው ባሰቧቸው ድርጅቶች ላይ ራሳቸውን በማስገባት መብቶቻቸውን የሚጠቀሙበት እድል ሰፊ እንዲሆን አስችሏል፡፡ በዚህም ባለፉት ዓመታት ለመድበለ ፓርቲ ዴሞክራሲው መፋፋት የራሳቸውን ድርሻ መወጣት የሚችሉ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመዝግበው ፍላጎታቸውን በማንፀባረቅ ላይ ይገኛሉ፡፡

በያዝነው ሳምንት የህዝብ ስልጣን እየመራ ያለው ኢህአዴግ እና 20 የሚሆኑ ህጋዊ በሆነ መንገድ ተመዝግበው በአገር ውስጥ እንቅስቃሴ እያደረጉ ያሉ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች በአገራቸው ጉዳይ ላይ ውይይትና ድርድር ለማካሄድ የሚያስችላቸውን ስምምነት አድርገዋል፡፡
ኢህአዴግና ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ ባካሄዱት ውይይት በሚያስማሙ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ለማካሄድና ድርድርና ክርክር በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ ደግሞ እንደአስፈላጊነቱ ድርድር ወይም ክርክር ለማካሄድ የሚያስችላቸው ቅደመ ሁኔታ ማዘጋጀት ላይ ተወያይተዋል፡፡ በዚህም በቀጣይ ከሚካሄዱ የጋራ መድረኮች በፊት በስብሰባ ስናስርዓት፣ በአጠቃላይ የመድረክ ሁኔታና በታዛቢ መረጣ ዙሪያ ሊኖሩ የሚገቡ ቅድመ ሁኔታዎችን አማራጮችን በጽሑፍ እስከ ጥር 25 ቀን 2009 . ድረስ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት /ቤት ለማስገባት ተግባብተዋል፡፡

በውይይቱ በአብዛኛው የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ይህ ውይይት መጀመሩንና የቀጣይ ድርድሮችንም ሆነ ክርክሮችን ለማድረግ በሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎች ላይ ለመነጋገር ኢህአዴግ ኃላፊነቱን ወስዶ መሰብሰቡ የሚመሰገን መሆኑን የገለፁ ሲሆን ፓርቲዎቹ ቀጣይነቱ ላይ ያላቸውን ስጋት ኢህአዴግ ምን ያህል ቁርጠኛ ነው የሚል ሃሳብ በመሰንዘር ገልጸዋል፡፡
ኢህአዴግ በአገራችን የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ እንዲጎለብት በአገር ውስጥ ካሉ ህጋዊ  የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ያለውን ፍላጎትና ቁርጠኝነት በተደጋጋሚ ገልጿል፡፡ ኢህአዴግ በአገራችን ያሉ ህጋዊ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደየራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ የሚደግፏቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ያሉ በመሆነቸው እነዛ የህብረተሰብ ክፍሎች ድምፃቸው የሚሰማበት ሁኔታ መኖር እንዳለበት ያምናል፡፡ በመሆኑን የምርጫ ህጉን ከማሻሻል ጀምሮ ሌሎች ርምጃዎችንም ለመውሰድ ያለውን ቁርጠኝነት አሳይቷል፡፡ በመሆኑም ኢህአዴግ በተለያዩ ድርጅታዊ ስብሰባዎችና መግለጫዎች እንዳሳወቀው ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የሚያደርገውን ተቀራርቦ የመስራት ቁርጠኝነት አጠናክሮ የሚቀጥልበት መሆኑን ከህዝባዊ ባህሪው በመነሳት መደምደም ይቻላል፡፡
በውይይቱ እንደተመላከተውም ኢህአዴግ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች በተጨማሪ ከምሁራንና ከሲቪክ ማህበራት ጋር ውይይት እንደሚያካሄድ በማስታወቅ ሁሌም ቢሆን ልምዶቻችንን በመቀመርና በቀጣይ መስተካከል የሚገባቸው ሁኔታዎች ላይ በመወያየት በአገራችን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታችን እንዲያብብ እንደሚሰራ ውይይቱን ሲመሩ የነበሩት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ አስረግጠው ገልጸዋል፡፡

ውድ አንባብያን በእኔ እምነት ያለውን የሰጠ ንፉግ አይባልም ነውና ተረቱ ኢህአዴግ ከተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር አብሮ ለመስራት ያለውን ቁርጠኝነት በተደጋጋሚ መግለፁ ይበል የሚያሰኝ ነውና ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች አብረው መስራታቸውና መታረም ያለባቸውን በማረም መጎልበት ያለባቸውን ደግሞ እንዲጎለብቱ በማድረግ ሁሉም ለአገራቸው የሚበጀውን ማድረጋቸው ዞሮ ዞሮ ጥቅሙ ህዝብ ላይ የሚያርፍ ነውና መጠራጠሩን ወደ ጎን በመተው በተጨባጭ ጉዳዮች ላይ በርትቶ መስራት ይጠበቃል፡፡


የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ 2009 . የመንግስትን የትኩረት አቅጣጫዎች ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለፌዴሬሽን ም/ቤት የጋራ የመክፈቻ ስነስርዓት ባቀረቡበት ወቅት በአገሪቱ ውስጥ በህጋዊና ሰላማዊ መንገድ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የተለያዩ የውይይት መድረኮች እንደሚካሄዱ መግለጻቸው ይታወሳል። ይህን ተከትሎም በጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የሚደረጉ ውይይቶች የሚከታተል ማዕከል ተቋቁሟል። መሪ ድርጅቱ ኢህአዴግም ከሰላማዊና ሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይቶች ለማድረግ መዘጋጀቱን አስታውቋል። ይህ የኢህአዴግን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ በመሆኑ ሁሉም ፖለቲካ ፓርቲዎች የነገዋን ሰላማዊና ዴሞክራያዊ ኢትዮጵያ ለመገንባት የጋራ ርብርብ የሚጠይቅ የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ በመግባት የድርሻቸውን ለመወጣት መትጋት ይገባቸዋል፡፡ በእኔ እይታ ይህ የተጀመረው እንቅስቃሴ ግን በራሱ ግብ ባይሆንም ይበል የሚያሰኝ ነውና ሳይደናቀፍ እንዲቀጥል ሁሉም ፓርቲዎች በቁርጠኝነት ሊሰሩ ይገባል ባይ ነኝ፡፡ ሰላም፡፡ 

Tuesday, 17 January 2017

የአገራችን ህዳሴ መሰረትበኤፊ ሰውነት

ወጣትነት ለነገ መሰረት የሚጥሉበት፤ የእርጅና ጊዜዎ በሃሴት እንዲያልፍ የሚተጉበት ሁሉን ማሰብ ማቀድና መከወን የሚችሉበት የጉብዝና ጊዜ ነው፡፡ ወጣትነት ያሰቡትን ሁሉ ማድረግ እንደሚችሉና አንዳንዴም በአዕምሮ የመጣን ነገር ሁሉ ለማስተናገድ የሚራወጡበት፤ ህልምዎን ለማሳካት አማራጭ ያሉትን መንገድ ሁሉ የሚጠቀሙበት የትኩስነት ወቅትም ነው፡፡ ወጣትነትን ሁሉም የሚደርስበትና የሚያልፍበት በመሆኑ ከራስ ሁኔታ በመነሳት ብቻ ስለወጣትነት ብዙ ማለት አያዳግትም፡፡ ይህ እውነታ እንዳለ ሆኖ ወጣትነት ብስለት በተሞላበት ሁኔታ መመራት የሚገባው የእድሜ ክልል መሆኑም አያጠያይቅም፡፡ ይህን የትኩስነት ጊዜ ረጋና ሰከን ብሎ ወጣት በመሆን ብቻ የሚገኝን ብርታትና ጉጉት ወደ መልካም ሁኔታዎች መቀየር ግድ የሚል ይሆናል፤ ወጣትነት በቅጡ ካልተመራ ጥፋትም ሊሆን ይችላልና፡፡

ይህን ካልኩ በአገራችን ታሪክን ስለቀየሩ ወጣቶችና ዛሬም ታሪክ እየቀየሩ ስላሉ የዘመናችን ብሩሃን አንዳንድ ነገር ማንሳት ፈለኩኝ፡፡ መቼም ትናንት ከሌለ ዛሬ፤ ዛሬ ከሌለ ደግሞ ነገ የለምና እናንተንም ወደ ትናንት ልመልሳችሁ ግድ ሆኗል፡፡ ከዛሬ ሃያ አምስት ዓመታት በፊት በደርግ ዘመነ መንግስት፤ ከዛሬ ሰላሳና አርባ ዓመታት በፊት ደግሞ የአፄ ሃይለስላሴ ዘመነ መንግስትን በዓይነ ህሊናችን ስናስታውስ የወጣትን ህዝባዊነትና አገር የመለወጥ ሃይል በተጨባጭ መመዘን ያስችለናል፡፡ እነዛ ወጣቶች ምን ያህል በአገራቸው ያልነበረውን የእኩልነትና በአገር ሃብት እኩል የመጠቀም መብት ለማረጋገጥ መስዋዕት እንደከፈሉና እንደተሳካላቸውም እናያለን፡፡ የመሬት ላራሹ ንቅናቄን ጨምሮ የአገራችን ምሁራንና አርሶ አደር ወጣቶች ለመላው የአገራችን ጭቁን ህዝብ ነፃነት የከፈሉትን ተጋድሎ ማሰብ የወጣትን ሃያልነት ለመረዳት ቀላል ነው፡፡  

የቅርቡን ብናነሳም የህዝብ ሸክም በጫንቃቸው የተሸከሙ፤ የህዝብ ህመም ህመማቸው የሆኑ ጥቂት የአገራችን ወጣቶች የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸው፤ ፓይለትነት፣ መሃንዲስነትና ዶክተርነት ሳያጓጓቸው የአገራችን ጭቁን ህዝብ እየከፈለው ያለው ዋጋ እንቅልፍ ቢነሳቸው ሁሉን እርግፍ አድርገው የህዝብን ትግል በመምራት በከፈሉት መስዋዕትነት ሩቅ የመሰለውን ቅርብ ከባድ የመሰለውን ቀላል አድርገው በእልህ አስጨራሽ ትግልና በመሪር ተጋድሎ የአገራችን ህዝብ የሰላም አየር እንዲተነፍስ መብቱና ነፃነቱ ህገ መንግስታዊ እውቅና እንዲያገኝና አገራችን ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ተከባብረውቧት የሚኖሩ የመፈቃቀድና የመተባበር አገር እንድትሆን አስችለዋል፡፡

የዛሬዋ ኢትዮጵያ ከትናንት የተለየች እንድትሆን ያደረጉ የትናንት ወጣቶች ናቸው፡፡ ዛሬ በአገራችን ያለው የኢኮኖሚያዊ ማህበራዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች መከበር የቻሉት የትናንት ወጣቶች መላው የአገራችንን ህዝብ አስተባብረው ለድል በማብቃታቸው ነው፡፡ ይህ እውነታ ወጣቶች ሁሌም ቢሆን በአገራቸው የትናንትና የዛሬ ታሪክ ውስጥ በማይጠፋ ማዕተም የተፃፈ ታሪክ ባለቤትና ባለውለታ ብሎም ወጣቶች በአገራቸው ጉዳይ ሁሌም ቢሆን የማይደራደሩ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ተጨባጭ ማሳያ ነው፡፡

የዛሬ 25 ዓመት በህዝብ ትግል፤ በቆራጥ ወጣቶች መሪነት አምባገነንና በተለይ ለወጣቶች ፈፅሞ የማይመቸው ስርዓት ተገርስሶ በምትኩ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ድርጅት የሆነው ኢህአዴግ አገር የማስተዳደር ስልጣን ከተረከበ በኋላ ከህገ መንግስቱ ጀምሮ የተለያዩ ህጎች፣ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እንዲሁም አሰራሮችና አደረጃጀቶች ሁሉ የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሆነው ተቀርፀዋል፡፡ በዚህም ባለፉት 25 ዓመታት በአገራችን ቀላል የማይባል ቁጥር ያለውን ወጣት በሁለንተናዊ መልኩ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡ የወጣቶችን ጉዳይ የሚከታተል መዋቅር ከፌዴራል ጀምሮ እስከ ወረዳ ድረስ በመዘርጋትም የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት የሚያጎለብት ተግባር ተፈፅሟል፡፡

ኢህአዴግ የሚመራው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት ባለፉት ዓመታት ለወጣቶች ልዩ ትኩረት በመስጠት ባከናወናቸው ተግባራት በገጠር ወጣቶች በግብርናና ከግብርና ውጭ ባሉ የስራ አማራጮች ሰፊ የስራ እድል እንዲፈጠርላቸውና የኢኮኖሚ አቅማቸውን በማሳደግ ህይወታቸው እንዲለወጥ ተደርጓል፡፡ በከተማም የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ስትራቴጂን በመቅረፅና ተግባራዊ በማድረግ ወጣቶች በአምስቱ የእድገት ተኮር ዘርፎች ተሰማርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ በመደረጉ ቁጥራቸው የማይናቅ ወጣቶችም ወደ መካከለኛ ባለሃብትነት በመሸጋገር ከራሳቸው አልፈው ህብረተሰባቸውንና አገራቸውን መጥቀም የሚችሉና ለሌሎች አርዓያ መሆን የሚችሉ ወጣቶች ማፍራት ተችሏል፡፡  

ከዚህ ባሻገር የአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር ወጣቶችን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመፍታት የማህበረሰቡን የአኗኗር ዘይቤ መሰረት ያደረጉ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የፖለቲካ ስራዎች በመከናወናቸው በተበታተነ ሁኔታ ሲኖሩ የነበሩትን የአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር ወጣቶች መሰረታዊ ችግሮች የማቃለልና ቋሚ የአኗኗር ዘይቤ እንዲከተሉ ማድረግ ተችሏል፡፡

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ አሁንም የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት በሁለንተናዊ መንገድ ከማጎልበት አኳያ ብዙ የሚቀሩ ስራዎች እንዳሉ እሙን ነው፡፡ በተደጋጋሚ እንደሚገለፀው ከጠቅላላው የአገራችን ህዝብ ከሰላሳ በመቶ በላይ የሚሸፍነው አምራች ወጣት የህብረተሰብ  ክፍል ነው ይህ አሃዝ የሚያመላክተው አገራችን ኢትዮጵያ የወጣቶች አገር መሆኗን ጭምር ነው፡፡ በመሆኑም ዘላቂ ልማትና ቀጣይነት ያለው ዴሞክራሲ ለማረጋገጥም ሆነ የኢትዮጵያን ህዳሴ እውን ለማድረግ የወጣቶችን ተሳትፎ ማሳደግና ተጠቃሚነታቸውንም ማረጋገጥ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስታችን ይህን እውነት በቅጡ በመገንዘብ ለወጣቶች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ባለፉት ዓመታት ብሄራዊ የወጣቶች ፖሊሲ እና የወጣቶች የእድገት ፓኬጆችን በማዘጋጀትና የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በያዝነው በጀት ዓመትም መንግስት የወጣቶችን ተሳትፎ የማጎልበትና ተጠቃሚነታቸውንም የማረጋገጥ ጉዳይን በልዩ ሁኔታ በመያዝ ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

በአገራችን አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ እንደሚያረጋግጠው ማንኛውም ዜጋ በነፃነት የመስራት የፈለገውን ያህል ሃብት የማፍራት ነፃነቱ የተጠበቀ በመሆኑ ወጣቶችን ጨምሮ በርካታ ዜጎች ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡ በገጠርም በከተማም ሚሊዬነር የሆኑ ወጣት ባለሃብቶችን ማፍራት ተችሏል፡፡ ምርትና አገልግሎታቸውን ወደ ውጭ መላክ የጀመሩ የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ሚሊዬነር አንቀሳቃሾችም ያለፉት ዓመታት ትሩፋቶች ናቸው፡፡ ከራሳቸው አልፈው ቤታቸውን ቤተሰባቸውንና ህብረተሰባቸውን መጥቀም የጀመሩ ወጣቶች ቁጥር ቀላል አይደለም ይህ መጠናከር ያለበት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በራሱ ግን ቀላል ውጤት ተደርጎ አይወሰድም፡፡ ወጣቶች ህገ መንግስታዊ መብታቸውን በመጠቀምና ከአቻዎቻቸው ጋር በመደራጀት መብቶቻቸውን የሚጠቀሙበት ስርዓት እውን መሆኑ የወጣቶች የፖለቲካ ተሳትፎና የውሳኔ ሰጭነት ሚናን ከማሳደጉ ባሻገር ችግራቸውን በራሳቸው መንገድ ተወያይተው የሚፈቱበትን ሰፊ እድልም የፈጠረ መሆኑን ካለፉት ዓመታት ተጨባጭ ውጤቶች መገንዘብ ይቻላል፡፡

ውድ አንባብያን ኢህአዴግ የሚመራው ልማታዊና ዴሞከራሲያዊ መንግስት የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማጎልበት እንቅፋቶች ሁሉ መወገድ እንደሚገባቸው ያምናል፡፡ በአድሎአዊና ግልፅ ባለሆነ አፈፃፀም የሚፈጠሩ መስተጓጎሎችንም ሆነ ሌሎች በአገልግሎት አሰጣጥ በኩል ያሉ የመልካም አስተዳደር እንቅፋቶችን ጨምሮ የወጣቶችን የፋይናንስና የክህሎት ክፍተትን ለመሙላት እየተሰራ ይገኛል፡፡ ወጣቶች ስራ ፈጣሪ ከመሆንም ይሁን በተፈጠረው የስራ እድል ከመጠቀም አኳያ ያለባቸውን የአመለካከትም ሆነ የአሰራር ማነቆ ለመፍታት መንግስት ከመቼውም ጊዜ በተሻለ መልኩ እየሰራ ይገኛል፡፡ ወጣቶች በተለያየ ጊዜ የሚያነሱትን የተሳትፎና የተጠቃሚነት ጥያቄ ደረጃ በደረጃ ለመመለስም ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ ከዚህ አኳያ ከጊዜው ጋር የሚሄድና የወጣቶችን የተጠቃሚነት ደረጃ የሚያሳድግ ፓኬጃና ማስፈፀሚያ ስትራቴጂ ወጥቷል፡፡ በያዝነው ዓመት ተሻሽሎ የወጣው ይህ የኢትዮጵያ ወጣቶች የልማትና የእድገት ፓኬጅና ስትራቴጂ እንዲሁም አሰራሮችን ለመተግበር እየተወሰደ ያሉ ሌሎች እርምጃዎች የልማታዊ መንግስታችንን ቁርጠኝነት የሚያመላክቱ ናቸው፡፡

ሁላችንም እንደምናውቀው በ1998 እና በ2002 አጠቃላይ ከወጣቶች ብሄራዊ ፖሊሲና ህገ መንግስት መርሆዎች ጋር የተቃኘ የወጣቶች ፓኬጅና የእሱ ማስፈፀሚያ ስትራቴጂ ወጥቶ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ በዚህም በርካታ ወጣቶችም ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡ በያዝነው በጀት ዓመት ደግሞ ይህን በማሻሻልና በመከለስ የኢትዮጵያ ወጣቶች የልማትና የእድገት ፓኬጅና ስትራቴጂ ተቀርፆ ወጣቶች ግንዛቤ እንዲይዙበት ስልጠና በመሰጠት ላይ ይገኛል፡፡ የጉዳዩ ባለቤት የሆኑ ወጣቶች በፓኬጁና በስትራቴጂው ላይ እውቀት እንዲጨብጡና አለ የሚሉትን ተግዳሮትና ቀጣይ አቅጣጫዎችን የሚያመላክት ውይይት የሚያደርጉበት እድል መመቻቸቱም የመንግስትን ህዝባዊነት የሚያረጋግጥ መሆኑ ለሁላችንም ግልፅ ነው፡፡

በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሰቲ እየተሰጠ ባለው ስልጠና ተሳታፊ ወጣቶች በፓኬጁና ስትራቴጂው አጠቃላይ አፈፃፀምና ያለፉ ልምዶች ላይ ተንተርሰው ጥያቄዎችን በማንሳትና ውይይት በማድረግ የጋራ መግባባት ፈጥረዋል፡፡ በፀጥታ ዘርፍ የሚታዩ የአፈፃፀም ችግሮች፣ የስራ እድል ፈጠራ በቂ አለመሆንና፣ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ በጥቃቅንና አነስተኛ የስራ መስክ ላይ የሚታዩ ተግዳሮቶችና መሰል ጉዳዮች ላይ አለ የሚሉትን ሃሳብ ከፓኬጁ በመነሳት የሰነዘሩ ሲሆን የወጣቶችና ስፖርት ሚንስቴር የሆኑት አቶ ርስቱ ይርዳው ለወጣቶቹ ምላሽ በመስጠት በቀጣይ በጋራ መስራት እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡ 

አቶ ርስቱ ወጣቶች አለ ብለው ያነሷቸው ችግሮች በመሰረታዊነት በአፈፃፀም የሚታዩና መንግስትም መቀረፍ ያለባቸው ችግሮች መሆናቸውን አስቀምጦ እየሰራበት መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ በተለይ ከፀጥታ ሃይሉ ጋር ተያይዞ የተነሳው በማስተማርና በመገምገም እንዲሁም እርምጃ በመውሰድ ጭምር መንግስት የማስተካከያ ተግባራትን እየፈፀመ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን በተመለከተ አሰራር ከመዘርጋት ባለፈ በዚህ ተግባር ላይ የተሰማሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከህዝቡ ጋር በመሆን በመለየት እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አመላክተዋል፡፡ በተመሳሳይ የስራ እድል ፈጠራውን ለማስፋትና የፋይናንስና የክፍሎት ክፈተቱንም ለመሙላት መንግስት የአስር ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ ከመመደብ ጀምሮ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን አቶ ርስቱ ለሰልጣኞቹ ተናግረዋል፡፡ 

ኢህአዴግ የሚመራው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት ፓኬጁን መከለስ የፈለገበት ዋናው ዓላማም የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ በመሆኑ በፓኬጁ ያሉትን መልካም እድሎች አሟጦ በመጠቀምና በአፈፃፀም የሚታዩ ክፍተቶችንም በጋራ በመታገል ለተግባራዊነታቸው ሁሉም ወጣት በእኔነት መንፈስ ሊሰራ ይገባል የሚል እይታ አለኝ፡፡ የወጣቶች ችግር ጊዜ የማይሰጥና የተቀናጀ መፍትሄ የሚጠይቅ ጉዳይ በመሆኑ መንግስት በየጊዜው እያደገ የመጣውን የወጣቶች ቁጥርና የወጣቶች ወቅታዊ ጥያቄን በማጤን አገራችን ከደረሰችበትና ልትደርስበት ካቀደችው የእድገት ደረጃ ጋር የሚጣጣሙ ፕሮግራሞችን መንደፉ ይበል የሚያሰኝ ተግባር መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ በመሆኑም የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸውን በማሳደግ የአገራችንን እድገት ማረጋገጥ ለቀጣይ መሰረት የሚጥል በመሆኑ ወጣቶችም ሆነ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በዚህ መንፈስ በመረዳት ፓኬጁ መሬት ሲወርድ ሳይሸራረፍ እንዲተገበር መታገል ይጠበቃል፡፡

ውድ አንባብያን የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት በተመለከት እስካሁን ያሉትን መልካም ልምዶች በማጎልበት ክፍተቶችን ደግሞ በመሙላትና ወደ ተሻለ ምዕራፍ በማሸጋገር ሁሉም ዜጋ በተለይ ወጣቶች በተረጋጋና ብስለት በተሞላበት መንፈስ ነገን ያማረ ለማድረግ መታገል ይኖርባቸዋል፡፡ ነገ የሚያምረው የአገራችን ሰላሳ በመቶ የሚሆነው ወጣት የራሱን ተሳትፎና ተጠቃሚነት በማሳደግ ለህብረተሰቡና ለአገሩ ለውጥ መስራት ሲችል ነውና ወጣትንትን መጠቀም ብሩህና የበለፀገች ኢትዮጵያን መገንባት በመሆኑ በዚህ መንፍስ መስራት ግድ የሚል ይሆናል፡፡ ወጣቱ ትውልድ የነገ አገር ተረካቢ ብቻ ሳይሆን የአገራችንን ህዳሴ እውን ለማድረግ በሚካሄደው ዘርፍ ብዙ ርብርብም ያለውን እምቅ እውቅት፣ ክህሎቱንና ጉልበቱንም ጭምር በተገቢው መንገድ ለተገቢው ሁኔታ በመጠቀም የማይተካ ሚናውን ሊጫወት ይገባል፡፡ ወጣቱ የአገራችን ህዳሴ መሰረት መሆኑን በማመን አገራዊ ኃላፊነቱንም ጭምር በቁርጠኝነት ለመወጣት ዝግጁ ሊሆን ይገባል ባይ ነኝ፡፡ ሰላም፡፡


ያለ ወጣቱ የተሟላ ተሳትፎና ተጠቃሚነት የተጀመረውን ፈጣንና ተከታታይ የኢኮኖሚ እድገት ማስቀጠልና የአገራችንን ህዳሴ እውን ማድረግ አይቻልም!

Wednesday, 11 January 2017

የፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉ የሕዝቡን ንቁ ተሳትፎ ግድ ይላል

(በውብዓለም ፋንታዬ)
የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ በአንድ ወቅት የሚጠናቀቅ ሳይሆን በሂደት የሚከናወን ነው፡፡ የስርዓት ግንባታውን ከዳር ለማድረስ በሂደቱ ከውስጥና ከውጭ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ማለፍ ያስፈልጋል፡፡ በሀገራችን እየተካሄደ የሚገኘው የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ በእስከአሁኑ ሂደት ውጣ ውረዶች ሳይበግሩት በርካታ ድሎችን አስመዝግቧል፡፡ በሂደቱ ያጋጠሙ በርካታ ተግዳሮቶችን ታግሎ በማስተካከል ሂደቱን ለማሳለጥ ተሞክሯል፡፡

Tuesday, 10 January 2017

በትጋታችን ያገኘንው ውጤት

(በኤፊ ሰውነት)
እንደሚታወቀው 2007. ጀምሮ በተፈጠረው የኤልኒኖ ክስተት ምክንያት ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የዓለም አገራት በአየር ንብረት መዛባት ተፅእኖ ስር እንዲወድቁ የተገደዱበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ይህ በአገራችንም የክረምት ዝናብ ላይ ተፅእኖ ያሳደረ ሲሆን በተለይ በመኸር አብቃይና በአርብቶ አደር አካባቢዎች ከፍተኛ የሆነ ጫና አሳድሯል፡፡ የበልግ ዝናብ ባለመስተካከሉና የክረምት ዝናብም በኤልኒኖ ክስተት ምክንያት ተፅእኖ ስር በመውደቁ በአገራችን በምግብና መሰል ጉዳዮች ላይ ችግር መፈጠሩ ይታወሳል፡፡ በመኸር አብቃይና በአርብቶ አደር አካባቢዎች ላይ የዝናቡ ሁኔታ በመዛባቱ በግብርና ምርት፣ በውሃ፣ በጤና፣ በትምህርት ልማት ስራዎች፣ በምግብና ስነ ምግብ ዘርፎች ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተፅእኖ ያሳደረበት ሁኔታ ፈጥሮ ነበር፡፡ በወቅቱ በአገራችን የእለት ደራሽ እርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር 2007 ነሃሴ ወር ከነበረበት 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን 2008 ጥር ወር ወደ 10 ነጥብ 2 ሚሊዮን አድጎ ነበር፡፡

Thursday, 5 January 2017

እውነትም መደገም የለበትም!!


(በኤፊ ሰውነት)
በተቀመጠበት ወንበር ላይ ድርቅ ብሏል፡፡ የጓደኞቹ ጫጫታና ሁካታ ስምጥ ካለበት የሃሳብ ባህር አላባነነውም፡፡ ዝም ብሎ ላስተዋለው በሆነ ጭንቀትና ሃሳብ ውስጥ እየተብሰለሰለ እንደሆነ መገመት አያዳግትም፡፡ እኔም ከጓደኞቹ ተለይቶ እንዲህ መብሰልሰሉ ምን ሃሳብ ቢሸከም ነው በሚል ጠጋ ብዬ ሰላም ወንድሜ ብዬ ትከሻውን ነካ ነካ አደረግኩት፡፡ አንዳች ጅራፍ ያረፈበት ይመስል ለራሴም ድንጋጤ እስኪፈጥርብኝ ድረስ ድንብር ብሎ ተነሳ ግራና ቀኙን እያየ እ እ እ ይቅርታ ሃሳብ ውስጥ ገብቼ ያለሁበትን እንኳን ዘንግቻለሁ አለኝ፡፡ እኔም ሁኔታውን እየተከታተልኩት እንደነበር ነግሬው ከአጠገቡ ካለው ወንበር ላይ ቁጭ ብዬ እንድንጨዋወት ጋበዝኩት፡፡ ለመሆኑ ምንድን ነው በሆድህ የያዝከው ነገር አልኩት፡፡ ምነው ችግር አለ እንዴ? ዓይን ዓይኑን እየተመለከትኩኝ ብታጋራኝ ትንሽ ይቀልህ ይሆናል እናም እስቲ የሆንከውን አጫውተኝ በማለት ተማፀንኩት፡፡

Monday, 2 January 2017

የመንግስት ሰራተኞች ውይይት ስኬቶቻንን የምናጎለብትበትና ድክመቶቻችንን የምናርምበት ሊሆን ይገባል፡፡

በሀገራችን ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡት ለውጦች የመላ ህዝቡ ተሳትፎ፣ የፈጻሚው አካል ንቁ እንቅስቃሴና የኢሕአዴግ አመራር ድምር ውጤቶች ናቸው፡፡ የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ በቀረፃቸው ፖሊሲና ስትራቴጂዎች እየተመራ ኢህአዴግ የሚጠበቅበትን አበርክቷል፡፡ የህዝቡ ያልተቆጠበ ድጋፍና ተሳትፎ ደግሞ የወጡት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች አተገባበር ውጤታማ እንዲሆን አድርጓል፡፡ በየደረጃው በሚገኙት የመንግስት መዋቅሮች የሚሰራው ፈጻሚው ሃይል ወይም ሲቪል ሰርቫንቱም ከፖሊሲዎቹና ስትራቴጂዎቹ የተቀዱ እቅዶችን መሬት በማስነካት ፍሬ እንዲያፈሩ ተግቷል፡፡ የዚህ ድምር ከትላልቅ ከተሞች ጀምሮ እስከ ገጠር ቀበሌዎች የዘለቀ ለውጥ እንዲመዘገብ አስችሏል፡፡